የኢሬቻ በዓል ምንድን ነው? ለምንስ ይከበራል?

የኢሬቻ በዓል ከገዳ ሥርዓት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሲሆን በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ለዘመናት ሲከበር መቆየቱን የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ።

በኦሮሞ ባህል ማዕከል የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት አቶ አለማየሁ ኃይሌ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ የክርስትና እና የእስልምና ሐይማኖቶች መስፋፋትን ተከትሎ የገዳ ሥርዓትም ሆነ የኢሬቻ ክብረ በዓል እየተቀዛቀዘ መጥቶ ነበር ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት ግን የኢሬቻ በዓል መከበር እየተጠናከረ ከኢትዮጵያ ባሻገር በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ የኦሮሞ ብሔር አባላት በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ።

በዋናነት ግን በኢትዮጵያ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ፤ በቢሾፍቱ ከተማ ደግሞ የሆራ ሃር-ሰዲ ከመስቀል በዓል በኋላ ባሉት ቅዳሜ እና እሁድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በታደመበት በዓሉ ይከበራል።

ኢሬቻ የምስጋና በዓል ነው።

የኦሮሞ ሕዝብ ምድር እና ሰማይን ለፈጠረው ፈጣሪው ዋቃ ምስጋናውን ለማድረስ የኢሬቻ በዓልን ያከብራል ይላሉ የማኅበረሰቡ ባህላዊ መሪዎች።

የኦሮሞ ሕዝብ ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው፤ ኢሬቻ።

የኦሮሞ ታሪክ ምሁሩ ዲሪቢ ደምሴ፤ "ኢሬቻ ማለት ዋቃ (ፈጣሪ) የፈጠረውን ማመስገን ማለት ነው" ይላሉ።

ማኅበራዊ ደረጃ እና የእድሜ ልዩነት ሳይፈጠር የኦሮሞ ሕዝብ የኢሬቻ በዓልን ለዘመናት በጋራ ሲያከብር ቆይቷል።

ኢሬቻ የዘመን መለወጫ በዓልም ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በማለፉ በኢሬቻ ቀን ምስጋናውን ለፈጣሪ ያቀርባል።

በክረምት ወራት ተራርቆ ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ መስከረም ላይ ይገናኛል። ሕዝቡም ክረምቱን በፈጣሪ ፍቃድ የሞላው ውሃ ጎድሎ ከዘመድ አዝማድ አገናኝን ብሎ ምስጋና ያቀርባል።

ከጨለማ ወደ ብርሃን ላሸጋገረው አምላክ አምላክ ምስጋና ያቀርባል።

የአንትሮፖሎጂ ባለሙያው ገመቹ መገርሳ (ዶ/ር)፤ "ክረምት ለሊት ነው። ለሊት ደግሞ ጨለማ ነው። ጨለማ ለአውሬ እንጂ ለሰው ልጅ አይሆንም። ጨለማው ሲነጋ ደግሞ ብርሃን ነው፤ ብርሃን ሲሆን ሃሳብ የለም ደስታ እንጂ። 'መስከረም በረ'ባ ማለት ይህ ነው" በማለት የኦሮሞ ሕዝብ ከክረምት መገባደድ በኋላ የኢሬቻ በዓልን የሚያከብርበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

ዲሪቢ ደምሴ የኢሬቻ በዓልን ለማክበረ የሚወጣ ታዳሚ እንደ ሳር ወይም አበባ ያለ እርጥብ ነገር በእጁ ይዞ እንደሆነ ይገልጻሉ።

"'ፈጠሪያችን ሆይ አንተ ያጸደቅከው ነው አብቦ ፍሬ ያፈራው፤ ለዚህም እናመስግንሃለን' በማለት እርጥብ ነገር ተይዞ ይወጣል" ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ይናገራሉ።

ኢሬቻ የሰላም እና እርቅ

ዲሪቢ በኢሬቻ በዓል ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ለመላው የሰው ልጅ ሰላምና ደኅንነት ፈጣሪውን ዋቃን ይለምናል፤ ያመሰግናል ይላሉ።

የአንትሮፖጂ ምሁሩ አለማየሁ (ዶ/ር)፤ "የተጣላ ታርቆ፣ ቂሙን ትቶ በነጻ ልቦና ፈጣሪ ንጹህ ወዳደረገው የውሃ አካል ይሄዳል። ኢሬቻ ቀልብ የሚነጻበት ቦታ ነው" ይላሉ።

መልካ እና ቱሉ

የኢሬቻ በዓል ሁለት ጊዜ ይከበራል።

እነዚህም የክራምት ወራት እንዳበቃ የሚከበረው ኢሬቻ መልካ (የውሃ አካል ዳርቻ የሚከበር) እና በዓመቱ አጋማሽ ላይ የሚከበረው ኢሬቻ ቱሉ (በተራራማ ቦታ) ናቸው።

የታሪክ ባለሙያው ኢሬቻ መልካ የምስጋና በዓል ሲሆን ኢሬቻ ቱሉ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ፈጣሪውን የሚለምንበት በዓል ነው ይላሉ።

"በበጋው የፀሐይ ሃሩር ሰው እና ክብት በሚቃጠልበት ጊዜ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ እንዲዘንብ የኦሮሞ ሕዝብ ወደ ተራራ ወጥቶ ፈጣሪውን ይለምናል። ተራራ ላይ ተወጥቶ ሲለመን ፈጣሪ ቶሎ ይሰማል የሚል እምነት አለ" ይላሉ።

"ይህን ተራራ የፈጠርክ ፈጣሪ ወቅቱን የሰላም አድርግልን፣ የሰላም ዝናብ አዝንብልን፣ ጎርፍን ያዝልን፣ የተዘራው ፍሬ እንዲያፈራ እንለምንሃለን" እያለ በኢሬቻ ቱሉ ላይ ፈጣሪውን ይለምናል በማለት ዲሪቢ ደምሴ ያስረዳሉ።