ገዢው ፓርቲ ብልጽግና በንጹሃን ላይ ግድያ መፈጸሙን አወግዛለሁ አለ

የኢትዮጵያ ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን እንደሚያወግዘወና የመንግሥት ሕግን የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 15/2014 ዓ.ም ማካሄድ የጀመረው የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አሸባሪ ባላቸው ቡድኖች በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን አውግዟል።

የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እያደረጉት ባለው ስብሰባ “በወቅታዊ አገራዊ የፀጥታ ጉዳይ’’ እንዲሁም “እየተወሰደ ባለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ላይ’’ ውይይት እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

“የሽብር ቡድኖቹ ይህን የቀቢጸ ተስፋ ጥቃት እየፈጸሙ ያሉት እየተወሰደባቸው ባለው ጠንካራ የሕግ ማስከበር እርምጃ የደረሰባቸውን ኪሳራ ለመሸሸግ ነው’’ ሲልም ሥራ አስፈጻሚው አመልክቷል።

ስለዚህም ሥራ አስፈጻሚው እየተካሄደ ባለው ስብሰባው ላይ እነዚህን ግድያዎች ለማስቆም እየተካሄደ ያለው “ሕግን የማስከበር እርምጃ" ተጠናክሮ እንዲቀጥል "አቅጣጫ" ማስቀመጡም ተጠቁሟል።

ባለፈው ሳምንት ውስጥ በጋምቤላ እና በኦሮሚያ ክልሎች በታጣቂ ቡድኖች በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

ሰኔ 07/2014 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።

ይህንን ተከትሎ ደግሞ በምዕራብ ኦሮሚያ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ በሚገኙ መንደሮች ላይ ቅዳሜ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ. ም. በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪል ሰዎች መገደላቸው በርካቶችን ያስቆጣ ክሰተት ሆኗል። 

በምዕራብ ኦሮሚያ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ በአብዛኛው በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጣረው ጥቃት አዛውንት፣ ህጻናት እና ሴቶችን ሰለባ ማድረጉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።

መንግሥት ጥቃቱን የፈጸመው በሽብርተኝነት የተፈረጀው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እያለ ሚጠራው ታጣቂ እነደሆነ ገልጿል።

መንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት የፈረጀው እና ሸኔ በሚል የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ በበኩሉ ይህንን አስተባብሏል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ባወጣው መግለጫ፣ ታጣቂዎቹ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጽሙና የጊምቢው ጥቃትም መንግሥት አደራጅቶታል ባለው ኢ-መደበኛ ኃይል የተፈጸመ ነው ብሏል።

በጋምቤላ ክልል ታጣቂ ኃይሎች የፈጸሙት ጥቃት ተከትሎ በተለይም በጥቃቱ ተሳትፈዋል ወይም ተባብረዋል ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ቤት ለቤት በመሄድ ጭምር ግድያዎች እንደተፈጸሙ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታውቆ ነበር።

በእነዚህ ጥቃቶች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት አልሰጡም በሚል በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከፍተኛ ትችቶችን እያስተናገዱ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማክሰኞ ዕለት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ የአገሪቱ ሠራዊት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በፈጸሙት ኃይሎች ላይ "አስተማሪ የሆነ እርምጃ" እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።