ዶናልድ ትራምፕ ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የሚለጥፉት ነገር ለከት እንዲኖረው አቃቤ ሕግ ጠየቀ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቅርቡ ችሎት የሚቀርቡት የቀድሞው የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ስለክሳቸው የሚናገሩት ነገር ለከት እንዲኖረው አቃቤ ሕግ ጠየቀ።

ፕሬዝደንቱ አንድ ዛቻ የተሞላበት ፅሑፍ ማሕበራዊ ሚድያ ላይ ከለጠፉ በኋላ ነው አቃቤ ሕግ ይህን ያለው።

አርብ ምሽት ይህን አቤቱታ ለፍርድ ቤት ያቀረበው አቃቤ ሕግ፤ ትራምፕ ስለ ክስ ሂደቱ ሚስጥራዊ መረጃ አሳልፈው ይሰጣሉ የሚል ስጋት አለው።

የቀድሞው ፕሬዝደንት አርብ ዕለት የለጠፉት መልዕክት ተከትሎ አቃቤ ሕግ ይህ ጉዳይ በክሱ የተካተቱ ሰዎችን የሚመለከት ሊሆን ይችላል ሲል ሞግቷል።

ነገር ግን የትራምፕ ጠበቃዎች መልዕክቱ የፖለቲካ ተቃናቃኞቻቸውን ዒላማ ያደረገው ነው ይላሉ።

ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማሕበራዊ ሚድያ ላይ ትራምፕ “እኔን ልታሳድዱኝ ከሞከራችሁ እኔም አሳድዳችኋለሁ” ሲሉ ለጥፈዋል።

አርብ እንዲህ ብለው የለጠፉት ትራምፕ ሐሙስ ለቀረቡባቸው አራት ክሶች ጥፋተኛ አይደለሁም ሲሉ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል አሜሪካን ለማጭበርበር ማሴር፣ ምስክሮች ላይ ጫና ማሳደር፣ እንዲሁም በዜጎች መብት ላይ ሤራ መወጠን የሚሉ ይገኙበታል።

አቃቤ ሕግ አቤቱታውን ካስገባ በኋላ በትራምፕ የቀረቡ ክሶችን ሲመሩ የቆዩት ልዩ አማካሪ ጃክ ስሚዝ፤ ትራምፕ የለጠፉት መልዕክት አሳሳቢና ሚስጥር ሊያጋልጥ የሚችል ነው ብለዋል።

ልዩ አማካሪው አክለው የቀድሞው ፕሬዝደንት ከሳቸው ተቃራኒ የሆኑ ዳኞችን፣ ጠበቃዎችና እማኞችን የማጥቃት ባሕሪ እንዳላቸው አውስተው “ይህ ባሕሪያቸው ምስክሮች ላይ ጫና የሚያሳድርና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ፍርድ እንዳይሰፍን የሚያደርግ ነው” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሪፐብሊካኖች ከወዲሁ ልዩ አማካሪው ላይ ጥቃት ማድረስ የጀመሩ ሲሆን አርብ ዕለት አላባማ ለተሰበሰቡ የፓርቲው ደጋፊዎች ስሚዝ “መጥፎ ሰው ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

አቃቤ ሕግ ባስገባው አቤቱታ ትራምፕ የለጠፉት መልዕክት “በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ” በዚህ የወንጀል ክስ ላይ ያሉ ሰዎችን የሚመለከት ነው ብሏል።

ዳኛ ታኒያ ቹትካን የትራምፕ ጠበቃዎች እስከ ሰኞ ከሰዓት 11፡00 ድረስ ምላሻቸው ይዘው እንዲመጡ አዘዋል።

የትራምፕ ጠበቃዎች ሶስት ተጨማሪ ቀናት ይሰጡን ብለው ቢጠይቁም ዳኛዋ ይህን ጥያቄ ውድቅ አድርገውታል።

አቃቤ ሕግ አቤቱታውን ካስገባ በኋላ የትራምፕ ቃል አቀባይ የቀድሞው ፕሬዝደንትን መልዕክት ክፋት የለውም ያሉ ሲሆን ፕሬዝደንቱ ዒላማ ያደረጉት የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ነው ብለዋል።

ደቡብ ካሮላይና ተገኝተው ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ያደረጉት ትራምፕ የቀረበባቸውን ክስ “እንደ ክብር ኒሻን” እንደሚመለከቱት ተናግረዋል።

ለደጋፊዎቻቸው ሲናገሩ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረጉበት ምክንያት “እኛን ስለሚፈሩ ነው” ብለው እሳቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ፅጥ ማሰኘት የክሱ ዓላማ ነው ብለዋል።

አክለው ወደ ዋይታ ሐውስ የሚመለሱ ከሆነ አሜሪካ ዳግም ነፃነቷን እንደምታገኝ ገልጠዋል።

በሰኔ 6 የአሜሪካ አመፅ የተሳተፉ ሰዎችን ክስ በመዳኘት የሚታወቁት ዳኛ ቹትካን በፈረንጆቹ ነሐሴ 28 ሁለቱንም ወገን ጠርተው የችሎቱ ቀን መች ይሁን በሚለው ጉዳይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።

አቃቤ ሕግ እንደሚለው የፍርድ ሂደቱ በፍጥነት መካሄዱ ጠቃሚ ነው።

ነገር ግን የትራምፕ ጠበቃ የሆኑት ጆን ላውሮ የቀድሞው ፕሬዝደንት የጥብቅና ቡድን ለዘግጅት ተጨማሪ ጊዜ ይፈልጋል ሲሉ ይከራከራሉ።

ትራምፕ አሁን አምስት ችሎት ይጠብቃቸዋል። ሶስቱ የወንጀል ክሶች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ የፍትሐ ብሔር ችሎት ናቸው።