ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እናት እና አራት ልጆቿን ጨምሮ 14 ሰዎች የሞቱበት የትራፊክ አደጋ በሰሜን ሸዋ
ከአዲስ አበባ በስተሰሜን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ውስጥ በደረሰ የትራፊክ አደጋ አንዲት እና አራት ልጆቿን ጨምሮ 14 ሰዎች ሞቱ።
እሁድ ሐምሌ 9/2015 ዓ.ም. ንጋት ላይ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ ወረቢ ተብላ በምትጠራ ስፍራ ነው ይህ አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ የደረሰው።
በአደጋው ወቅት የ13 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ፖሊስ ሲያስታውቅ ሦስት ሰዎች ደግሞ ቆስለው ነበር። ከሰዓት በኋላ ቢቢሲ ለማወቅ እንደቻለው ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል የአንድ ተጨማሪ ሰው ሕይወት በማለፉ የሟቾች ቁጥር ወደ 14 ከፍ ብሏል።
ለዚህ የትራፊክ አደጋ ምክንያቱ ቁልቁለት ቦታ ላይ ከባድ የጭነት መኪና በሕዝብ ማመላለሽ ሚኒባስ ላይ ስለወጣበት መሆኑን በደገም ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ባልደረባ የሆኑት ኢንስፔክተር ሽመልስ ቦሬሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኢንስፔክተሩ እንዳሉት አደጋውን ያደረሰው የጭነት ተሽከርካሪ ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር 500 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጭኖ ሲጓዝ የነበረ ተሳቢ መኪና ሲሆን፣ “ቁልቁለት ላይ ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ ሲጓዝ ነበር” ብለዋል።
ከባድ ተሸከርካሪው ቁልቁለት መንገድ ላይ ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ በኋላ፣ ሁለት መኪኖችን ገጭቶ በመጨረሻ የሕዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ መኪና ላይ ሙሉ በሙሉ ስለወጣበት በውጡ የነበሩ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል።
በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡት 14 ሰዎች መካከል መምህርት አስመሬ ጎሶማ እና አራት ልጆቿ ይገኙበታል።
መምህርቷ የ18፣ 15፣ 8 እና የ1 ዓመት ልጆቻቸውን ይዘው ከአዲስ አበባ ወደ ጎሃ ጽዮን ቤተሰብ ጥየቃ እየጓዙ የነበረ ሲሆን፣ በአደጋው የእናት እና የሁሉም ልጆቻቸው ሕይወት አልፏል።
ኢንስፔክተር ሽመልስ ቦሬሳ እንዳሉት የትራፊክ አደጋው እንደደረሰ የ13ቱ ሰዎች ሕይወት ወዲያውኑ ያለፈ ሲሆን፣ ሌሎች ሦስት ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በኩዩ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረው ነበር።
ነገር ግን ሰኞ ከሰዓት በኋላ ቢቢሲ ባገው መረጃ መሠረት አንድ የተጨማሪ ሰው ሕይወት በማለፉ በአደጋው የሞቱ ሰዎች አሃዝ 14 ደርሷል።
አደጋው የደረሰባቸው ሰዎች ሲጓዙበት የነበረው ሚኒባስ ሙሉ በሙሉ መውደሙን እና ሌሎች ሦስት ተሸከርካሪዎች ላይም ከባድ ጉዳት ማጋጠሙን ኢስፔክተር ሽመልስ ተናግረዋል።
“20 ዓመት ፖሊስ ሆኜ ሰርቻለሁ። እስካሁን በሕይወቴ እንዲህ አይነት አሰቃቂ አደጋ አይቼ አላውቅም። የሰዎችን አስክሬን ማውጣት በራሱ እጅግ ሰቅጣጭ ነበር” ብለዋል ኢንስፔክተር ሽመልስ።
በዚህም ምክንያት በሕዝብ ማመላለሻ ሚኒባሱ ውስጥ ከነበሩት መካከል በሕይወት የወጡት ሁለት ብቻ መሆናቸውን ተናግረው እነርሱም ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።
ኢንስፔክተሩ የአካባቢው መንገድ ጠመዝማዛማ እና ቁልቁለታማ ከመሆኑም በላይ ወቅቱ የዝናብ በመሆኑ አሸከርካሪዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ ማሽከርከር እንዳለባቸው መክረዋል።
በኢትዮጵያ የተሸከርካሪዎች ቁጥር ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቢሆንም በአገሪቱ በሚደርሱ የትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር ግን እጅግ ከፍተኛ ነው።