የዚህ ሳምንቱ የዩኬ ምርጫ ተፎካካሪዎች እነማን ናቸው? ምርጫው ለስደተኞች ምን ይዞ ይመጣል?

የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ የአገሪቷ ጠቅላላ ምርጫ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫው ይካሄድበታል ያሉት ቀን ከሚጠበቀው የቀደመ ነው። ምርጫው ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው በሚወጥለው ዓመት ጥር ወር ላይ ነበር።

ሪሺ ሱናክ ምርጫው ቀድሞ እንዲካሄድ ለምን ፈለጉ? ዋነኛ ተፎካካሪዎች እነማን ናቸው? በምርጫው ድል ካልቀናቸው የሪሺ ሱናክ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ዕቅድ ምን ይሆናል?

ቢቢሲ በእነዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን ተመልክቷል።

በዩኬ አጠቃላይ ምርጫ የሚካሄደው መቼ ነው?

በዩኬ አጠቃላይ ምርጫ ሐሙስ ሰኔ 27/2016 ዓ.ም. ይካሄዳል። በአገሪቱ የፖለቲካ የሥልጣን ዘመን በአምስት ዓመት የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ወግ አጥባቂው ፓርቲ የመጨረሻውን ምርጫ ያሸነፈው በአውሮፓውያኑ 2019 ታኅሣሥ ወር ላይ በመሆኑ በሕጉ መሠረት ቀጣዩ ምርጫ መካሄድ የነበረበት ጥር 2025 ነበር።

ሆኖም ይጠበቅ ከነበረው ጊዜ በወራት ቀድሞ ከቀናት በኋላ ጠቅላላ ምርጫው ይካሄዳል።

የዩኬ ፓርላማ 650 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፣ መራጮች በታችኛው ምክር ቤት ይወክለናል የሚሉትን አንድ የፓርላማ አባል ይመርጣሉ።

አብዛኞቹ ተመራጮች የፖለቲካ ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩ ሲሆን፣ የተወሰኑ ደግሞ በግላቸው የሚወዳደሩ ናቸው።

ሪሺ ሱናክ ምርጫው ቀድሞ እንዲካሄድ ለምን ፈለጉ?

የሪሺ ሱናክ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ከ2021 ወዲህ በሕዝብ አስተያየት መለኪያ የሚያገኘው ነጥብ እየቀነሰ መጥቷል።

የቢቢሲ የፖለቲካ አርታኢ ክሪስ ሜሰን እንደሚሉት በፓርቲው ያሉ አንዳንድ ፖለቲከኞች ቀኑ ቢጨምርም ብዙ ነገሮች ላይሻሻሉ ይችላሉ የሚል ሃሳብ አላቸው። በመሆኑም ምርጫው ቀደም ብሎ እንዲካሄድ የተፈለገው ቀናት በጨመሩ ቁጥር የወግ አጥባቂው መዳከም ሊባባስ ይችላል በሚል ስጋት ነው።

በሌላ አገላለጽ “አሁን ላይ ምርጫው ካልተካሄደ ውድቀቱ ሊብስ ይችላል በሚል ነው” ይላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀራቸው ጊዜ ያስቀመጧቸው የተወሰኑ ዓላማዎች መሳካታቸውን አሊያም ለማሳካት በሒደት ላይ መሆናቸውን ለማሳየትም ዕድል ያገኛሉ።

አሁን ላይ ያለው የዋጋ ግሽበት ምጣኔ እንደ ስኬት ሊጠቀስ እንደሚችል የሚገልጹት የፖለቲካ አርታኢው፣ “የዋጋ ግሽበት በመንግሥት ተግባር ላይ ብቻ የተወሰነ ባይሆንም፤ መንግሥታት የሚወቀሱት የዋጋ ግሽበቱ ሲያሻቅብ ነው። በመሆኑም ሲቀንስ የተወሰነ ተቀባይነት ያገኛሉ ብሎ መጠበቅም ምክንያታዊ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

በዩኬ ከመስከረም 2022 እስከ መጋቢት 2023 ባሉት ሰባት ወራት ውስጥ የዋጋ ግሽበቱ 11.1 በመቶ ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ ግንቦት ላይ ይህ አሃዝ ወደ 2 በመቶ አሽቆልቁሏል።

“ምጣኔ ሃብቱ ላይ የሚታየው መሻሻል በትንሹም ቢሆን ለሪሺ ሱናክ ተስፋ ሰጪ ይመስላል” ብለዋል ክሪስ ሜሰን።

ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ያላቸው የሕዝብ አስተያየት

በቅርቡ የተሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት መለኪያ የሪሺ ሱናክ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ከዋና ተፎካካሪው ሌበር ፓርቲ ያነሰ የሕዝብ ተቀባይነት እንዳለው ያመለክታል።

ባለፉት 12 ወራት በተሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት ሌበር ፓርቲ ከ40 በመቶ በላይ ድምጽ ያገኘ ሲሆን፣ ወግ አጥባቂው ፓርቲ ማግኘት የቻለው 19 በመቶ ብቻ ነው።

ሆኖም የሕዝብ አስተያየት ሁልጊዜ ትክክል ስለማይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ፣ በዋጋ ግሽበቱ ላይ የታየው አበረታች ለውጥ እና በፓርቲው ፖሊሲ ላይ ያደረጉት ትኩረት ተቀባይነታቸውን ለመጨመር እንደሚረዳቸው ተስፋ ያደርጋሉ።

ሌላኛው 'ሪፎርም ዩኬ' ፓርቲ 16 በመቶ የሕዝብ አስተያየት በማግኘት በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሪፎርም ዩኬ ያለው ድጋፍ በአገሪቷ ቢስፋፋም ባለው ድጋፍ የፓርላማ መቀመጫ ለማግኘት ከባድ ሊሆንበት ይችላል።

ከዚህ ቀደም በአገሪቷ ከሚገኙ ፓርቲዎች ሦስተኛው ትልቅ ፓርቲ የሆነው ሊበራል ዲሞክራትም 10 በመቶ የሕዝብ አስተያየት ቢኖረውም በፓርላማ በሚያገኙት መቀመጫ ላይ ትኩረት አድርገው በመሥራት በምርጫው የፓርላማ መቀመጫ እንደሚያገኙ ተስፋ ሰንቀዋል።

የሪሺ ሱናክ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ዕቅድ ምን ይሆናል?

ሪሺ ሱናክ ከምርጫው በፊት የተወሰኑ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ እንደሚልኩ ቀደም ሲል ቃል ገብተው ነበር።

በአነስተኛ ጀልባዎች የኢንግሊዝ ቻናልን አቋርጠው በሕገ ወጥ መንገድ የሚገቡ ስደተኞችን ያስቆማል በሚል ይህንን የስደተኞች ፖሊሲ ማስፈፀም በሥልጣን ዘመናቸው ቅድሚያ የሚሰጡት ቁልፍ ተግባር እንደሆነም ተናግረው ነበር።

ሆኖም ጠቅላላ ምርጫው ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቅበት ቀን አስቀድሞ እንደሚካሄድ ካሳወቁ በኋላ ይህ ዕቅድ ተፈፃሚ የሚሆነው እንደገና ከተመረጡ በኋላ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም አወዛጋቢ የሚባለው ወደ አገሪቱ በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄያቸው ሂደት በሩዋንዳ እንዲታይ ለማድረግ የመላክ ሂደቱም ይዘገያል ተብሏል።

የዩኬ ፖለቲከኞች ሕገ ወጥ ስደትን ለመከላከል ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ከምርጫው በፊት ወደ ሩዋንዳ ስደተኞችን እንደሚልኩ ተጠብቆ የነበረ ሲሆን፣ ከምርጫው በፊት እንደማይላኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ሌበር ፓርቲ በበኩሉ በምርጫው ካሸነፈ ይህንን የመንግሥት ዕቅድ ለማጠፍ ቃል ገብቷል።

በዚህም ምክንያት ስደተኞች ወደ ሩዋንዳ ላይላኩ ይችላሉ የሚል ጥያቄን አጭሯል።

305 ሚሊዮን ዶላር እንደወጣበት የተገለጸው ይህ ዕቅድ በስድስቱ ሳምንት የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሁለቱ ዋና ተፎካካሪ ፓርቲዎች [ወግ አጥባቂው እና ሌበር ፓርቲ ] መካከል ዋነኛ የሚለያዩበት ጉዳይ ይሆናል።

የምርጫው ቁልፍ ተወዳዳሪዎች እነማን ናቸው?

በምርጫው አብዛኛውን ድምጽ ያገኛሉ ተብሎ የሚጠበቁት ገዢው ወግ አጥባቂው ፓርቲ እና ሌበር ፓርቲ ናቸው።

የ44 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ወግ አጥባቂውን ፓርቲ ይመራሉ። ሱናክ እአአ በ2022 ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲመረጡ 42 ዓመታቸው የነበረ ሲሆን፣ ይህም በዘመናዊ የአገሪቷ ታሪክ በዕድሜ ትንሹ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የዩኬ እና የሕንድ የዘር ሐረግ ያላቸው የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትርም ናቸው።

ተፎካካሪያቸው የሌበር ፓርቲ መሪ ሰር ኪር ስታመር 61 ዓመታቸው ነው። ስታመር እአአ በ2020 የፓርቲው መሪ ሆነው የተመረጡት ጀረሚ ቦርቢን በመተካት ነበር። ቀደም ብሎ የወንጀል ዐቃቤ ሕግ አገልግሎት ኃላፊ እና የሕዝብ ዐቃቤያነ ሕግ ዳይሬክተር ነበሩ።

ከምርጫው በፊት በምክር ቤቱ እና በአባላቱ ላይ ምን ተፈጠረ?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምርጫው በፊት ፓርላማውን እንዲበትኑ ንጉሡን በጠየቁት መሠረት ሐሙስ ግንቦት 30 ፓርላማው ተበትኗል።በዚህ ወቅት የፓርላማ አባላት ኃላፊነታቸውን ያጡ ሲሆን እንደገና ለመመረጥ ዘመቻ ማካሄድ ይጠበቅባቸዋል።

ከ100 በላይ የፓርላማ አባላት በሚቀጥለው ምርጫ እንደማይወዳደሩ ገልጸዋል።

መንግሥትም በምርጫ ዘመቻው ወቅት የሚኒስትሮች እና የመሥሪያ ቤት ተግባርን በሚገድበው ቅድመ ምርጫ ጊዜ ውስጥ ገብቷል።

የምርጫው ውጤት ከተገለጸ በኋላስ ምን ይሆናል ?

ድምጽ ከተቆጠረ በኋላ ንጉሡ ብዙ መቀመጫ ያገኘውን የፓርቲው መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን እና መንግሥት እንዲመሠርት ይጠይቃሉ።

በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ የምክር ቤት መቀመጫ ያገኘው ፓርቲ መሪ የተቃዋሚ መሪ ይሆናል።

የትኛውም ፓርቲ አብላጫ መቀመጫ ካላገኘ ከጠቅላላ ምርጫው በፊት አገሪቷን ሲመሩ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር በሥልጣን ላይ የሚቆዩ ሲሆን መንግሥት የመመሥረት ዕድል ያገኛሉ።

በዚህም ከሌላ ፓርቲ/ፓርቲዎች ጋር ጥምር መንግሥት ሊመሠርቱ ይችላሉ። በጥምር ፓርቲ የሚመራ መንግሥት ለመመሥረት ካልፈለጉ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን የፓርላማ አባላቱን ይዞ ለመምራት ይሞክራሉ።

ይህ ግን በራሱ የምክር ቤት አባላት ብቻ ሕግ ማጽደቅ እንዳይችል እና በሌሎች ፓርቲዎች በሚሰጠው ድምጽ ላይ ጥገኛ እንዲሆን ያደርገዋል።

ጥምር መንግሥት የመመሥረቱ ሃሳብ ካልተሳካ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣናቸው መልቀቅ ከፈለጉ ደግሞ የዋናው ተፎካካሪ ፓርቲ መሪ መንግሥት እንዲመሠርት ዕድል ይሰጠዋል። በተመሳሳይም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጥምር መንግሥት በመመሥረት አሊያም አነስተኛ የምክር ቤት መቀመጫ ይዞ ሊመራ ይችላል።