ለሌላ ሰው 'አለርጂ' የሚሆኑ ሰዎች እንዳሉ ያውቃሉ? መፍትሄው ምንድን ነው?

ሰዎች ለተለያዩ ምግቦች አለርጂ መሆናቸውን በስፋት ሲናገሩ ይሰማል። እነዚህ ሰዎች የማይስማማቸውን ምግብ ከተመገቡ የሰውነት መቆጣትን ጨምሮ መታመም ይገጥማቸዋል።

ከዚህ ባሻገር አንዳንድ ሰዎች ከሰዎች ጋር በሚኖራቸው ንክኪ ምክንያት የሚቀሰቀስ አልርጂ እንዳለባቸው ያውቃሉ?

በዚህም የተነሳ አንዳንድ ሰዎች ለሌሎች አለርጂዎች ናቸው። በተለይ ይህ ሁኔታ በወንድና ሴት ተጓዳኞች መካከል ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው።

አንድ ሰው ለሌላ ሰው አለርጂ መሆንን በተመለከተ አስካሁን በስፋት የሚነገር ነገር ስለሌለ ለብዙዎች እንግዳ ጉዳይ ነው።

ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ለሚለው ጥያቄ እንቆቅልሹ ገና ለመፈታት በሂደት ላይ ነው የሚለው ትክክለኛ መልስ ነው።

ማሳሰቢያ፡ ይህ ዘገባ ግልጽ ወሲባዊ ቋንቋዎችን እና አገላለጾችን ይዟል።

ማውራ ሕይወቴን ያዳነው ኮንዶም ነው ትላለች።

የ43 ዓመቷ ማውራ የምትኖረው በአሜሪካ ኦሃዮ ግዛት ነው።

ማውራ ችግሩ የጀመረው በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ እያለች ነው። ከዚያ ቀስ እያለ እያደገ መጣ። "የወሲብ ግንኙነት ከፈጸምኩ በኋላ [ያለ ኮንዶም] ብልቴ ሲያቃጥለኝ አስተዋልኩ" ስትል ተናግራለች።

ማውራ፣ ለደኅንነቷ ሲባል ስሟ የተቀየረ፣ ይህንን ለወዳጅዋ መናገር አልደፈረችም።

እናም እስኪሄድ ድረስ ጠብቃ በደንብ ታጠበች።

የምትጠቀምባቸውን የንጽህና መጠበቂያዎች፣ ከሳሙና እስከ ማለስለሻ ድረስ ቀየረች።

ነገር ግን ችግሩ ከመዳን ይልቅ እየተባባሰ መጣ። ይህ ደግሞ የሚሆነው የወንዱ ዘር ፈሳሽ ሲነካት ነው።

በመጨረሻ ከዚያ ወዳጇ ጋር ተለያየች። ቀጥሎ ያዘችው ጓደኛ ኮንዶም ለመጠቀም የማያመነታ ነበር።

ማውራ "አንድ ምሽት ከወሲብ በኋላ አልጋ ላይ ተኝተን ምላሴ በድንገት ማበጥ ጀመረ" ትላለች።

"ወዳጄ የሆነውን ነገር አይቶ ጮኸ፤ 'አየር እያጠረሽ ነው' ብሎ መተንፈሻ መሳሪያ (ኢንሄለር) ወደ አፌ አስጠጋው። በግድ ገፍቶ ካስገባው በኋላ አየር ይሰጠኝ ጀመር። እንደ ዕድል ሆኖ፣ መድኃኒቱን ወደ ሳምባዬ ለመሳብ በቂ እስትንፋስ ነበረኝ።"

ማውራ የአስም እንዲሁም የበርካታ አለርጂዎች ታማሚ ናት። ያኔም ኮንዶም ተቀድዶ የወንዱ ዘር ፈስሶ ሊሆን እንደሚችል ታምናለች።

አሁን እርሷ እና ለረዥም ጊዜ ወዳጅዋ ሆኖ የዘለቀው ግለሰብ በኮንዶም አጠቃቀም ላይ የበለጠ ጥንቁቅ ናቸው።

በእሷ ላይ እስኪደርስ ድረስ የወንድ የዘር ፈሳሽ አለርጂ መኖሩን አታውቅም ነበር።

ምንም እንኳን በጣም አልፎ አልፎ ቢሆንም፣ አንዳንድ ሰዎች የሌሎች ሰዎች አካል ሲነካቸው አለርጂ ያዳብራሉ።

ይህ ደግሞ ጤናን ብቻ ሳይሆን ሥራን፣ ግንኙነትን እንዲሁም አንድ ሰው ከቦታ ቦታ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ያውካል።

ይህ እንዴት ሊከሰት ይችላል? በስፋት እነዚህን አለርጂዎች የሚያስከትሉ ነገሮች አሁንም ምሥጢር ናቸው።

ግን እውነት አለርጂ ናቸው ወይስ ሌላ ሕመም?

ተመራማሪዎች የሰውነታችንን የመከላከል ሥርዓት እንዲሁም ኬሚስትሪ ሲፈትሹ ምላሽ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን አግኝተዋል።

ቆዳ

የአንዳንድ ሰዎች ቆዳ ለቅባቶች እና ለሽቶዎች ቶሎ ምላሽ ይሰጣል።

እንደ ዲዮዶራንት እና አፍተርሼቭ ያሉ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው። ከ15 በላይ ሽታ ያላቸው ቅባቶች ከአለርጂ ጋር ዝምድና አላቸው።

በእርግጥ አለርጂውን የሚቀሰቅሰው ነገር ሁሌም ግልጽ አይደለም።

በኦስትሪያ የሚገኘው የኬፕለር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ዶክተር የሆኑት ሳቢን አልትሪችተር እንደተናገሩት ቀጥተኛ ግንኙነቱ ባይረጋገጥም የመከላከል አቅማችን ላይ ቁልፍ ሚና ያላቸው ህዋሳት ላይ ችግር ያለባቸው አንዳንድ ታካሚዎች ከሌሎች ሰዎች ቆዳ የሚለቀቁ ተፈጥሯዊ የሰውነት ሽታዎች ወይም ኬሚካሎች ስሱ እንደሆኑ ይጠራጠራሉ።

ቆዳ ለሰውነት ሽታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ብዙ ውህዶችን ያመነጫል።

እነዚህ የቆዳ ጋዞች እንደ ቶሉይን ያሉ ኬሚካሎችን ሊያካትቱ ይችላሉ።

ቶሉይን (Toluene) በድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ቀለሞችን እና ፕላስቲኮችን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት ያገለግላል።

ሰዎች ቶሉይንን ሆን ብለው ወደ ሰውነታቸው ይስባሉ። ይህም ራሳቸውን ሆን ብለው ለማደንዘዝ ወይንም በሥራ ቦታ ባለማወቅ ማስቲሽ ሲስቡ እንደማለት ነው።

ቶሉይን በትምባሆ ጭስ ውስጥ ከሚገኙ በርካታ ኬሚካሎች ውስጥ አንዱ ነው።

ለሌሎች ሰዎች የሚኖረንን ምላሽ ላይ ጥቂት መረጃ የሚሰጠን ፒፕል አለርጂክ ቱ ሚ (ፒኤቲኤም) የሚባለው ምሥጢራዊ ሁኔታ ነው።

ፒኤቲኤም ያልተለመደ እና አግላይ ሲሆን ሰዎች እንደ ማሳል፣ መታፈን ያሉ አለርጂ መሳይ ምልክት እንዲያዳብሩ ያደርጋል።

እአአ በ2023 በጃፓን ቶካይ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዮሺካ ሴኪን እና ባልደረቦቻቸው የፒኤቲኤም ምልክቶችን በሚያሳዩ ሰዎች የሚወጣውን የቆዳ ጋዞች መርምረዋል።

ቡድኑ ካጠናቸው 75 የቆዳ ጋዞች ውስጥ በተለይ ቶሉይን የመገኘት ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ፒኤቲኤም ያለባቸው ሰዎች ይህንን ኬሚካል በአማካይ ምልክቱ ከሌለባቸው በ39 እጥፍ ለቅቀዋል።

"ቶሉይን በምንተነፍስበት ጊዜ በአየር ውስጥ ወደ ውስጥ ይገባል። እንደ ጎጂ ውህድ፣ በተለምዶ በጉበት በኩል አልፎ በሽንት ይወጣል" ሲል ሴኪን ያስረዳሉ።

"ነገር ግን የፒኤቲኤም ታካሚዎች ቶሎይንን የማሟሟት አቅማቸው ቀንሷል። ይህም በደማቸው ውስጥ እንዲከማች እና በኋላም በቆዳ በኩል እንዲለቀቅ ያደርጋል" ብለዋል።

የሰውነት ፈሳሾች

አለርጂ የሆንባቸው ነገሮች በሌላ ሰውነት ውስጥ በሚገኙ ፈሳሾች በኩል በመግባት ሊቀሰቀሱብን ይችላሉ።

የለውዝ አለርጂ ያለበት ሰው ምንም እንኳ ለውዝ ባይመገብም፣ ለውዝ ከበላ ሰው ጋር በሚሳሳምበት ወቅት ሊቀሰቀስበት ይችላል።

ይህ ግለሰቡ ጥርሱን፣ ምላሱን እና ጥፍሩን በሚገባ ቢያጸዳ እንኳ በሰውነቶቹ ፈሳሾች በኩል ንጥረ ነገሮቹን የማግኘት ዕድል አለው።

የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች አለርጂ ያለባቸው ሴቶች መድኃኒቱን ከወሰዱ ሰዎች ጋር በሚፈጸሙ ግንኙነቶች አለርጂያቸው ተቀስቅሶባቸዋል።

ነገር ግን ከእነዚህ ውጫዊ አለርጂዎች ባሻገር በተወሰኑ የሰውነት ፈሳሾች ውስጥ ያሉ ፕሮቲኖችም ሊቀሰቅሱ ይችላሉ።

አንዳንድ የሕክምና ተቋማት በጉዳዩ ላይ እውቀቱ ቢኖራቸውም አሁንም ግን ከወንድ የዘር ፈሳሽ ጋር በተያያዘ ክፍተት ይታያል።

የወንድ ዘር ፈሳሽ አለርጂ ሴሚናል ፕላዝማ ሃይፐርሴንሲቲቭ ተብሎ ይጠራል።

አካል ከወንድ የዘር ፈሳሽ ጋር ከተገናኘ በኋላ ከማሳከክ እስከ መተንፈስ አለመቻል ድረስ ያሉ አለርጂዎችን ያስከትላል።

በአብዛኛው የሚያጠቃው ዕድሜያቸው በ20ዎቹ እና በ30ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ግሰለቦችን ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2024 ከአንድ መቶ ያነሱ ሕሙማን ተገኝተዋል።

አለርጂው ብዙውን ጊዜ የሚቀሰቀሰው በሴሚናል ፕላዝማ ውስጥ ባለው ፕሮቲን የተነሳ ነው።

የሲንሲናቲ ዩኒቨርሲቲ የአለርጂ ባለሙያ የሆኑት ጆናታን በርንስታይን በሽታውን በደንብ አልተረዳነውም ይላሉ። በጥልቀት ለማጥናት ደግሞ በቂ ሕሙማን ወይም ጥሩ የእንስሳት ሞዴሎች የሉም።

አለርጂው የወንዴው ዘር ባረፈበት ቦታ ብቻ ምልክቶችን በቆዳ ላይ ይተዋል። ብዙ ጊዜ ምልክቶቹ የሚገኙት በሴት ብልት አካባቢ ነው።

ምልክቶቹ ከወሲብ በኋላ ወዲያውኑ ኃይለኛ ሕመም እና ማቃጠል ናቸው።

አንዲት ታካሚ ስሜቱን ስትገልጸው "እንደ አሲድ" ነው ያለች ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ በሴት ብልት ውስጥ "በአንድ ሺህ መርፌዎች" እንደመወጋት ያህል ነው የተሰማኝ ብላለች።

ሕክምናው

ዶ / ር በርንስታይን በአንድ ወቅት ታካሚዎች ያለባቸውን አለርጂ ለመቀነስ የፍቅር ጓደኛቸውን የዘር ፈሳሽ በቆዳቸው ስር በመርፌ ለመስጠት ሞክረዋል።

ይህ ለራሳቸው የዘር ፈሳሽ አለርጂ የሆኑ ወንዶችን ለማከም ከሚጠቀሙበት ዘዴ ጋር ተመሳሳይ ነው። ይሁን እንጂ ይህ የሕክምና ዓይነት በጣም ውድ ነው።

በኋላ ዶ/ር በርንስታይን እና ቡድናቸው በተመሳሳይ መልኩ የሚሠራ ቀላል፣ ግን ሁለት ሰዓት በሚፈጅ ሕክምና አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጥ መፍትሄ አግኝተዋል።

በዚህ ሕክምና የወንድ የዘር ፈሳሽን ከሴሚኒየም ፈሳሾች ይለያሉ። ፈሳሹን ካቀጠኑት በኋላ በየ15 ደቂቃው በትንሽ በትንሹ ወደ ሕመምተኛዋ ብልት ውስጥ ያስገባሉ።

ቀስ በቀስ መጠኑን ይጨምሩታል። ይህም በሽተኛዋ የመቋቋም አቅም እንድታዳብር እና ከፍቅር አጋሯ ጋር ያለ ኮንዶም የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንድትፈጽም ይረዳታል።