የአል ሻባብ መስራች እና ከፍተኛ አዛዥ መገደሉን የሶማሊያ መንግሥት አስታወቀ

የአልሻባብ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአል ሻባብ መስራች እና ከፍተኛ አዛዥ አብዱላሂ ናዲር ቅዳሜ መስከረም 21/2015 ዓ.ም. መገደሉን የሶማሊያ መንግሥት አስታወቀ።

ከታጣቂው ቡድን መሥራቾች አንዱ የሆነውና ዋነኛ አዛዥ እንደሆነ የሚነገረው ይህ ግለሰብ የተገደለው በደቡባዊቷ መካከለኛ ጁባ ክልል ውስጥ መሆኑም ተገልጿል።

አብዱላሂ ናዲር የአልሻባብ የሃይማኖት እሳቤዎችን የሚያሰርጸው ክፍል ኃላፊ እንደነበርም የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ገልጿል።

በተጨማሪም አሜሪካ ግለሰቡን ለያዘ ወይም ለገደለ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ሽልማትም ለመስጠትም ቃል ገብታ ነበር።

አብዱላሂ ናዲር የቡድኑን መሪ አህመድ ኦማር ዲሪዬን (አቡ ኡበይዳህን) ሊተካ የሚችል ሰው እንደሆነ በአልሻባብ ይቆጠር ነበር ብሏል።

ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት አለው የሚባለው የሶማሊያው ታጣቂ ቡድን የአልሻባብ መሪ አህመድ ለረዥም ጊዜ የጤና ችግር ላይ ነው ሲባል ቆይቷል።

የቡድኑ መስራችና ዋነኛ አዛዥ አብዱላሂ ቅዳሜ ዕለት የተገደለው በሰው አልባ አውሮፕኖች (ድሮን) ጥቃት ነው ሲል አንድ የሶማሊያ የግል ሚዲያ ዘግቧል።

የሶማሊያ የጸጥታ ኃይሎች ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመሆን በወሰዱት የጥምር ዘመቻ አብዱላሂ መገደሉን የማስታወቂያ ሚኒስቴሩ ቢገልጽም ደረሰ ስለተባለው የሰው አልባ ጥቃት ምንም ያለው ነገር የለም።

በአልሻባብ ከፍተኛ አመራሮች፣ ታጣቂዎች እና ይዞታዎች ላይ በተደገጋሚ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት የሚፈፅመው የአሜሪካ ሠራዊት የአፍሪካ ኮማንድ ስለ ግድያው የሰጠው መግለጫ የለም።