ሩሲያ ባደረሰችው ጥቃት የደም ማዕከል መምታቷን ዜሌንስኪ ተናገሩ

ጥቃት ደረሰበት የተባለው ማዕከል

የፎቶው ባለመብት, TELEGRAM/VOLODYMYR ZELENSKY

በሩሲያ የተመራ የአየር ጥቃት በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን አንድ የደም ማዕከል መትቶ ሰዎች እንደሞቱና እንደተጎዱ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ተናገሩ።

ቮሎድሚር ዜሌንስኪ እንዳሉት ኩፒያንስክ በተባለችው ከተማ ከደረሰው የአየር ጥቃት በኋላ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እሣት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነው።

“ሽብርተኞችን ማሸነፍ ለሕይወት ዋጋ ለሚሰጥ ሁሉ የክብር ጉዳይ ነው” ነው ብለዋል ፕሬዝደንቱ።

ሩሲያ እስካሁን ደረሰ ስለተባለው ጥቃት የሰጠችው አስተያየት የለም።

በማሕበራዊ ሚድያ ገፅ ሐሳባቸውን ያሰፈሩት ዜሌንስኪ ጥቃት አድራሾቹን “ማንኛውም ለመኖር የሚያስችል ነገርን ለማጥፋት የተነሱ አውሬዎች ናቸው” ብለዋል።

“ይህ የጦር ወንጀል ብቻ ስለሩሲያ ወረራ ብዙ ነገር ይነግረናል” ሲሉ አክለዋል።

ፕሬዝደንቱ በጥቃቱ ምን ያክል ሰው እንደሞተ አሊያም እንደተጎዳ ያሉት ነገር የለም።

ቢቢሲ ደረሰ የተባለውን ጥቃት በራሱ እስካሁን ማጠራት አልቻለም። ሩሲያ እስካሁን የቀረቡባትን ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረጉ ናቸው የተባሉ የጦር ወንጀል ክሶች ታስተባብላለች።

ኩፕያንስክ ከተማና ዙሪያዋ ሞስኮው በፈረንጆቹ የካቲት 2022 ዩክሬንን ስትወር በሩሲያ እጅ ከወደቁ ሥፍራዎች መካከል ናቸው።

ቀጣናው ነፃ የወጣው ባለፈው መስከረም የዩክሬን ኃይል ባደረገው ፈጣን መልሶ ማጥቃት ነው።

ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ጨምረው እንደጠቀሱት ቅዳሜ ዕለት ሩሲያ በምዕራብ ኼምለኒስኪ ክልል የሚሳዔል ጥቃት አድርሳለች።

ሩሲያ፤ ዩክሬን በጥቁር ባሕር 11 ሰዎች ጭና የነበረች መርከብን መትታብኛለች ብላ ከወቀሰች በኋላ ሞስኮው አደረሰቻቸው የተባሉ ጥቃቶች የተሰሙት።

ዩክሬን በተለይ ባለፉት ቀናት በተደጋጋሚ የአየርና የባሕር ድሮን ጥቃቶች ሩሲያ ላይ ማድረሷ ተዘግቧል።

የሩሲያ የአየር ኃይል ባለሥልጣናት እንዳሉት ጥቁር ባሕር ኬርች ስትሬይት ላይ የነበረችው መርከብ ሞተር ቢመታም ማንም ሰው ጉዳት አልደረሰበትም።

ኬርች ስትሬይት ጥቁር ባሕርን ክሬሚያ ከሚገኘው አዞቭ ባሕርን የሚያገናኝ ነው። የዩክሬን ሰርጥ የሆነው ክሬሚያ በፈረንጆቹ 2014 በሩሲያ ተገንጥሎ መወሰዱ ይታወሳል።

ዩክሬን መርከቧ ላይ ስለደረሰው አደጋ ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠችም።

ነገር ግን የዩክሬን የደኅንነት ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የባሕር ድሮን ጥቅም ላይ ውሏል።