አዲስ የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር በፍጥነት እየቀነሰ መሆኑን ተመራማሪዎች አስታወቁ

የውልደት መጠን አስገራሚ በሆነ ፍጥነት እየቀነሰ መሆኑን ተመራማሪዎች አስታወቁ።

ይህ የውልደት መጠን በፍጥነት እየቀነሰ መምጣቱ ከ80 ዓመታት በኋላ የበርካታ አገራት የህዝብ ቁጥራቸው በግማሽ እንዲቀንስ ያደርጋል ተብሏል።

በጎርጎሳውያኑ 2100 የስፔን እና የጃፓን የህዝብ ቁጥርን ጨምሮ የ23 አገራት ጠቅላላ ህዝብ ቁጥር በግማሽ ይቀንሳል። ይህም ብቻ ሳይሆን መሰል አገራት በእድሜ የገፉ አዛውንቶችን በብዛት ይኖራቸዋል ይላል ተመራማሪዎች ይፋ ያደረጉት ጥናት።

እየሆነ ያለው ምንድነው?

የውልደት መጠን መቀነስ- ማለት አንዲት ሴት በህይወት ዘመኗ በአማካይ የምትወልዳቸው የልጆች መጠን ማለት ነው።

በጎርጎሳውያኑ 1950 ላይ አንዲት ሴት በአማካይ 4.7 ልጆች ይኖራት ነበር። ይህ አሃዝ እአአ 2017 ላይ ግን 2.4 የደረሰ ሲሆን፤ እአአ 2100 ላይ ግን አሃዙ ወደ 1.7 ይወርዳል ተብሎ ተገምቷል።

በዚህ መሠረት ተመራማሪዎች አጠቃላይ የዓለማችን ህዝብ ቁጥር 2064 ላይ 9.7 ቢሊዮን እንደሚጠጋ የገመቱ ሲሆን 2100 መጀመሪያ ላይ ግን ቁጥሩ ወደ 8.8 ቢሊዮን ዝቅ ይላል።

ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ክርስቶፈር መሪ "ይህ ተፈጥሯዊ የህዝብ ቁጥር መቀነስ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የውልደት መጠን ለምን እየቀነሰ መጣ?

የውልደት መጠን ለመቀነሱ እንደምክንያት ከሚጠቀሱ ገዳዮች መካከል አንዱ በርካታ ሴቶች በትምህርት እና በሥራ መጠመዳቸው መሆኑን ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።

ከዚህ በተጨማሪ የወሊድ መቆጣጠሪ አማራጮች በስፋት መኖራቸው ሴቶች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ልጆች የመውለድ ፍላጎት እንዲኖራቸው ማድረጉን ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።

የህዝብ ቁጥራቸው የሚቀንሰው የትኞቹ አገራት ናቸው?

አሁን ላይ 128 ሚሊዮን ገደማ ህዝብ ያላት ጃፓን ከ80 ዓመታት በኋላ የህዝብ ቁጥሯ በ53 ሚሊዮን ሊቀንስ እንደሚችል ተገምቷል። የ1.4 ቢሊዮን ህዝብ መኖሪያ የሆነችው ቻይናም ከ80 ዓመታት በኋላ የህዝብ ቁጥሯ በግማሽ ቀንሶ 732 ሚሊዮን ዜጎች ብቻ ይኖራታል ተብሎ ተገምቷል።

ጣሊያንም በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ የህዝብ ቁጥሯ ከ61 ሚሊዮን ወደ 28 ሚሊዮን እንደሚወርድ ተጠብቋል። ከእነዚህ ሶስት አገራት በተጨማሪ የህዝብ ቁጥራቸው ይቀንሳል ተብሎ የተገመቱት አገራት 23 ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ታይላንድ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ደቡብ ኮሪያ ተጠቃሽ ናቸው።

ይህ ለሰው ልጆች ችግር ይሆን?

አነስተኛ የሆነ የህዝብ ቁጥር ወደ ከባቢያዊ አየር የሚለቀው የካርቦን መጠን አነስተኛ ነው። ለእርሻ ተብሎ የሚመነጠረው የእርሻ መሬትም እንደሚቀንስ እሙን ነው። ይህ ግን እንደምናስበው የሰው ልጆች መቀነስ ለምድራችን ጤና የሚበጅ ላይሆን ይችላል።

ፕሮፌሰር መሪ እንደሚሉት በቀጣዮቹ አስርተ ዓመታት የውልደት መጠን በመቀነሱ አጠቃላይ የዓለም ህዝብ ቁጥር ይቀንሳል ሲባል ከግምት መግባት የሚኖርበት፤ ከወጣቶች ይልቅ እድሜ የገፉ ሰዎች በምድር ላይ መኖራቸውን ነው ይላሉ።

ይህ ጥናት ያስቀመጠው ትንበያ፡

  • እአአ 2017 ላይ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ከ681 ሚሊዮን በ2100 ወደ 401 ሚሊዮን ዝቅ ይላል
  • እአአ 2017 ላእ እድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ የሆኑ አዛውንቶች ከ141 ሚሊዮን በ2100 ወደ 866 ሚሊዮን ከፍ ይላል

ፕሮፌሰር መሪ ይህ ከፍተኛ የሆነ የማህበራዊ ህይወት ላይ ለውጥ እንደሚያስከትል ስጋታቸውን ገልጸዋል። "እድሜው በገፋ ማህብረሰብ ውስጥ ማን ሰርቶ ግብር ይከፍላል? ለአዛውንቶች የጤና አገልግሎ ማን ሊከፍል ነው? አዛውንቶችን ማን ሊንከባከብ ነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

ለዚህ መፍትሄ ይኖር ይሆን?

እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ አገራት በውልደት መጠን የሚቀንሰውን የህዝብ ቁጥር ከፍ ለማድረግ የሌሎች አገራት ስደተኞችን እየተቀበሉ ይገኛሉ። ይህ ግን ወደፊት በርካታ አገራት የህዝብ ቁጥር በተመሳሳይ ሁኔታ ስለሚቀንስ ዘላቂ መፍትሄ የመሆኑ ነገሩ ላይ ጥያቄ አስነስቷል።

ፕሮፌሰር መሪ እንደሚሉት ከሆነ አንዳንድ አገራት ዜጎች ልጆች እንዲወልዱ ለማበረታታት ለእናት እና አባት ተጨማሪ የወሊድ ፍቃዶችን መስጠትን ጨምሮ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን እየሰጡ ቢገኙም የእነዚህ እርምጃዎች ውጤት የሚታወቅ አሁን ላይ አይደለም።

የአፍሪካስ እጣ ፈንታ ምን ይሆን?

ከተቀሩት አህጉራት በተለየ መልኩ አፍሪካ የህዝብ ቁጥር እንደሚጨምር ተገምቷል።

ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት የህዝብ ቁጥር 2100 በሶስት እጥፍ እንደሚጨምር ተገምቷል።

ከ80 ዓመታት በኋላ ናይጄሪያ 791 ሚሊዮን ህዝብ በመያዝ በርካታ ሰዎች የሚኖሩባት ሁለተኛዋ አገር ትሆናለች።