ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደብረጽዮን የሚመራው ህወሓት የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮችን በ "ብሔራዊ ክህደት" ከሰሰ
በህወሓት ሊቀ መንበር የሚመራው የደብረጽዮን ገብረሚካኤል ቡድን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ወገን ያሉትን አመራሮች "ብሔራዊ ክህደት" መፈጸምን ጨምሮ በተለያዩ ጥፋቶች የሚከስ መግለጫ አወጣ።
በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ማብቃት ተከትሎ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከተመሠረተ በኋላ በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው አለመግባባት ተባብሶ በሁለት ወገን በመሆን ሲካሰሱ እና ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ መቆየታቸው ይታወቃል።
በተለይ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ የተካሄደው እና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም በከፍተኛ የህወሓት አመራር ዕውቅናን ካላገኘው የድርጅቱ ጉባኤ በኋላ ውዝግቡ ተባብሶ ቀጥሏል።
ሁለቱ ወገኖች በክልሉ እና በመካከላቸው ያሉ ችግሮችን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ውይይት አድርገው ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ እንደሚሠሩ ተነግሮ ነበር።
ነገር ግን ረቡዕ ታኅሣሥ 2/2017 ዓ. ም. በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው የህወሓት ወገን ባወጣው መግለጫ ላይ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ባሉት ወገኖች ላይ ብርቱ ክሶችን ሰንዝሯል።
በህወሓት ሊቀ መንበር የሚመራው ቡድን አቶ ጌታቸው እና አብረዋቸው ያሉት የድርጅቱ አመራሮች ከፓርቲው የተባረሩ በመሆናቸው በህወሓት ስም የያዙትን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊነቶችን እንዲለቁ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ የነበረ ሲሆን ጉዳዩንም ለፌደራል መንግሥቱ አቅርበው ነበር።
በረቡዕ ዕለቱ መግለጫ ላይም የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትን ለመተካት የቀረበው ሐሳብ "በሁለት ሳምንት ውስጥ ይታያል የሚል ሐሳብ ከፌደራል መንግሥት መቅረቡን ተከትሎ በሂደት ላይ ያለ ጉዳይ ነው" ብሏል።
ይሁን እንጂ ለውይይቱ ቅርብ የሆኑ ምንጭ ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ምርጫ ተካሂዶ መደበኛ አስተዳደር እስኪመሠረት ድረስ ያለው ጊዘያዊ አስተዳደር እንደሚቀጥል ማሳወቃቸውን ገልጸው ነበር።
በህወሓት በኩል የወጣው መግለጫ ከዚህ በፊት ሲያቀርብ ከነበረው ክስ ጠንከር ባለ ሁኔታ በአቶ ጌታቸው ወገን ያሉትን አመራሮች "ከህወሓት ተነጥሎ የወጣ" በማለት የሕዝቡን ጥቅም አሳልፎ ሰጥቷል ሲል በክህደት ከሷል።
"ብሔራዊ ክህደት እየፈጸመ ያለው ቡድን የትግራይ ብሔራዊ ጥቅምን አሳልፎ ለኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረባቸው ጥያቄዎች ላይ የህወሓትን ስም አጉድፏል" ይላል መግለጫው።
ከዚህ ጋር ተያይዞም "ከህወሓት ተነጥሎ የወጣ" የሚለው ቡድን፣ ለፌደራል መንግሥቱ ያቀረባቸው ሐሳቦች "የትግራይ ሠራዊትን ስም የሚያጠለሽ፣ የቀድሞ ተዋጊዎች ትጥቅ የማስፈታትና የተሃድሶ ሂደት (ዲዲአር) እንዲፋጠን በማድረግ የትግራይ የፀጥታ ኃይል ትጥቅ እንዲፈታ እያደረገ ነው" ሲልም ወቅሷል።
በተጨማሪም "የትግራይ ሠራዊት ወደ ኢትዮጰያ ሠራዊት እንዲቀላቀል ሐሳብ ማቅረቡና ዲዲአር እስኪፈጸም ሠራዊቱ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥር እንዲሆን መጠየቁን" በማንሳት ክህደት ካላቸው ጉዳዮች መካከል አካቷል።
ሌላው በመግለጫው የተነሳው ሕገ ወጥ የማዕድን ማውጣት ተግባር በክልሉ ውስጥ ይካሄዳል የሚለው ጉዳይ ነው።
ለዚህም በሰሜን ምዕራብ የትግራይ ዞን ውስጥ ያለው የማዕድን ቁፋሮ ሥራዎች "ከቁጥጥር ውጪ እንደሆነ በማስመሰል፣ በትግራይ በኩል ከኤርትራ ጋር ግንኙነት እንዳይፈጠር ለመከልከል በሚል ሰበብ የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ ትግራይ እንዲገባ ጥያቄ አቅርቧል" ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ ክስ ሰንዝሯል።
የክልሉ ጊዘያዊ አስተዳደር እና ተባርረዋል ከመባላቸው በፊት የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ እና ሌሎችም ከእሳቸው ጋር ያሉት አመራሮች "ልክ እንደ ኢህአዴግ ህወሓትን ከውስጥ ለማፍረስ ሲሠራ ቆይቷል" በማለት ፓርቲውን ለማዳከም እየሠሩ ነው ብሏል።
እንዲሁም በህወሓት ስም የወጣው ይህ መግለጫ፣ ለውጥ ማምጣት በሚል ስም "የትግራይን ሕዝብ እና ሠራዊትን በመበተን፣ የወረዳ ምክር ቤቶችን በማፍረስ" በክልሉ "የቀለም አብዮት" ለማነሳሳት እየሠሩ ነው ብሏል ።
መግለጫው ጠንካራ የሚባሉ ክሶችን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ባሉ አባሎች ላይ ካቀረበ በኋላ፣ በማጠቃለያው ላይ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ችግሩን "በአጭር ጊዜ መልክ ለማስያዝ የሚያስችል ዕቅድ አውጠቶ በመወሰን ወደ ትግል ገብቷል" ብሏል።
ነገር ግን ውሳኔው እና የሚወሰደው እርምጃ ምን እንደሆነ ያለው ነገር የለም።
በተለያዩ መልኮች የክህደት ድርጊት ፈጽሟል በሚል ብርቱ ክሶች የቀረቡበት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የሚገኘው የህወሓት ወገን እስከ ሐሙስ ታኅሣሥ 3/2017 ዓ. ም. አመሻሽ ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።