የዩክሬን ምክር ቤት አንዳንድ የሩሲያ ዘፈኖችን አገደ

ከሩሲያ ጋር ወራትን ያስቆጠረ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው የዩክሬን ምክር ቤት አንዳንድ የሩሲያ ሙዚቃዎች እንዲታገዱ ወሰነ።

ሙዚቃዎቹ በመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች እንዳይከፈቱ ወስኗል።

ነገር ግን እገዳው የተጣለው በሁሉም የሩሲያ ሙዚቃዎች ላይ አይደለም።

ይህ ውሳኔ እአአ ከ1991 ወዲህ (ዩክሬን ከሶቪየት ሕብርት ወጥታ ነጻ አገር ከሆነች በኋላ) የሩሲያ ዜጎች የሆኑ ሰዎች ያወጧቸውን ሙዚቃዎችን በተመለከተ የተጣለ እገዳ ነው።

የሩሲያን ወረራ የተቃወሙ ሩሲያውያን ያለቀቋቸው ዘፈኖች ግን የዩክሬን እገዳ የማይመለከታቸው ይሆናል።

በተጨማሪም ከሩሲያ እና ቤላሩስ መጻሕፍት ወደ ዩክሬን ማስገባትም ይታገዳል።

በምሥራቅ እና በደቡብ ዩክሬን የሚኖሩ ዜጎች ከሩሲያ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው። አፍ መፍቻቸውም ሩስኪ (ሩሲያኛ) ነው።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ግን ዩክሬናውያን ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ትስስር ለመግታት ተገደዋል።

የዩክሬን ምክር ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት፣ እገዳ የተጣለባቸው ዘፈኖች በራድዩ ወይም በቴሌቭዥን አይጫወቱም።

ሙዚቃዎቹን በትምህርት ቤቶች፣ በሆቴሎች፣ በሲኒማ ቤቶች እንዲሁም መጓጓዣዎች ውስጥ ማሰማት ተከልክሏል።

ከምክር ቤቱ 450 አባሎች መካከል 303ቱ የእገዳ ውሳኔውን ደግፈዋል።

“በሙዚቃ በኩል ዩክሬን ውስጥ የሩሲያ ፕሮፓጋንዳ እንዳይስፋፋ ይከላከላል። በምትኩ የዩክሬን ብሔርተኛ ዘፈኖች ይበረታታሉ” ተብሏል።

እአአ በ1991 ዩክሬን ከሶቪየት ሕብረት ነጻ መውጣቷን ካወጀች በኋላ፣ የሩሲያ ዜግነት ያገኙ ሙዚቀኞች የለቀቋቸው ዘፈኖች ከዚህ በኋላ በዩክሬን አይደመጡም።

በወቅቱ ሕይወታቸው ሲያልፍ የዩክሬን ዜግነት የነበራቸው ሙዚቀኞች ሥራዎች በእገዳው አልተካተቱም።

ከሞቱ ዓመታት የተቆጠረ እንደ ተቻኮቭስኪ እና ሾስታኮቪች ያሉ ሩሲያውያን አቀናባሪዎች ሙዚቃዎች አልታገዱም።

ጦርነቱን የሚቃወሙ ሩሲያውያን ሙዚቀኞች፣ ጦርነቱን ከማውገዝ በተጨማሪ የዩክሬንን ራስ ገዝነት ዕውቅና መስጠት አለባቸው።

በራድዮ የሚሰራጩ የዩክሬን ሙዚቃዎች ወደ 40 በመቶ ከፍ እንዲሉና የመርሀ ግብሮች ዩክሬን ነክ አጀንዳ ይዘት በ75 በመቶ እንዲጨምርም ተወስኗል።

ከሩሲያ፣ ከቤላሩስ እና በወረራ ከተያዙ የዩክሬን አካባቢዎች የሚመጡ መጻሕፍት ታግደዋል።

ሩሲያ ውስጥ የተመረቱና ከሌሎች አገራት ወደ ዩክሬን የሚገቡ ምርቶ ላይም እገዳ ተጥሏል።

ከዚህ በኋላ መጻሕፍት የሚተረጎሙት በዩክሬን አገር በቀል ቋንቋዎች ወይም በሌሎች ይፋዊ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ቋንቋዎች ይሆናል።