ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእስራኤል ካቢኔ የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነት አጸደቀ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጥምር መንግሥት ከሐማስ ጋር የተደረሰውን እና በመጪው እሁድ ተግባራዊ የሚሆነውን የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት አጸደቀ።
ውሳኔው የታወጀው ለሰዓታት እስከ ምሸት ድረስ ከቀጠለው ውይይት በኋላ ነው። ሁለት የቀኝ አክራሪ ሚኒስትሮች ስምምነቱን ተቃውመውታል።
የአገሪቱ የጸጥታ ካቢኔ ቀደም ሲል የተኩስ አቁም ስምምነቱ "የጦርነቱን ዓላማዎች ለማሳካት ይደግፋል" ሲል እንዲጸድቅ ሐሳብ ማቅረቡን የኔታንያሁ ጽህፈት ቤት አስታውቆ ነበር።
ለአስራ አምስት ወራት የዘለቀውን ጦርነት እልባት ይሰጠዋል የተባለውን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ረቡዕ፣ ጥር 7/2017 ዓ.ም. ይፋ መሆኑን ተከትሎ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት 73 ፍልስጤማውያን በአንድ ምሽት መገደላቸውን በሐማስ የሚተዳደረው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ አስታውቋል።
ኳታር፣ አሜሪካ እና ግብጽ ያደራደሩት ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት ሦስት ምዕራፍ አለው።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ሴቶች፣ ህጻናት እና አዛውንቶችን ጨምሮ 33 ታጋቾች ይለቀቃሉ።
እስራኤል በምላሹ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትለቃለች።
የእስራኤል ጦር ከምሥራቃዊ የጋዛ ክፍል እንደሚወጣ እና የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጿል።
በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገቡም ይፈቀዳል።
በሁለተኛው የስምምነቱ ዙር ተጨማሪ ታጋቾች የሚለቀቁ ሲሆን፣ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ እና "ዘላቂ መረጋጋትን ማምጣት" ያለመ ሲሆን ይህም የሚተገበረው የመጀመሪያው ዙር 16 ቀን ሲሞላው ነው።
ሦስተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ ጋዛን መልሶ መገንባት ሲሆን፣ ይህም ዓመታት ይወስዳል።
በዚህ ምዕራፍ የታጋቾች አስክሬንም ይመለሳል።
ኳታር በመጀመሪያው ምዕራፍ የሚለቀቁት የእስራኤል ታጋቾች "ሰላማዊ ሴቶች፣ ሴት ወታደሮች፣ ህጻናት፣ አዛውንቶች፣ የታመሙ እና የቆሰሉ ሲቪሎች" እንደሚገኙበት ገልጻለች።
የእስራኤል የፍትህ ሚኒስቴር በታጋቾች ምትክ የሚለቀቁ በእስራኤል እስር ቤቶች ያሉ የ737 ፍልስጤማውያን ስም ዝርዝር ይፋ ማድረጉ ተገልጿል። የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስም እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት ቀጥላለች።
እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ46,870 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።
ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።
እስራኤል በጋዛ ጦርነት በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል። እስራኤል ይህንን አልተቀበለችውም።
መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የእስራኤል ባለሥልጣናት ፍልስጤማውያንን ከሰብዓዊነት ባወረደ መልኩ የሚሰጧቸው ትርክቶች እንዲሁም እስራኤል ሆን ብላ ተቋማት ላይ ካደረሰቻቸው ውድመቶች እና እልቂቶች በመነሳት የዘር ጭፍጨፋ እንደሆነ ድምዳሜ ላይ መድረሱን ገልጾ ነበር።
በተጨማሪም በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን ሆን ብላ በገፍ በማፈናቀል የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል መፈጸሟን ሂውማን ራይትሰ ዋች አስታውቆ ነበር።
እስራኤል በበኩሏ ሪፖርቱን አጣጥላ "ሙሉ በሙሉ ስህተት እና ከእውነታ የራቀ ነው" ማለቷ ይታወሳል።