የቀድሞው የሠላም ሚኒስትር ዲዔታ የአቶ ታዬ ደንደአ ያለመከሰስ መብት ተነሳ

የቀድሞው የሠላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲዔታ እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል፣ አቶ ታዬ ደንደኣ ያለመከሰስ መብታቸው ተነሳ።

አቶ ታዬ አባል የሆኑበት፣ የኦሮሚያ ምክር ቤት (ጨፌ) ያለመከሰስ መብታቸውን ያነሳው ዛሬ ሰኞ፣ የካቲት 11/2016 ዓ.ም. እያካሄደ ባለው መደበኛ ጉባዔ ላይ ነው።

የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዲዔታው፤ ከሁለት ወር በፊት ታኅሣሥ 2/2016 ዓ.ም ነበር ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ከሽብር ድርጊት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለጸው፡፡

የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አባል እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት እንደራሴ የሆኑት አቶ ታዬ፤ በግል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው እና በመገናኛ ብዙኃን ላይ መንግሥትን ይተቹ ነበር።

አቶ ታዬ፤ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው ከቀናት በፊት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንዲሁም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የፌደራል መንግሥቱ ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ያደረገው ድርድር መክሸፍን አስመልክተው ትችት ሰንዝረው ነበር።

በኦሮሚያ ክልል ስላለው ግጭት እና በአዲስ አበባ ሊካሄድ ታቅዶ በተከለከለው ሠላማዊ ሰልፍ ዙሪያ መንግሥት ላይ ያላቸውን ወቀሳ በጠንካራ ቃላት ገልጸው ነበር።

የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዲዔታ ከዚህ ትችታቸው በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተፈረመ ደብዳቤ ከሥልጣናቸው ተነስተዋል።

አቶ ታዬ ይህ ደብዳቤ በደረሳቸው ምሽት በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና ቤታቸው ላይ ብርበራ መካሄዱን ባለቤታቸው በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የአቶ ታዬን በቁጥጥር ስር መዋል በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ በሽብር ቡድንነት ከተፈረጀው መንግሥት ሸኔ እያለ ከሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር “መንግሥትን በአመጽ፣ በሽብር እና በትጥቅ ለመጣል” ሲያሴሩ እንደተደረሰባቸው ጠቅሷል።

ቢቢሲ የአቶ ታዬን ባለቤት እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ኮሚሽንን ጠይቆ መረዳት እንደቻለው አቶ ታዬ በቁጥጥር ከዋሉ ጊዜ ጀምሮ ፍርድ ቤት አልቀረቡም።

አቶ ታዬ ደንደአ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት መንግሥትን በመተቸት ይታወቁ የነበረ ሲሆን፣ ተፈርዶባቸው ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ ቆይተዋል።

በአገሪቱ የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ከእስር የወጡት አቶ ታዬ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመሪነት መንበሩን ከያዙ በኋላ ከቅርብ ደጋፊዎቻቸው መካከል በመሆን ወደ መንግሥት ሥልጣን መምጣታቸው ይታወቃል።

አቶ ታዬ ኢህአዴግን የተካው ብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የኦሮሚያ ምክር ቤት አባል ከመሆናቸው በተጨማሪ በፓርቲው፣ በኦሮሚያ ክልል እና በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ሠርተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለሦስት መስመር የምስጋና ደብዳቤ ምክንያቱ ባልተገለጸ ሁኔታ ከኃላፊነታቸው አስከተነሱበት ታኅሣሥ 1/2016 ዓ.ም. ድረስም አቶ ታዬ ከሁለት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲዔታ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።