ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከበርካታ ሕጻናት ሞት በኋላ በ4 የሕንድ ምርት በሆኑ ሽሮፖች ላይ ማስጠንቀቂያ ወጣ
በርካታ ቁጥር ያላቸው ሕጻናት ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ የሕንድ ምርት በሆኑ አራት የሽሮፕ አይነቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ።
የዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ ማስጠንቀቂያውን ያወጣው በአፍሪካዊቷ ጋምቢያ የ66 ሕጸናት ሕልፈት ከሽሮፖቹ ጋር ሳይገናኝ አይቀርም ከተባለ በኋላ ነው።
ሽሮፖቹ ለከፍተኛ የኩላሊት ጉዳት እና ለ66 የሕጻናት ሞት ምክንያት ሳይሆኑ አይቀርም ብሏል የዓለም ጤና ድርጅት።
የዓለም ጤና ድርጅት ወላጆች ለልጆቻቸው ከመስጠት መቆጠብ አለባቸው ያላቸው ሽሮፖች ፕሮመታዚን ኦራል ሶሉሽን (Promethazine Oral Solution)፣ ኮፌክስማሊን ቤቢ ካፍ ሲረፕ (Kofexmalin Baby Cough Syrup)፣ ማኮፍ ቤቢ ካፍ ሲረፕ (Makoff Baby Cough Syrup) እና ማግሪፕ ኤን ኮልድ ሲረፕ (Magrip N Cold Syrup) የሚባሉት ናቸው።
እነዚህ የሕጻናት ሽሮፖችን ያመረተው ማይደን ፋርማሱቲካልስ የሚባል የሕንድ ኩባንያ ሲሆን፤ ለሽሮፖቹ የደኅንነት ማስረጃ ማቅረብ አለመቻሉን የዓለም ጤና ድርጅት ጨምሮ አስታውቋል።
አምራቹ ኩባንያ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያለው ነገር የለም። ቢቢሲም ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
የሕንድ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ሽሮፖቹ ለሕጻናቱ ሞት ምክንያት መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲሰጣቸው የዓለም ጤና ድርጅትን መጠየቃቸው ተገልጿል።
ሽሮፖቹን መጠቀም በተለይ በሕጻናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ወይም ሞትን ሊያስከትል እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ሽሮፖቹ የጤና ጉዳት እንደሚያስከትሉ ማወቅ የቻለው የጎብኚዎች መዳረሻ በሆነችው በጋምቢያ በተለይ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ከፍተኛ የኩላሊት ጉዳት የሚያጋጥማቸው ሕጻናት ቁጥር መጨምሩን ተከትሎ ነው።
ይህን ተከትሎ የአገሪቱ መንግሥት ዜጎች ፓራሲታሞል ሽሮፖችን መጠቀም በማቆም በምትኩ የሚዋጥ ኪኒኒ እንዲጠቀሙ አሳስቧል።
የጋምቢያ ጤና ኃላፊዎች ባለፈው ወር ትክክለኛውን ቁጥር ሳይጠቅሱ በርካታ ሕጻናት ሕይወታቸው አልፏል ብለው ነበር።
የዓለም ጤና ድርጅት በሽሮፖቹ ላይ በተደገረ ምርመራ ዳይታይለን ግላይኮል እና ኢታይለን ግላይኮል የተሰኙ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ንጥረ ነገሮች ተገኝተዋል።
እነዚህ ንጥረ ነገሮች መርዛማ ሲሆኑ የሆድ ሕመም፣ ትውከት፣ ተቅማጥ፣ ራስ ምታት እና ለሞት የሚዳርግ ከፍተኛ የኩላሊት ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ረቡዕ መስከረም 25/2015 ዓ.ም. በጄኔቭ ንግግር ሲያደርጉ፤ “የእነዚህ ጨቅላ ሕጻናት ሕልፈት ለወላጆቻቸው ልብ የሚሰብር ነው” ብለዋል።
የሕንድ ማዕከላዊ የመድኃኒት ጥራት ተቆጣጣሪ ድርጅት ሽሮፖቹ ለጋምቢያ ብቻ መላካቸውን ለዓለም ጤና ድርጅት መግለጹን ኤአፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ምንም እንኳ እነዚህ አራት የሕጻናት ሽሮፕ አይነቶች የተሰራጩት በጋምቢያ ብቻ ነው ቢባልም መደበኛ ባልሆነ የገበያ ስንሰለት ወደ ተቀሩት ጎረቤት አገራትም ሳይሰራጩ አይቀርም ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የዓለም ጤና ድርጅት አምራቹ ሽሮፖቹ ውስጥ የተገኙትን መርዛማ ኬሚካሎች በሌሎች ምርቶቹ ላይ በመጠቀም ሕንድ ውስጥ እና ወደተቀረው ዓለም ልኮ ሊይሆን ይችላል ብሏል።