ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ስብሰባ ላይ ምን ጉዳዮች ተነሱ?
ከየካቲት ወር ጀምሮ በተለያየ ፈርጅ ከሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ሲወያዩ የከረሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ 12ተኛ ውይይታቸውን ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር አድርገዋል።
ትላንት ሰኞ መጋቢት 23/2016 ዓ.ም. በተደረገው በዚህ ስብሰባ ላይ ከአገር አቀፍ እና ክልላዊ ፓርቲዎች የተወጣጡ ከ400 በላይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መሳተፋቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
ከቅዳሜ ዕለት ጀምሮ ወደ የአፍሪካ አመራር ልኅቀት አካዳሚ የገቡት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንደ ቀደሙት የውይይት ተሳታፊዎች ሁሉ በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ የመንግሥት “ሜጋ ፕሮጀክቶችን” እሁድ ዕለት ጎብኝተዋል።
ሰኞ ጠዋት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የተደረገው ውይይት ሲጀመር ዐቢይ ለውይይቱ መነሻ ሀሳብ የሚሆን ወይም የመንግሥትን አፈጻጸም የሚያስረዳ ንግግር ሳያደርጉ ለተሳታፊዎች በቀጥታ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ዕድል ወደ መስጠት እንደሄዱ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ የማቅረብ ዕድል መስጠት ሲጀምሩ አብዛኛው የውይይቱ ተሳታፊዎች እጃቸውን እንዳወጡ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ሊቀ-መንበር አቶ አላምረው ይርዳው ለቢቢሲ ተናግረዋል። ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ለማቅረብ ዕድል ያገኙ አጠቃላይ ተሳታፊዎች ቁጥር 20 ገደማ መሆኑን አክለዋል።
የፓርቲ አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ምን ጠየቁ?
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በውይይቱ ላይ እንደተነሳ የጠቀሱት ጉዳይ በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነባ ያለው የመንገድ ኮሪደር እና ሌሎች “ሜጋ ፕሮጀክቶች” ጉዳይን ነው።
የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙሳ አደም፤ “ከፕሮጀክቶቹ ጋር ተያይዞ ዜጎች ይፈናቀላሉ” የሚል ሀሳብ እንደተነሳ አስታውሰዋል። አቶ አላምረው በበኩላቸው “በመንገድ ኮሪደር ልማት እና በመሳሰሉ የሚነሱ ዜጎች ዘርን መሠረት ያደረጉ ናቸው” በሚል ጥያቄ መቅረቡን ገልጸዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ መልስ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ “አዲስ አበባ ውስጥ የአንድ ብሔር [መኖሪያ] የሆነ ሰፈር የለም” በማለት በፕሮጀክቱ ምክንያት ሰዎች እየተነሱ ያለው ብሔርን መሠረት ባደረገ መልኩ አለመሆኑን እንደተናገሩ አቶ አላምረው ጠቅሰዋል።
በከተማዋ እየተከናወነ ያለው ፕሮጀክት አስቀድሞ “ጥናት የተደረገበት” እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስረዳታቸውን አቶ ሙሳ ገልጸዋል። “ማንም ሰው ያለቤት አይቀርም፤ አሁን ካሉበት የተሻለ ካልሆነ ከዚህ የባሰ ኑሮ አይኖራቸውም” የሚል ምላሽ መሰጠቱንም አስታውሰዋል።
መንግሥት እየገነባቸው ካሉ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ የፖለቲካ የፓርቲ አመራሮች፤ “ከግንባታዎቹ በላይ የዜጎች ሰላም እና ደኅንነት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል” የሚል ሀሳብ አንስተው እንደነበር የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ምክትል ሊቀ መንበር ዶ/ር ራሄል ባፌ ገልጸዋል። በአማራ ክልል ያለው ግጭትም ከዚሁ ጋር ተያይዞ መነሳቱንም ጠቅሰዋል።
ዐቢይ በምላሻቸው፤ “ቢያንስ የአገር ውስጥ ግጭቶችን እናስቀጥላለን ብለን ያልንበት አካሄድ የለም። በተቻለ መጠን ሰላም እንዲኖር እንፈልጋለን” ማለታቸውን ዶ/ር ራሄል አስታውሰዋል። አቶ ሙሳ በበኩላቸው “ለመነጋገር እና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ነን” የሚል ምላሽ መሰጠቱን አንስተዋል።
በውይይቱ ላይ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጉዳይ መነሳቱንም ተሳታፊዎቹ ጠቅሰዋል። እንደ ተሳታፊዎቹ ገለጻ ከምክክሩ ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ የብልጽግና ፓርቲ ምክክሩ ላይ በተለያየ መልኩ “ተፅእኖ እያሳደረ ነው” የሚል አንድምታ ያለው ነው።
አቶ አላምረው እንደሚያስረዱት፤ “በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ላይ በአብዛኛው እየተወከሉ ያሉት የብልጽግና ሰዎች ናቸው” የሚለው ቅሬታ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለዚህ በሰጡት ምላሽ ብልጽግና ፓርቲ እንደ ሌሎች ፓርቲዎቹ ሁሉ “እንደ አንድ ተሳታፊ” እንደሚታይ መናገራቸውን አቶ አላምረው ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “[በአገራዊ ምክክር] አሰራር የሚፈጠሩ ስህተቶች ካሉ አንድ ሁለት ብላችሁ አምጡ፤ እኛ ከመብታችን ውጪ ሄደን ከሆነ ከስር ጀምሮ እናርማለን። ግን ከስር ጀምሮ ያሉት ነገሮች በሕግ እና በሕግ [እየተከናወኑ ነው]። አንድም የአገራዊ ምክክሩን ሕግ የጣሰ ሥራ እንዳይሠራ በከፍተኛ ሁኔታ እየሠራን ነው” ማለታቸውን የአገው ብሄራዊ ሸንጎ ሊቀ-መንበሩ ተናግዋል።
የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ሊቀ-መንበር አቶ አላምረው በውይይቱ ላይ መነሳቱን የጠቀሱት ሌላኛው ጉዳይ የአገው እና ራያ ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች ናቸው። አቶ አላምረው፤ የአገው ሕዝብ “ከአሁን በኋላ በአማራ ክልል ውስጥ መኖር እንደማይችል” በመጥቀስ የክልልነት ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
ሌላ የስብሰባው ተሳታፊ በበኩላቸው የራያ ሕዝብን በተመለከተ “በዚህ በኩል ትግራይ የእኛ ነው ይላል፤ በዚያ በኩል አማራ የእኛ ነው ይላል፤ ለምን መፍትሔ አትሰጡንም?” በማለት ተመሳሳይነት ያለው ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል።
ዐቢይ የአገው ሕዝብን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ “የአገው ሕዝብ አቃፊ ሕዝብ ነው። ስለዚህ የተወሰኑ የፖለቲካ ኃይሎች በሚፈጽሙት ስህተት ከአማራ ጋር አልኖርም ማለት ጥሩ የፖለቲካ አስተሳሰብ አይደለም። ይህ ችግሮችን በመፍታት የሚቀረፍ ነው” ማለታቸውን አቶ አላምረው አስረድተዋል።
የራያ ሕዝብ ጥያቄን በተመለከተም መንግሥት ችግሩ እንዲፈታ የሚፈልገው “አማራም፣ ትግራይም ‘የኔ ነው’ ማለታቸውን አቁመው፤ የራያ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን” እንደሆነ ተናግረዋል ተብሏል።
ስለተነሱት ጥያቄዎች እና ስለተሰጡ ምላሾች ተሳታፊዎች ምን ያስባሉ?
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከረጅም ጊዜ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መገናኘታቸውን በጥሩነት ቢያነሱም በተለይ ከተሳታፊዎች የተነሱ ጥያቄዎች የሚያረኩ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢሶዴፓ ምክትል ሊቀ መንበር ዶ/ር ራሄል፤ የቀረበው ጥያቄ “የተደራጀ አልነበረም” ያሉ ሲሆን፣ ይህም የሆነው የውይይቱ ትኩረት ተለይቶ ባለመቅረቡ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
“በአፈጻጸም ግምገማ እና የወደፊት አቅጣጫ ላይ ‘እናውራ፣ ጥያቄ አንሱ’ ነው የተባለው። [ተሳታፊዎች] የተናጠል፣ የመሰላቸውን ነገር ያነሳሉ። አንድ ሆነን የተነሳንበት ዕድል የለም። አንድ መድረክ ላይ አልነበርንም” ብለዋል።
የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙሳም በበኩላቸው፤ ጥያቄ ለማቅረብ ዕድል ያገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች “በተቻለ መጠን አስፈላጊ ነገሮችን በደንብ ገልጸዋል” ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል። ከቀረበው ጥያቄ አንጻር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው መልስ “ይበልጥ ግልፅነት የታየበት” መሆኑንም አክለዋል።
ተመሳሳይ ሀሳብ የሚያነሱት አቶ አላምረው፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚፈትኑ ጠንካራ ጥያቄዎች” አለመነሳታቸውን አስታውሰዋል።
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ያሉ ግጭቶች ጉዳይ በይበልጥ ይነሳል ብለው ጠብቀው እንደነበር የሚናገሩት አቶ አላምረው፤ “ስለ ጦርነቱ ያነሳ ሰው የለም ማለት ይቻላል። በጣም በደምሳሳው ‘ሰላም ቢመጣ’ ያሉ ሰዎች አሉ። የአማራ ፓርቲዎችም ነበሩ ግን ግን ጠንካራ ሆነው [ጉዳዩን] ሊያነሱ አልቻሉም” ብለዋል።
አቶ አላምረው፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አንድ ሰው ረጅም ጊዜ ሲያወራ ዝም ብሎ የማዳመጥ ችሎታን አይቼባቸዋል” ሲሉም ትዝብታቸውን አጋርተዋል።