የሰዎች አስክሬን 'የጅብ እራት' የሆነበት የትግራይ ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሰዎች አስክሬን በጅብ መበላቱ፣ ከተሞች ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙ፣ አረጋውያን እና ታዳጊ ሴቶች ለውትድርና መመልመላቸው በትግራይ ጦርነት ሳቢያ ከተሰሙ አሰቃቂ ታሪኮች መካከል ናቸው።
በጦርነቱ ሳቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው ይገመታል።
ከጦርነቱ በፊት ትግራይ የጎብኚዎች መዳረሻ ነበረች። ከዓለት ድንጋይ የተፈለፈሉ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ጥንታዊ መስጊዶች፣ ዕድሜ ጠገብ በግዕዝ የተጻፉ መዛግብትም የሚገኙባት ናት።
ዛሬ ላይ ግን ትግራይ የጦርነት አውድማ ሆናለች።
በአገሪቱ የኃይል ሚዛን ለማግኘት እንዲሁም ትግራይን ለመቆጣጠር፤ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና የኤርትራ ጦር በአንድ ወገን ሆነው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ውጊያ ከጀመሩ ሁለት ዓመት ሊሞላ ነው።
ትግራይ ያለ ባንክ፣ ስልክ፣ ኢንተርኔት እንዲሁም ያለ መገናኛ ብዙኃን ዕይታ ለ17 ወራት ከበባ ውስጥ ቆይታለች።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች በተለያየ ጊዜ የጦር ሜዳ የበላይነትን አግኝተዋል። ማሳያዎች እንጥቀስ።
የትግራይ ኃይሎች በአገር መከላከያ ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል ተብሎ መወንጀሉን ተከትሎ፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ኃይሎች በኅዳር 2013 ዓ. ም. የትግራይ መዲና መቀለን ይዘዋል።
የትግራይ ኃይሎች በመልሶ ማጥቃት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ከገቡ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተቃርበው ነበር።
ከሰሞኑ ደግሞ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጥምር ኃይሎች በጀመሩት ማጥቃት ቁልፍ ከተማዋ ሽረን ጨምሮ ሌሎችም የትግራይ አካባቢዎች መልሰው እየያዙ ነው።
በአሜሪካ የሚገኘው ‘ወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን’ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አሌክስ ዲ ዋል “ቢያንስ 500 ሺህ የሚሆኑ ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን ወታደሮች በጦርነቱ በቀጥታ እየተሳተፉ ነው። በትግራይ በኩል 200 ሺህ ወታደሮች አሉ” ብለዋል።
ለ50 ቀናት ካልተቋረጠ ውጊያ በኋላ በያዝነው ሳምንት በሽረ ግንባር ያሉት የትግራይ ኃይሎች ተተኳሽ በማጣታቸው የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት መከላከል እንዳልቻሉ አክለዋል።
“ለትግራይ ኃይሎች ይህ ትልቅ ክፍተት ነው። ንጹኃን ዜጎችን ለጭፍጨፋ፣ መደፈር እና ረሃብ ይዳርጋል” በማለት አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በሽረ እንዲሁም በሌሎች በያዛቸው አካባቢዎች ሰብአዊ እርዳታ እንደሚሰጥና አገልግሎቶች እንደሚመለሱም ቃል ገብቷል።
ሽረ በትግራይ ያለው ሰብአዊ ቀውስ ማሳያ ናት።
አንድ የረድዔት ሠራተኛ እንደሚሉት፤ ከጦርነት ቀጠናዎች በመሸሽ ወደ 600 ሺህ የሚጠጉ ንጹኃን ዜጎች በሽረ ከተማ እና በዙሪያው በሚገኙ አካባቢዎች ተጠልለዋል።
“ከ120 ሺህ በላይ ሰዎች ጫካ ውስጥ፣ ዛፍ ሥር እየተኙ ነበር ያሉት” ሲሉ ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የረድዔት ሠራተኛ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ኃይሎች ያደረሱትን ከፍተኛ ድብደባ ተከትሎ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የረድዔት ሠራተኞች ሽረን ጥለው ወጥተዋል።
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደገቡ ሌሎች ከተሞች ሁሉ በሽረም ጥቃት ይደርስብናል በሚል ፍርሀት በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎችም ሽረን ለቀው እየወጡ ነው።
የረድዔት ሠራተኛው “መስከረም ላይ በሽመብሊና መንደር 46 ሰዎች ታፍሰው እንደተገደሉ አራት የዐይን እማኞች ተናግረዋል። የመንደሩ ነዋሪዎች የሰዎቹን አስክሬን ያገኙት ከተገደሉ የቤት እንስሳት አስክሬን ጋር ተቀላቅሎ ነው” ብለዋል።
“የተወሰኑትን ሰዎች አስክሬን ጅቦች በልተውታል። ሰዎቹ የተለዮት ለብሰውት በነበረው ልብስ ነው። የዐይን እማኞቹ እንዳሉት ሰዎቹን ለመቅበር ግዜ አልነበረም። እስካሁን ጅቦቹ አስክሬኖቹን በልተው ጨርሰው ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል” ሲሉም አክለዋል።
ግድያው የተፈጸመው አነስተኛ ቁጥር ያላቸውና በጦርነቱ ተሳታፊ ያልሆኑ የኩናማ ብሔረሰብ ሰዎች ላይ መሆኑ ነገሩን የበለጠ የከፋ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
“ሁለቱም ወገኖች ወታደሮች እያጡ ነው። ወደ መንደሮች ሲገቡ እልሀቸውን የሚወጡት ነዋሪዎች ላይ ነው” ሲሉ የረድዔት ሠራተኛው አክለዋል።
የትግራይ ኃይሎች ወደ ትግራይ ከመመለሳቸው በፊት በአማራ እና አፋር ክልሎች ሳሉ የመድፈር፣ ከሕግ አግባብ ውጭ የመግደል እና የመዝረፍ ክሶች ቀርቦባቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዘመኑ ያለፈበት የውጊያ ስልት
በጦርነቱ ከደረሰው ቀውስ ባሻገር ሁሉም ተዋጊ ኃይሎች “የሰው ማዕበል” በመጠቀም የበላይነት በማስጠበቅ እንዲሁም በግዳጅ ሰዎችን ለውትድርና በመመልመልም ይከሰሳሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙት የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ አብዱራሕማን ሳይድ “ሰዎች በግዳጅ ወታደር ይሆናሉ። ከተወሰኑ ሳምንታት ሥልጠና በኋላ የጠላት ኃይል ወደሰፈረበትና ፈንጅ ወደተቀበረበት አካባቢ በከፍተኛ ቁጥር ይላካሉ” ይላሉ።
“የጠላት ኃይል ተኩስ ይከፍትና አብዛኞቹን ይገድላቸዋል። ጠላት ጥይት እስከሚጨርስ ድረስ በከፍተኛ ቁጥር መሄዳቸውን ይቀጥሉና አካባቢውን ይቆጣጠራሉ” ሲሉም ያክላሉ።
አብዱራሕማን ጨምረውም “ዘመኑ ያለፈበት የውጊያ ስልት ነው። ይህንን መንገድ በ1890ዎቹ መጀመሪያ የተጠቀሙት የአቢሲኒያ ንጉሥ የጣልያን ወራሪዎችን ለማሸነፍ ነበር። የጣልያን ኃይል በአየር ኃይል የበላይነት ቢኖረውም በርካታ ሰዎች ሲላኩበት አቅሙን ተፈታትኖታል” ብለዋል።
ይህ የጦርነት መንገድ በርካታ ሰዎች የሚያልቁበት እንደሆነ የሚናገሩት አብዱራሕማን፣ በሁለት ዓመቱ ጦርነት ከ700 ሺህ እስከ 800 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ይገልጻሉ።
“ጦርነቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ዘግናኙ ነው” ሲሉም ጨምረዋል።
አሜሪካ የሚገኙት የአፍሪካ ቀንድ ተንታኝ ፈይሰል ሮብሌ፣ የትግራይ ኃይሎች የሰዎች ማዕበል ተጠቅመዋል የሚለውን ባይቀበሉትም፣ በጦርነቱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥርን በተመለከተ ከአብዱራሕማን ጋር የሚቀራረብ ቁጥር ያስቀምጣሉ።
“በጦርነቱ የመጀመሪያ ሁለት ክፍሎች ወደ 500 ሺህ ሰዎች ሞተዋል። በሦስተኛው ዙር ደግሞ 100 ሺህ ሰዎች ሳይሞቱ አልቀረም” ብለዋል።
ፈይሰል እንደሚሉት፣ የትግራይ ኃይሎች በአግባቡ የሠለጠኑና ለመዋጋትም “የፈቀዱ” ሲሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች በቁጥር እና በአየር ኃይል ብልጫ አላቸው።
"አሁን አምባሳደር የሆኑ ጀነራል እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግሥት በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ወጣት ወንዶችን ሊመለምል ይችላል። ተዋጊ ጀቶች እና ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ የቱርክ ድሮኖችም አሏቸው። የትግራይ ኃይሎች ግን የአየር ኃይል የላቸውም” ሲሉ ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዕዝ ወደ ኤርትራ መዲና አሥመራ ተዛውሯል የሚሉት ፈይሰል፤ ተዋጊ ጀቶች ከኢትዮጵያ አየር ኃይል መቀመጫ ቢሾፍቱ በተሻለ ለትግራይ ከምትቀርበው አሥመራ እንደሚነሱ ጠቅሰዋል።
ሰው አልባ ተዋጊ አውሮፕላኖቹ ግን አሁንም መነሻቸው ቢሾፍቱ ነው ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቁርሾ ማወራረድ
ኤርትራ ወደ ጦርነቱ የገባችው ከህወሓት ጋር በቋጠሩት ቁርሾ ምክንያት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን እስከሚመጡ ድረስ ህወሓት የጥምር ፓርቲው አስተዳደርን በበላይነት ይዞ ቆይቷል።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ የድንበር ጦርነት 80 ሺህ ሰዎች ሞተዋል። ኢትዮጵያ ለኤርትራ እንድትሰጥ የተወሰነውን ግዛት ህወሓት መራሹ አስተዳደር ሳያስተላለፍ ቆይቷል።
ከሁለት ዓመት በፊት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሲነሳ ግን ኤርትራ ግዛቱን በቁጥጥር አውላለች።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ህወሓትን እንዲያጠፉ የሚደግፉት ህወሓት ለኤርትራ ስጋት እንዳይሆን ለመከላከል ነው ሲሉ ተቺዎች ያስረዳሉ።
“የኤርትራ ስጋት፤ ህወሓት ተመልሶ ኢትዮጵያን ወደማስተዳደር ይመጣል ወይም ደግሞ በአሥመራ የሚታዘዘው አስተዳደር መሥርቶ ቀይ ባሕርን ለመጠቀም ያውለዋል የሚል ነው። ትግራይ ገና ያላደገች፣ ባሕር አልባም ናት” ይላሉ አብዱራሕማን።
ባለፉት ሳምንታት የትግራዩ ጦርነት ሲፋፋም፣ የኤርትራ መንግሥት ወታደሮቹን በስፋት እንዳሰማራ እና ኃይሉን ያልተቀላቀሉ ሰዎችን በመላው አገሪቱ አድኖ ወታደር እያደረገ እንደሆነ ብዙ ምንጮት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
መስከረም ላይ የኤርትራ ወታደሮች አክሩር በተባለች ከተማ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ገብተው የውትድርና ጥሪውን ያልተቀበሉ ቄስ፣ ወጣት ምዕመናን እና መዘምራን እንዳፈኑ ከምንጮች ተሰምቷል።
ፕ/ር አሌክስ ዲ ዋል እንዳሉት፣ ወታደራዊ ጥሪው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ “የትኛውንም አማራጭ እንደሚጠቀሙ” ማሳያ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በግዳጅ ወታደር የሆኑ ሰዎችን በከፍተኛ ቁጥር ወደ ትግራይ አላኩም።
“ኤርትራ ትግራይ ውስጥ ኃይሎች አሏት። አብዛኛው ውጊያ እየተካሄደ ያለው ግን ከኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ነው። ኢሳያስ ጦርነቱን እየመራ ያለው ጦርነቱን እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል ለዐቢይ ማሳየት እንደሚችል ስለሚያምን ነው። ሆኖም ግን ጦርነቱ የሞት እና ሕይወት ጉዳይ ስለሆነ የትግራይ ተወላጆች በቢላ እና ድንጋይም ቢሆን ይዋጋሉ” ሲሉ አስረድተዋል።
ንግግር ላይኖር ይችላል
ጦርነቱ ከአራት እስከ ስድስት በሚደርሱ ግንባሮች እየተካሄደ እንደሚገኝ እንዲሁም በአዲግራት አቅራቢያ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች እንደሰፈሩ አብዱራሕማን ይናገራሉ።
“በአዲግራት እና መቀለ ጥቃት ለመሰንዘር ዝግጁ ናቸው” ሲሉም ያክላሉ።
በጦር ግንባር የሚገኙ ምንጮች ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ኃይሎች ከሽረ ወደ ታሪካዊቷ አክሱም፣ ወደ አድዋ እና ወደ አዲግራት ማቅናት ጀምረዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለቱ ወገኖች ግጭቱን በሰላም እንዲፈቱ ቢወተውቱም፤ አብዱራሕማን ንግግር ይኖራል ብለው አያምኑም።
“በታሪክ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የቀድሞዋ አቢሲኒያ መሪ መደቦች ለሥልጣን ይዋጋሉ። ሌላ ኃያል እስከሚመጣ ድረስ ኃያላኑ የንጉሦች ንጉሥ ይሆናሉ። ግጭትን በሰላም የመፍታት ባህል የለም። በዜሮ የማባዛት አካሄድ ነው” ሲሉ ያብራራሉ።
ፕ/ር አሌክስ እንደሚሉት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአፋጣኝ የተኩስ አቁም ማስፈን ይኖርበታል።
“ይህ ካልሆነ ግን የዘር ጭፍጨፋ እና የጅምላ ረሃብ ስጋት አንዣቧል” ይላሉ።
በቤልጄም ምሁራን የተመራ ቡድን በዚህ ዓመት መባቻ ላይ እንዳለው፣ ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ከ250 ሺህ በላይ የትግራይ ተወላጆች በረሃብ እና ተያያዥ ምክንያቶች ሞተዋል።
ፕ/ር አሌክስ “እህል መሰብሰብ መጀመር የነበረበት አሁን ነው። ነገር ግን ኤርትራ መራሹ ኃይል የትግራይን መሬት ብኩን አድርጎታል” ይላሉ።












