ኢላን መስክ ብራዚል ውስጥ ተዘግቶ የነበረውን ኤክስ 5 ሚሊዮን ዶላር ከፍሎ አስከፈተ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የብራዚል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ ላይ ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ ማንሳቱን አስታውቋል።
ዳኛ ኤክሳንደር ዴ ሞራየስ ውሳኔያቸውን ሲያነቡ ማኅበራዊ ሚድያው ላይ የተጣለው ዕግድ የተነሳው ቅጣቱን ስለከፈለ እና የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጩ ገፆችን ስለዘጋ ነው ብለዋል።
በመግለጫው መሠረት የኢላን መስክ ንብረት የሆነው ኤክስ 5.1 ሚሊዮን ዶላር ከፍሏል። ኩባንያው በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ብራዚል ውስጥ ተወካይ ለመቅጠርም ተስማምቷል።
ዳኛው የኢላን መስክ ማኅበራዊ ሚድያ ብራዚል ውስጥ እንዲታገድ ወስነው የነበረው መንግሥት የተሳሳተ መረጃ ያሰራጫሉ ያላቸውን ገፆች ባለመዝጋቱ ነው። በተለይ አንዳንድ ገፆች በ2022 የነበረውን የብራዚል ምርጫ ለማደናቀፍ የተሳሳተ መረጃ አሰራጭተዋል ተብለው ይጠረጠራሉ።
የብራዚል ኔትዎርክ አቅራቢ ድርጅቶች ተቆጣጣሪ የሆነው አናቴል በሚቀጥሉት 24 ሰዓታት ውስጥ ኤክስን ለተጠቃሚዎች ክፍት እንዲያደርግ ተነግሮታል።
የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ ብራዚል ውስጥ 24 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይነገራል።
ኢላን መስክ ለወራት ከፍርድ ቤት የተሰጠውን ትዕዛዝ አልቀበልም ሲል ቆይቷል። መስክ ብራዚል የሚገኙ የኤክስ ሠራተኞችን አባሮ በሀገሪቱ የሚገኘውን ቢሮ መዝጋቱ ይታወሳል።
“ብራዚል የሚገኘውን ቢሯችንን መዝጋት ቀላል አልነበረም” ሲል ቢሊየነሩ በወቅቱ ተናግሮ ነበር።
ከኤክስ በተጨማሪ ቴስላ የተሰኘ የኤሌክትሪክ መኪና ማምረቻ እና ስፔኤክስ የተባለ የሕዋ ምርምር ተቋም ያለው መስክ ዳኛው በወቅቱ የሰጡትን ውሳኔ ክፉኛ ተቃውሞ ነበር።
“የንግግር ነፃነር አርማ ነኝ” የሚለው መስክ ዳኛው የተሰጣቸውን ሥልጣን ያለአግባብ እየተጠቀሙ ነው በማለት ማኅበራዊ ሚድያው መዘጋቱ እንዳበሳጨው ግልጿል።
ኤክስ ብራዚል ውስጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል መታገዱን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ሌሎች አማራጮችን ሲጠቀሙ ተስተውለዋል። አንደኛው አማራጭ የነበረው ብሉስካይ የተባለው ማኅበራዊ ሚድያ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ‘ቪፒኤን’ በመጠቀም ኤክስን ሲጎበኙ ቆይተዋል።
ነገር ግን ባለፈው መስከረም ማኅበራዊ ሚድያው ከፍርድ ቤት የተሰጠውን ትዕዛዝ ለማክበር ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል።
ማክሰኞ ዕለት ኤክስ የተባለው ማኅበራዊ ሚድያ ሙሉ በሙሉ ወደ ብራዚል መመለሱ ይፋ ሆኗል።
የቀድሞው ትዊተር ብራዚል ውስጥ ከ20 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን ይህም ላቲን አሜሪካ ውስጥ ቁጥር አንድ ሀገር ያደርጋታል።












