አዲሱ የኬንያ ፕሬዝደንት መሠረታዊ ድጎማዎችን አነሱ

በምርጫ ቅስቀሳቸው የመደበኛ ኬንያዊያንን ህይወት አሻሽላለሁ፣ የስራ ዕድል ፈጥራለሁ እና የኑሮ ውድነትን እቀንሳለሁ በማለት ቃል የቡት ዊልያም ሩቶ፣ የነዳጅ ድጎማን ማንሳታቸው በርካታ ኬንያውያንን እያነጋገረ ነው።

በመላው ዓለም በተለያዩ ምክንያቶች እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ዜጎች እንዲቋቋሙ በማሰብ መንግሥታት ድጎማዎችን እያስተዋወቁ ባሉበት በዚህ ወቅት አዲሱ የኬንያ መሪ ግን ቀዳሚ ባደረጉት የፖሊሲ ማስተካከያ የነዳጅ ድጎማን አንስተዋል።

በዚህ ኬንያውያንን ባስገረመ ውሳኔ የነዳጅ ዋጋ በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛው የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ እንዲደርስ የሚያደርግ ነው።

በርካቶች በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ቅሬታቸውን እየገለጹ ሲሆን የኢኮኖሚ ተንታኞች በበኩላቸው ምርጫውን እጅግ ጠባብ በሆነ ልዩነት ያሸነፉት ዊልያም ሩቶ ገና በስልጣን ዘመናቸው መጀመሪያ ላይ ድጋፍ ሊያሳጣቸው የሚችል ውሳኔ ነው ያሳለፉት ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የናይሮቢ ነዋሪ የሆኑት ጆን ማና "ከወራት በፊት ወደ ስራ ለመሄድ መኪና መንዳት አቁሜያለሁ። አሁን ደግሞ ማታቱዎች (የሕዝብ ታክሲዎች እና አውቶብሶች) የታሪፍ ጭማሪ አድርገው ይህንንም ጉዞ የበለጠ ውድ ይሆንብኛል ብዬ እየሰጋሁ እገኛለሁ’’ ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፕሬዚደንት ሩቶ በምርጫ ቅስቀሳቸው የመደበኛ ኬንያውያንን ህይወት አሻሽላለሁ፣ የስራ ዕድል ፈጥራለሁ እና የኑሮ ውድነትን እቀንሳለሁ በሚል ቃል የገቡ ሲሆን ለዚህም ራሳቸው ከዝቅተኛ ኑሮ ተነስተው አሁን ያሉበት ደረጃ መድረሳቸውን በማጉላት አስተጋብተዋል።

በምርጫ ዘመቻው ከገቡት ቃል ውስጥ አንዱ የነዳጅ ዋጋን ለመቀነስ፣ በነዳጅ ላይ የሚጣለውን ግብር ማንሳት እና ይህንንም ተከትሎ የመሰረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ ዝቅ ማድረግ ነበር።

ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር የድጎማ ፕሮግራሙ ማብቃቱን አስታውቀው ድጎማው ቢቀጥል እስከ መጪው ሰኔ ወር ድረስ ኬንያ 2.3 ቢሊየን ዶላር ታወጣ እንደነበር ተናግረዋል።

"ይህ ከጠቅላላው የአገሪቱ የመንግሥት የልማት በጀት ጋር ሲነጻጸር እኩል ነው" ያሉት ፕሬዘዳንቱ ድጎማው የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የታለመለትን ዓላማ ማሳካት አልቻለም ብለዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ድጎማ ለኬንያ ዘላቂነት የሌለው መፍትሄ ብሎም ለአጭበርባሪዎች ዕድል ከመስጠት ባሻገር ለመደበኛው ዜጋ ያን ያህል ፋይዳ እንደሌለው ይናገራሉ።

ነገር ግን የነዳጅ ዋጋ በ13 በመቶ ጨምሮ 1.49 ዶላር ወይም 78 ብር መግባቱ ጫና መፍጠሩ አይቀሬ ነው ሲሉ ይስማማሉ።

"ተፅዕኖው በእርግጠኝነት መሰማቱ አይቀርም። ምክንያቱም የሁሉም ነገር ዋጋ ከነዳጅ ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ መጨመሩ ስለማይቀር’’ ሲሉ ተንታኙ ኸርማን ማንዮራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እንዲህ ያለ ትልቅ ውሳኔ ገና አዲስ መንግሥት ሳይቋቋም በፊት መደረጉ አላስፈላጊ ብሎም “ከታሰበበት የመንግሥት ውሳኔ ይልቅ የአንድ ሰው ውሳኔ እንዲመስል አድርጓል’’ ሲሉም ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ የካቢኔ አባላቶቻቸውን አዋቅረው ብሎም የፓርላማውን ይሁንታ የሚሹ የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውን አላሾሙም።

ተንታኙ ጃቫስ ቢጋምቦ በበኩላቸው ፕሬዘዳንቱ ጉዳዩን በቅድሚያ ለኬንያውያን ማስረዳት ብሎም የድጎማውን ገንዘብ በምን ላይ ሊያውሉት እንዳሰቡ ለማስረዳት ተጨማሪ ጊዜ ወስደው እርምጃውን ህዝባዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረግ ነበረባቸው ብለዋል።

ፕሬዘዳንት ሩቶ የኬንያውያን የዕለት ተዕለት ተቀዳሚ ምግቦችን ለማዘጋጀት ጥቅም ላይ የሚውለውን የበቆሎ ዱቄትዋጋ በግማሽ የቀነሰውን ድጎማ ግዜው ማብቃቱን ተከትሎ ለተጨማሪ ግዜ አላራዝምም ብለዋል።

ኬንያ በከፍተኛ እዳ ውስጥ የምትገኝ አገር ስትሆን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ጋር ባላት የብድር ውል መሠረት ድጎማውን ማንሳቷ አስፈላጊ ተብሎ የተቀመጠ ነበር።

"እነዚህ ድጎማዎች ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች ይልቅ ከፍተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች የበለጠ የማገዝ አዝማሚያ አላቸው" ሲሉ የአይኤምኤፍ የአፍሪካ ዳይሬክተር አበበ ሥላሴ ተናግረዋል።

ፕሬዚደንት ሩቶ በናፍጣ እና ኬሮሲን ላይ አነስተኛ ድጎማ አድርገዋል። ናፍጣ በአብዛኛው የሕብ ትራስፖርት አግልግሎት ሰጪዎች እና ፋብሪካዎች ጥቅም ላይ ይውላል። እንዲሄም ኬሮሲን በተለይም የገጠር ቤተሰቦች ምግብ ለማብሰል እና በምሽት ብርሃን ለማግኘት የሚጠቀሙበት ነው።

በነዳጅ እና በቆሎ ዱቄት ላይ የሚደረገው ድጎማ ተቀንሶ በምትኩ የማዳበሪያ ወጪን ለመቀነስ መታሰቡም ይፋ ሆኗል።

በኬንያ የማዳበሪያ ዋጋ፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት ከከፈተች በኋላ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

ኬንያ ራሷን ለመመገብ የሚያስችል በቂ በቆሎ ስለማታመርት በአገር ውስጥ ምርት ፍላጎትን ማሟለት ካስፈለጋት አገራዊ ምርትን ማሳደግ ይጠበቅባታል።

በኬንያ አርሶ አደር ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ ያላቸው አዲሱ ፕሬዘዳንት ሩቶ "የኑሮ ውድነት ዝቅ የማድረግ ስትራቴጂያችን አምራቾችን በማብቃት ላይ የተመሰረተ ነው" ብለዋል።

በመሆኑም አዲሱ አስተዳደር ከመጪው ሰኞ ጀምሮ 1.4 ሚሊዮን ባለ 50 ኪሎ ግራም ማዳበሪያ የያዙ ከረጢቶችን አሁን ከሚሸጥበት 54 ዶላር ወደ 29 ዶላር ዝቅ ለማድረግ ማሰባቸውን ፕሬዝደንቱ ይፋ አድርገዋል።

ፕሬዝደንቱ የወሰዷቸው እነዚህ ውሳኔዎች በሚቀጥሉት ወራት የኑሮ ውድነቱን ጋብ ካላደረጉት የሩቶ ተቀባይነት ላይ ትልቅ ጫና ሊያመጣ እንደሚችል ተንታኙ ቢጋምቦ አስጠንቅቀዋል።

"በሚቀጥሉት ስድስት እና ስምንት ወራት ውስጥ የሚደረጉት ውሳኔዎች የኑሮ ውድነቱን ካልቀነሱት የዜጎች ደስታ ብዙም አይቆይም" ሲሉ ተናግረዋል።