የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄንሪ ኪሲንጀር በ100 ዓመታቸው አረፉ

የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄንሪ ኪሲንጀር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውስጥ ትልቅ ሚና የተጫወቱት የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄንሪ ኪሲንጀር በ100 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።

በኒክሰን እና በፎርድ የፕሬዝዳንትነት ዘመን የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት እና የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።

እአአ በ1970ዎቹ አጋማሽ ከስልጣን ቢለቁም ለብዙ አሥርት ዓመታት መሪዎች ለምክር ሲጎበኟቸው ቆይተዋል።

በጀርመን የተወለዱት የቀድሞው ዲፕሎማት በኬንታኪ በሚገኘው ቤታቸው ህይወታቸው ማለፉ ተነግሯል።

በእሳቸው የተመሰረተው የፖሊሲ አማካሪ ተቋም የሆነው ኪስንጀር ረቡዕ ምሽት በሰጠው መግለጫ የሞታቸውን ምክንያት አልገለጸም።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ዩናይትድ ስቴትስ "በውጭ ጉዳዮች ላይ የምትተማመንበትን እና ልዩ የሆነ ሰው አጥታለች" ሲሉ ሃዘናቸውን ገልጸዋል።

የፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ሴት ልጆች ትሪሲያ ኒክሰን ኮክስ እና ጁሊ ኒክሰን አይዘንሃወር ኪሲንጀር የኖሩት ህይወት ታሪክ "በጣም ልዩ እና የአሜሪካዊነት መገለጫ ነው” ብለዋል።

"ሄንሪ ኪሲንጀር ሠላምን ለማስቀጠል ባከናወኗቸው በርካታ ስኬቶች ለረዥም ጊዜ ይታወሳሉ። እኛ ግን የማንረሳው ባህሪያቸው ነው” ሲል መግለጫው አክሏል።

በአውሮፓውያኑ1923 በጀርመን የተወለዱት እና የመምህር ልጅ የነበሩት ኪሲንጀር፤ ቤተሰቦቻቸው በ1938 ከናዚዎች ጭፍጨፋ ሲሸሹ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ ያቀኑት።

በአውሮፓውያኑ1943 የአሜሪካ ዜግነት ያገኙት ኪሲንጀር፤ ለሦስት ዓመታት በአሜሪካ ጦር እና በኋላም በፀረ ስለላ ጓድ ውስጥ አገልግለዋል።

የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ ካገኙ በኋላ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነት አግኝተዋል።

እ.ኤ.አ. በ 1969 የወቅቱ ፕሬዝዳንት ኒክሰን የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አድርገው ሾሟቸው ፣ ይህ ስፍራ በአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ላይ ትልቅ ስልጣን ሰጣቸው ።

ከ1969-77 ባሉት ስምንት ዓመታት የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። በነዚህም ዓመታት አሜሪካ በቬትናም ጦርነት ያላትን ተሳትፎ ያቆመችበት፤ ከቻይና ጋር ግንኙነቷን የጀመረችበት ወቅት ነው። በተጨማሪ በአውሮፓውያኑ 1973 ግብጽ እና ሶርያ በአንድ በኩል ሆነው ከእስራኤል ያደረጉት የመካከለኛው ምስራቅ የዮም ኪፑር ጦርነት እንዲቆም አድርገዋል።

ኪሲንጀር ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ዡ ኤንላይ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኪሲንጀር ተወዳጅነትና ዝናን ባተረፉባት ቻይና የሞታቸው ዜና ዌቦ በተሰኘው የአገሪቱ ማህበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ በስፋት ተነግሯል።

የቻይና መገናኛ ብዙሃን “የቻይና ሕዝብ የረዠም ጊዜ ወዳጅ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

የቻይና ማዕከላዊ ቴሌቪዥን ጣብያ በአሜሪካ-ቻይና ግንኙነት ውስጥ ትልቅ ሚና የነበራቸው “ታዋቂ ዲፕሎማት” እና “ህያው” ሲል ጠርቷቸዋል።

ባለፉት ዓመታት ኪሲንጀር ከሶቪየት ኅብረት ጋር በሰብዓዊ መብቶች ላይ ፉክክር በመግባት እና የቺሊውን አውጉስቶ ፒኖቼን ጨምሮ አፋኝ አገዛዞችን ይደግፋሉ በሚል ከፍተኛ ትችቶችን አስተናግደዋል።

ኪሲንጀር ግን ይህን ትችት ውድቅ ያደርጉታል።

"ይህ የአለመረዳታቸው ነጸብራቅ ነው" ሲሉ ጠጠር ባለ ድምጸ በቅርቡ ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

እአአ በ 1973 የኖቤል የሠላም ሽልማትን ከሰሜን ቬትናሙ ሌ ዱክ ቶ ጋር ቢሸለሙም ሊ ሽልማቱን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም።

ሽልማቱ ሁለት የኖቤል ኮሚቴ አባላት ሥራቸውን እንዲለቁ ምክንያት ሆኗል።

የኪሲንጀር የመካከለኛው ምስራቅ የሠላም ጥረቶች 'የሸትል ዲፕሎማሲ' በመባል ይታወቅ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኪሲንጀር በ1977 የመንግስትን ኃላፊነታቸውን ቢለቁም በህዝብ ጉዳዮች ትንታኔ በመስጠት ቀጥለዋል።

የእሳቸውን ምክር ለማግኘት ከጆን ኤፍ ኬኔዲ እስከ ጆ ባይደን ያሉ በደርዘን የሚቆጠሩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች እና የሕግ ይጎበኟቸው ነበር።

ኪሲንጀር ከማኦ ዜዱንግ እስከ ዢ ጂንፒንግ ያሉትን ሁሉንም የቻይና መሪ ያነጋገሩ ብቸኛው አሜሪካዊ ናቸው።

የተለያዩ ኩባንያዎች የቦርድ አባል በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በውጭ ፖሊሲና የደኅንነት መድረኮች ከመገኘት ባለፈ 21 መጻሕፍትን አሳትመዋል።

100ኛ ዓመታቸውን ካከበሩም በኋላ ኪሲንጀር ንቁ ተሳትፏቸው ቀጥሏል። የቻይና እና አሜሪካ ግንኙነት ቀዝቀዝ ባለበት ወቅት እንኳን አዛውንቱ በሐምሌ ወር ወደ ቤጂንግ ባደረጉት ድንገተኛ ጉብኝት ከፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ተገናኝተው ነበር።

ጉብኝቱ ዋይት ሃውስን ያስቆጣ ሲሆን የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ የአሜሪካ መንግስት ያላገኘውን “አንድ ዜጋ" ከቻይና መሪዎች ጋር መገናኘቱ ያሳዝናል ሲሉ በቁጭት ገለጸዋል።

እአአ በ2022 ከኤቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እድሉ ቢኖራቸው ኪሲንጀር የትኛውን ውሳኔያቸውን እንደሚቀይሩ ተጠይቀው ነበር።

"በህይወቴ ሙሉ ስለእነዚህ ችግሮች እያሰብኩ ነበር። የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዬም ሆነ ስራዬ ነው። እናም እኔ ያቀረብኳቸው ምክሮች ምርጥ ነበሩ" ብለዋል።

ኪሲንጀር 50 ዓመታት የሚጠጋ ህይወታቸውን ከባለቤታቸው ናንሲ ኪሲንገር ጋር አሳልፈዋል።

ኤልዛቤት እና ዴቪድ የሚባሉ ልጆችን ከቀድሞ ጋብቻቸው ያፈሩ ሲሆን አምስት የልጅ ልጆችን ለማየት በቅተዋል።