በመፈንቅለ መንግሥት እና በምርጫ ናይጄሪያ የመሩት ሙሐመዱ ቡሃሪ

የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዝደንት ሙሐመዱ ቡሃሪ እሁድ ዕለት ሕክምናቸውን በሚከታተሉበት ለንደን ሕይወታቸው ማለፉን የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ተናገሩ።

የፕሬዚደንት ቦላ ቲኒዩ ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ "ፕሬዝደንት ቡሃሪ ለረጅም ጊዜ ባደረባቸው ሕመም በለንደን ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል" ብለዋል።

የቡሃሪን አስከሬን ለቀብር ወደ ናይጄሪያ አጅቦ ለማምጣት ምክትል ፕሬዝደንቱ ካሺም ሸቲማ እና የጽህፈት ቤታቸው ኃላፊ ወደ ለንደን እንዲሄዱ ትዕዛዝ መሰጠቱን ተናግረዋል።

ሙስሊም የሆኑት ቡሃሪ በትውልድ አገራቸው በሰሜን ምዕራብ ካትቲና በሙስሊሞች ሥርዓት መሠረት ይቀበራሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ገለፀዋል።

የ82 ዓመቱ ቡሃሪ በ1980ዎቹ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ ዳግም በምርጫ ተፎካክረው የአገሪቱን ርዕሰ ብሔርነት የተረከቡ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት ናቸው።

ቡሃሪ በነበራቸው ፀረ ሙስና አቋም በርካታ ተከታዮችን አፍርተው ነበር።

ራሳቸውን "የተለወጠ ዲሞክራት" ብለው መጥራት የሚወዱት ቡሃሪ የወታደር ልብሳቸውን በማውለቅ የናይጄርያን የባህል ልብስ እና ቆብ መልበስ አዘወተሩ።

ቡሃሪ "እኔ የሁሉም ነኝ፤ የማንም አይደለሁም" ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው እና ተቺዎቻቸው ደጋግመው ይናገሩ ነበር።

ቡሃሪ እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 ዛሬ ድረስ የናይጄሪያ የመጀመሪያው ፍትሃዊ ፉክክር ተብሎ በሚሞካሸው ምርጫ ጉድላክ ጆናታንን አሸንፈዋል።

በርካቶች ጡረተኛው ሜጀር ጄነራል ልክ ወታደራዊ አዛዥ ሳሉ እንዳደረጉት ታጣቂ ኃይሎችን ከአገሪቱ ያስወግዳሉ ብለው ተስፋ አድርገው ነበር።

ከዚያ ይልቅ በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ ብቻ ተወስኖ የነበረው አለመረጋጋት ተስፋፋ።

በሰሜን ምዕራብ የሚገኙ ታጣቂዎች፣ የታጠቁ ተገንጣዮች እና በደቡብ ምሥራቅ ያሉ ወንበዴዎች የሰሜን ናይጄሪያን ከፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ውጪ አደረጉት።

ቡሃሪ ወታደራዊ እንዲሁም የሲቪል አዛዥ ሆነው በአብዛኛው ሙስናን መከላከል የአጀንዳቸው ማጠንጠኛ ነበር።

በናይጄሪያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ስር የሰደደ ሙስና ሰዎችን ወደ ኋላ እየጎተተ ነው ብለው ያምኑ ነበር።

በ82 ዓመታቸው በለንደን በሕክምና ላይ ሳሉ ያረፉት የናይጄሪያው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙሐማዱ ቡሃሪ፣ የቀድሞ ወታደራዊ ጄነራል፣ ራሳቸውን የተለወጠ ዲሞክራት አድርገው በምርጫ ወደ ሥልጣን ቢመለሱም ለናይጄርያውያን የገቡትን ቃል እንደሚያሳኩ ለማሳመን በብርቱ ታግለዋል።

ቡሃሪ እአአ በ2015 ሥልጣን ከያዙ በኋላ ግን በርካቶችን ማስደሰት አልቻሉም።

ሥልጣን የተረከቡት የናይጄሪያ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን ቦኮ ሃራም ወደ 300 የሚጠጉ ሴት ተማሪዎችን ከሰሜን ምሥራቅ ቺቦክ ከተማ አፍኖ ከወሰደ በኋላ ነበር።

ቡሃሪ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ካቢኔያቸውን ለመሰየም ስድስት ወራት ፈጅተዋል።

በዚያን ጊዜ በነዳጅ ላይ የተመሠረተው የናይጄርያ ምጣኔ ሃብት በዝቅተኛ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ የተነሳ ተንኮታኩቶ ስለነበር ሰዎች "ቀሰስተኛው" (Baba Go Slow) የሚል ቅጽል ስም አሰትቷቸዋል።

በድሆች፣ በተለይም በብዛት በሰሜናዊ ናይጄሪያ በሚገኙ ሙስሊሞች ዘንድ ዝነኛ የሆኑት ቡሃሪ እአአ በ2019 ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ተመርጠዋል።

ምንም እንኳን በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው በናይጄሪያ ታይቶ አይታወቅም የተባለ የኢኮኖሚ ውድቀት ቢከሰትም፣ታጣቂዎች የነዳጅ ማውጫዎችን ቢያጠቁም፣ ይፋ ባልሆነ ሕመም ሳቢያ በተደጋጋሚ ሆስፒታል ቢገቡም ዳግም መመረጥ ችለው ነበር።

የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ቡሃሪ እአአ በ1980ዎቹ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ያልተሳካላቸውን አካሄድ ተግባራዊ አድርገዋል።

የናይጄሪያን መገበያያ ገንዘብን 'ለብሔራዊ ኩራት' በሚል በሰው ሠራሽ መንገድ ከፍተኛ ዋጋ ሰጥቶ ማቆየት መርጠው ነበር።

ፕሬዝደንቱ ልክ እንደ መጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው፣ አይኤምኤፍን የናይራ ዋጋ እንዲቀንስ የሰጠውን ምክር ችላ ብለዋል።

እአአ በ2022 በናይጀር ዴልታ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ላይ ስርቆት በማጋጠሙ የተነሳ በአገሪቱ ሁለት አስርት ዓመታት ታሪክ ውስጥ ዝቅተኛ ነው የተባለ ምርት ወደ ውጪ ልትልክ ችላለች።

የፀረ ሙስና እርምጃቸውም ከፍተኛ ሙሰኞችን ወደ ሕግ ለማምጣት አልቻለም የሚል ጠንከር ያለ ትችት ይቀርብበታል።

የመብት ተሟጋች ቡድኖች ቡሃሪ የአምባገነንነት ዝንባሌያቸውን ፈጽሞ አልለቀቁም ሲሉ ይነቅፏቸዋል።

በ2020 የፖሊስን ጭካኔ የተቃወሙ ያልታጠቁ ሠልፈኞች በፀጥታ ኃይሎች በጥይት ተገደለዋል።

ያንን ተከትሎም በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተቃውሞ ሠልፎች እና አለመረጋጋቶች ተከስተዋል።

ይህም በ1999 ወታደራዊ አገዛዝ ካበቃ በኋላ በጣም የተስፋፋ ሕዝባዊ አመፅ ሆኖ ተመዝግቧል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በታኅሣሥ 17/1942 በካትሲና ግዛት ዳውራ የተወለዱት ቡሃሪ በ19 ዓመታቸው ወደ ውትድርና ገብተዋል።

በአገሪቱ መከላከያ ውስጥም እስከ ሜጀር ጄነራልነት ድረስ አገልግለዋል።

እአአ በ1983 የተዛባውን የአገሪቱን አስተዳደር ለማደስ ቃል በመግባት በወታደራዊ መሪነት የአገሪቱን ሥልጣን ተቆጣጠሩ።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ካስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ አንስቶ በሁሉም የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃዎችን ወሰዱ።

እአአ በ1984 አስተዳደራቸው በብሪታንያ ይኖሩ የነበሩትን የቀድሞ ሚኒስትር እና ቀንደኛ ተቺያቸውን ለማገት ሞክሯል።

የለንደን አየር ማረፊያ ባለሥልጣናት የተጠለፉትን ፖለቲከኛ የያዘውን ሳጥን ሲከፍቱ ሴራው ከሽፏል።

የመጀመሪያው የሥልጣን ቆይታቸው አጭር ነበር። ከ18 ወራት በኋላ በሌላ ወታደራዊ መሪ ኢብራሂም ባባንጊዳ ከሥልጣን ተነስተዋል።

ከዚያ በኋላ ለ30 ዓመታት ያህል እምብዛም ተጽዕኖ ባልነበራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በመሳተፍ ለፕሬዝደንትነት ሲወዳደሩ የቆዩት ቡሃሪ በ2015 ጉድላክ ጆናታንን አሸንፈው የአገሪቱን ርዕሰ ብሔርነት ተቆጣጥረዋል።

ቡሃሪ በ2015 ከማሸነፋቸው በፊት ሦስት ጊዜ ለፕሬዝደንትነት ተወዳድረው ነበር።

ቡሃሪ በማኅበራዊ ደኅንነት ፕሮግራሞች፣የባቡር መስመሮች ግንባታ፣መንገዶች፣ ግድቦች፣አየር ማረፊያዎች እና የኃይል መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት የናይጄሪያውያንን ሕይወት ለማሻሻል እንደሚያልሙ ይናገሩ ነበር።

የመሠረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች የናይጄሪያ ምጣኔ ሃብት መሠረት ናቸው ሲሉ ይናገሩ ነበር።

የቀድሞ ወታደራዊ መሪ ራሳቸውን ዳግም እንደ ተወለደ ዲሞክራት አድርገው ለማቅረብ ቢሞክሩም ጤንነታቸውን በሚመለከት ግን ግልጽ ለመሆን ቁርጠኛ አልነበሩም።

ናይጄሪያውያን በተደጋጋሚ ሆስፒታል ስለሚተኙት ርዕሰ ብሔራቸው በቂ መረጃ ሳያገኙ፣ ለትልቁ ኃላፊነት ብቁ መሆናቸውን ደጋግመው እንደጠየቁ ዓመታትን አሳልፈዋል።

ሙሐመዱ ቡሃሪ ሁለት ጊዜ ያገቡ ሲሆን፣ ከመጀመሪያ ባለቤታቸው ሳፊናቱ ዩሱፍ (1971-1988) በመቀጠልም በ1989 ካገቧት ከአይሻ ሃሊሉ 10 ልጆችን አፍርተዋል።