ሪፓብሊካኖች ጆ ባይደንን ከስልጣን ለማውረድ ምርመራ እንደሚከፍቱባቸው አስታወቁ

ተቃዋሚዎቹ የሪፓብሊካን ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ከስልጣን ለማውረድ ይፋዊ ምርመራ እንደሚከፍቱባቸው አስታወቁ።

ሪፓብሊካኑ የምክር ቤት አባል ኬቪን ማካርቲ ፕሬዝዳንቱ ላይ የሚከፈተው ምርመራ “ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም እና ሙስና” ላይ መሠረት ያደረገ ይሆናል ብለዋል።

ሪፓብሊካኖች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫውን ወንበር ከያዙ በኋላ በፕሬዝዳንት ባይደን ላይ ምርመራ ከፍተዋል።

እስካሁን ድረስ ምርመራው ፕሬዝዳንቱ ላይ ይህ ነው የሚባል ማስረጃ ማግኘት ባይችልም የፕሬዝዳንቱ ልጅ የንግድ እንቅስቃሴ ግን ባይደንን ሊያስጠይቃቸው ይችላል።

ሪፓብሊካኖች የጆ ባይደን ልጅ ሃንተር ባይደን ለንግድ ሥራው መቀላጠፍ የአባቱን ሥልጣን መከታ ማድረጉን እና ሙስና መፈጸሙን ባይደን ያውቁ ነበር ይህም ያስጠይቃቸዋል ይላሉ።

ማካርቲ የፕሬዝዳንቱን ተግባር በተመለከተ “ተዓማኒ እና ከባድ” የሆኑ ጥሰቶች አሉ ብለዋል በካፒቶል ሂል በሰጡት መግለጫ።

ዋይት ሃውስ ግን የሪፓብሊካኖችን ምርመራ ለማጣጣል ግዜ አልወሰደበትም። የዋይት ሃውስ ቃል አቀባ አያን ሳምስ ሪፓብሊካኖች ፕሬዝዳንት ባይደንን ለዘጠኝ ወራት ሲመረምሩ ቢቆዩም አንድም ጥፋት ሊያገኙባቸው አልቻሉም ብለዋል።

ቃል አቀባዩ የሪፓብሊካኖችን እንቅስቃሴ “ጽንፈ የያዘ የከፋ ፖለቲካ” ሲሉ ገልጸውታል።

በአሁኑ ወቅት የባይደን ልጅ ሃንተር ባይደን በውጭ አገራት የንግድ ሥራዎቹ ከግብር ማጭበርበር ጋር በተያያዙ ወንጀሎች በፖሊስ ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል።

ሪፓብሊካኖቹ ሃንተር የፕሬዝዳንቱ ልጅ በመሆኑ መርማሪዎች ጉዳዩን በተለይ ሁኔታ ይዘውለታል ይላሉ።

ዋይት ሃውስ ግን በሃንተር የወንጀል ምርመራ ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት አልፈጸምኩም ያለ ሲሆን ፕሬዝዳንቱም በሃንተር የውጭ አገራት የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ምንም አይነት ተሳትፎ የላቸውም ብሏል።

በአሜሪካ ሕገ-መንግሥት መሠረት በስልጣን ላይ ያለ ፕሬዝዳንት “በአገር ክህደት፣ ጉቦ በመቀበል ወይም በሌሎች ከፍተኛ ወንጀሎች እና ያልተገቡ ባህሪዎች” ከስልጣናቸው ማስነሳት የሚያስችል ምርመራ ሊከፍትባቸው ይችላል ይላል።

ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ባይደንን ከስልጣን ለማስነሳት የሚደረገው ጥረት ውጤታማ የመሆኑ አጋጣሚ እጅጉን ያነሰ ነው።

ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን የማስነሳት ክሱ እንዲቀጥል ቀድሞ መሆን ያለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ድጋፍ እንዲሰጡት ነው።

በምክር ቤቱ 222 ለ 212 በሆነ ልዩነት አብዛኛውን ወንበር የያዙት ሪፓብሊካኖች ሲሆኑ የምርመራ ሂደቱ እንዲቀጥል ድምጽ ቢሰጡ ጉዳዩ ወደ ሴኔቱ ያመራል።

በሴኔቱ ደግሞ የባይደን ፓርቲ አባላት የሆኑት ዴሞክራቶች አብላጫውን ወንበር ይዘው ስለሚገኙ ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን ለማስነሳት የሚደረገውን ሂደት ውድቅ ያደርጉታል ተብሎ ይጠበቃል።