ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቻይናዋ ግዛት ጥንዶች ያለገደብ ልጆች እንዲወልዱ ፈቀደች
በቻይናዋ ሴቹዋን ግዛት የሚኖሩ ጥንዶች ያለገደብ ልጆች እንዲወልዱ ተፈቀደላቸው። ይህ የተሰማው አገሪቷ እየቀነሰ ያለውን የሕዝብ ብዛት ቁጥር ለማስተካከል እየሞከረች ባለችበት ወቅት ነው።
የቻይና የሕዝብ ብዛት በ60 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀነሱ ባለፈው ሳምንት የአገሪቱ መንግሥት አሳውቆ ነበር።
ለአስርት ዓመታት አገሪቷ አንድ ቤተሰብ የአንድ ልጅ ብቻ እንዲኖረው የሚያስገድድ ፖሊሲ የነበራት ሲሆን፣ አሁን ግን እንደ አውሮፓውያኑ 2021 ጀምሮ ጥንዶች እስከ ሦስት ልጅ እንዲወልዱ ፈቅዳለች።
አሁን ሴቹዋን ግዛት ባደረገችው የፖሊሲ ለውጥ ያላገቡ ግለሰቦችም ልጆች ወልደው ማሳደግ እንዲችሉ ተፈቅዷል።
ቀደም ብሎ ያላገቡ ሴቶች ልጆቻቸውን ማስመዝገብ አይችሉም ነበር።
ቻይና በ1979 የተዋወቀውንና አነጋጋሪ የሆነውን የአንድ ልጅ [ዋን ቻይልድ] ፖሊሲዋን ያነሳችው እንደ አውሮፓውያኑ 2016 ነበር።
ይህንን ሕግ የጣሱ ወላጆች ቅጣት ይጣልባቸው ነበር። አንዳንድ ጊዜም ሥራቸውን ያጡ ነበር።
በባህልም ወላጆች ከሴቶች ይልቅ ለወንድ ልጅ እንዲኖራቸው ስለሚፈልጉ፣ የአንድ ልጅ ፖሊሲው አስገዳጅ ጽንስ ማቋረጥ እንዲኖር ምክንያት ሆኗል።
ይሁን እንጂ በ2016 የተደረገው ለውጥ እየቀነሰ የመጣውን የውልደት መጠን አላቆመውም። ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የሞት መጠን ከውልደት መጠን በልጧል።
አሁን ላይ 80 ሚሊየን ሕዝብ በሚኖርባት እና በአገሪቷ በደቡብ ምዕራብ በምትገኘው ሴቹዋን ግዛት ነዋሪዎች ያለምንም ገደብ የፈለጉትን ያህል ልጅ መውለድ እንዲችሉ ተፈቅዶላቸዋል።
የቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ መንግሥት የውልደት መጠንን መጨመር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ገልጾ ነበር።
መንግሥታቸው እያሽቆለቆለ ያለውን የውልደት መጠን ለመቀልበስ የግብር እፎይታ እና የተሻለ የእናቶች ጤና እንክብካቤ እየሰጠ ነው።
የሴቹዋን የፖሊሲ ለውጥ የተሰማው ቻይና ከኮቪድ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ሞቶች እየታገለች ባለበት ወቅት ነው። አገሪቷ ታኅሣሥ ወር ላይ ዜሮ ኮቪድ ፖሊሲዋን ካነሳች በኋላ ወረርሽኙ በመላ አገሪቷ ተዛምቷል።
ይህ የሕዝብ መጠን መቀነስ ጉዳይ የቻይና ብቻ ሳይሆን ጃፓንን ጨምሮ ሌሎች ጎረቤት አገሮችም ያጋጠማቸው ችግር ነው።
የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በአገሪቷ ያለው የወሊድ መጠን መቀነስ አገሪቱን አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደጣለው በቅርቡ ተናግረዋል።
በዚህም ሳቢያ አገሪቱ እንቅስቃሴ የምታቆምበት አፋፍ ላይ እንደሆነችም አስጠንቅቀዋል።
ከ125 ሚሊዮን የጃፓን ዜጎች መካከል በዓመት ከ800,000 በላይ የወሊድ መጠን እንዳለ ተገልጿል።
ይህ አሃዝ እአአ በ1970ዎቹ ቁጥሩ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ነበር ተብሏል።