ፊሊፒንስ፤ ቻይና በውሃ ታንክ መርከቦቼን መትታለች ስትል ወቀሰች

የፊሊፒንስ የባሕር ዳርቻ ዘብ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፊሊፒንስ ባሕር ድንበር ጥበቃ ውጥረት በነገሰበት የደቡብ ቻይና ባሕር ቀጣና ቤይጂንግ መርከቦቼን በውሃ ታንክ መትታብኛለች ሲል ወቀሰ።

ፊሊፒንስ እንዳለቸው ይህ የሆነው አንድ መርከቧ ለወታደሮች የሚሆን አቅርቦት የያዙ ጀልባዎችን ጭኖ በመጓዝ ላይ ሳለ ነው።

ወታደሮቹ አወዛጋቢ በሆነው ስፓርትሊ በሚባሉት ደሴቶች ላይ መቀመጫቸውን ያደረጉ ናቸው።

ዩናይትድ ስቴትስ የቤይጂንግን “አደገኛ ደርጊት” የኮነነች ሲሆን የቻይና “ባሕር ኃይል ሚሊሻ” ላደረሰው ጥቃት ተወቃሽ ነው ብላለች።

ቻይና እስካሁን ስለጉዳዩ ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠችም።

ቤይጂንግ እና ማኒላ ስፓርትሊ ደሴቶችን ጨምሮ ጠቅላላው የደቡብ ቻይና ባሕር በይገባኛል ሲወዛገቡ ኖረዋል።

ማሌዥያ፣ ቪየትናም፣ ብሩኔይ እና ታይዋንም በዚህ ባሕር ላይ የይገባናል ጥያቄ ያነሳሉ።

የፊሊፕንስ ባሕር ዳርቻ ዘብ ባወጣው መግለጫ ክስተቱ የተፈጠረው ቅዳሜ ዕለት መሆኑን ጠቅሶ መርከቦቹ ወደ ስፓርትሊ ደሴቶች እያቀኑ እንደነበር ገልጧል።

የቻይና ተግባር “ከልክ ያለፈ እና ሕገ-ወጥ ነው” ያለው መግለጫው ቤይጂንግ ዓለም አቀፍ ሕግ ጥሳለች ሲል ወቅሷል።

የዩናይትድ ስቴት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ “ለፊሊፒኖ አጋሮቻችን” ድጋፍ እንሰጣለን ብሏል።

“የውሃ ታንክ በመተኮስ እና መርከቦች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ ቻይና በፊሊፒንስ ሕጋዊ ተግባር ጣልቃ ገብታለች። የፊሊፒንስ መርከቦችና ሠራተኞች ላይም አደጋ ጥላለች” ይላል ሚኒስቴሩ ያወጣው መግለጫ።

ዓለም አቀፉ የግልግል ችሎት ቻይና ጠቅላላው የደቡብ ቻይና ባሕር የኔ ነው ማለቷ ትክልል አይደለም የሚለውን ውሳኔ ቤይጂንግ አትቀበልም።

የደቡብ ቻይና ባሕር በጣም ውጥረት ካለባቸው የዓለማችን አካባቢዎች አንዱ ሲሆን በዚህ የባሕር ክፍል ምክንያት በተለይ በቅርብ ዓመታት በቻይናና በአሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሯል።

ይህ ባሕር በየዓመቱ 5 ትሪሊዮን ዶላር የሚሆን ንግድ የሚከናወንበት ሲሆን ቤይጂንግ በየጊዜው እያደረገችው ያለው ጫና ይህንን የንግድ ትሥሥር እንዳያላላው ተሰግቷል።