በኢትዮጵያ ጉብኝት ስላደረጉት የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ አንዳንድ እውነታዎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ

የፎቶው ባለመብት, hopr

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ

በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በሁለቱ አገራት ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች ላይ ውይይት በማድረግ አዳዲስ የትብብር ስምምነቶች መፈራረማቸው ዘግቧል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ረቡዕ ታኅሣሥ 8/2018 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የጋራ ስብሰባ ላይ ብሔራዊ ቴሌቪዥኑ ላይ በቀጥታ ያልተላለፈ ንግግር አድርገዋል።

በዓለም የአገራት የምጣኔ ሀብት ደረጃ ላይ አሜሪካን፣ ቻይናን፣ ጀርመንን እና ጃፓንን ተከትላ በአምስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው እና በሕዝብ ብዛት የዓለማችን ቀዳሚ አገር የሆነችው ሕንድ 15ኛው ጠቅላይ የሆኑት ናሬንድራ ሞዲ ማን ናቸው? ለየት ለየት የሚያደርጓቸው እውነታዎች የትኞቹ ናቸው?

 የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ

የፎቶው ባለመብት, pmo

የምስሉ መግለጫ, የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ንግግር ሲያደርጉ

ከሕንዷ ጉጃራት ግዛት ከዝቅተኛ ደረጃ ተነስተው በዓለም ታላላቅ ምጣኔ ሀብት ካላቸው አገራት መካከል አንዷን ለረጅም ጊዜ ለመምራት ችለዋል።

ሞዲ ወደ ፖለቲካው ዓለም የገቡት ገና በለጋ የወጣትነት ዕድሜያቸው በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲሆን፣ በኃያሉ የሂንዱ ብሔረተኛ ፓርቲ ባሃራቲያ ጃናት ፓርቲ (ቢጄፒ) ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ውስጥ አልፈዋል።

በአውሮፓውያኑ 2001 የጉጃራት ግዛት ዋና አስተዳዳሪ፣ በ2014 የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ከፍተኛው ሥልጣን ጨበጡ።

ከአስር ዓመታት በላይ በመሪነት ሥልጣን ላይ የቆዩት ሞዲ በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ አሸንፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ በሕንድ ውስጥ ያላቸው ተቀባይነት በተለይም በሂንዱዎች መካከል ከፍተኛ ሲሆን፣ ድጋፋቸውንም ለማጠናከር የሂንዱ ዕምነት ቤተ መቅደሶችን ይጎበኛሉ።

የሕንድ የሙስሊም ዕምነት ተከታይ ቡድኖች ግን በሞዲ የሥልጣን ዘመን በአገሪቱ ውስጥ አድሎዎ እና ጥቃት በተደጋጋሚ እንደሚገጥማቸው እና "እንደ ሁለተኛ ዜጋ" እንደሚኖሩ ቅሬታ ቢያሰሙም ገዢው ፓርቲ ግን ይህንን ያስተባብላል።

ናሬንድራ ሞዲ የሚከተሉት ፖሊሲ አገራቸው ከሁሉም ኃያላን አገራት ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲኖራት ማድረግ ነው። በዚህም ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ እና ከሩሲያ ጋር የጠበቀ ግንኙነትን መፍጠር ችለዋል።

በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ያላቸው ተደማጭነትም ከፍተኛ ሲሆን የአፍሪካ፣ የእስያ እና የሌሎች በመልማት ላይ ያሉ አገራትን ጉዳዮች አንስተው ይከራከራሉ። በተለይ በ2023 ሕንድ ባስተናገደችው የቡድን 20 ጉባኤ ላይ በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ድምጽ በማሰማት በዓለም መድረክ አድናቆትን አግኝተዋል።

ምንም እንኳን እየጨመረ ባለው የሥራ አጦች ቁጥር እና የዋጋ ንረት ምክንያት ትችት ቢገጥማቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕንድ ውስጥ ልማትን በማስፋፋት እና በሕዝባዊ መድረኮች ላይ በመገኘት ተወዳጅነት በማትረፋቸው እርሳቸው በተደጋጋሚ ከመመረጣቸው በተጨማሪ የፓርቲያቸው ተወዳጅነት ጨምሯል።

የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር

የፎቶው ባለመብት, PM Office

ስለ ሞዲ ለየት ያሉ እውነታቸው

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሞዲ በአስራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳሉ ለአጭር ጊዜ ከአገር አገር የሚዘዋወሩ መነኩሴ ነበሩ። ለሁለት ዓመታትም ወደተለያዩ የሕንድ ግዛቶች በመዘዋወር የተለያዩ ባህሎችን እና ታዋቂ የሂንዱ ቤተ መቅደሶችን ለማወቅ ችለዋል።

በቤተሰባቸው አመቻችነት በአፍላ ዕድሜያቸው በአውሮፓውያኑ 1968 ከጃሾዳቤን ሞዲ ጋር ጋብቻ መሥርተዋል። ብዙም ስለ ትዳር ሕይወታቸው የማይናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጆች ያሏቸውም። ባለፈው ዓመት ምርጫ ወቅትም "ልጆች የሉንም፤ ለእናንተ ልጆች ነው እየሠራን ያለነው" በማለት በይፋ ተናግረዋል።

በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ኢንድራ ጋንዲ በመላው አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግገው የሞዲ ድርጅትን በማገድ በርካታ ተሳታፊዎቹን ሲያስሩ፣ ሞዲ የሲክ መነኩሴ መስለው ከእስር አምልጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ከፖለቲካው ባሻገር በርካታ መጽሐፍ ያላቸው ደራሲ ሲሆኑ፣ በጉጂራት ቋንቋ የሥነ ግጥም ስብስቦችንም አሳትመዋል።

ሞዲ በሚከተሉት የጾም ሥርዓት የሚታወቁ ሲሆን፣ በአንዳንድ ወቅቶችም ሙሉ ለሙሉ ለዘጠኝ ቀናት ራሳቸውን ከምግብ አቅበው ትኩስ ውሃ ብቻ በመጠጣት እንደሚጾሙ ይነገራል። እንዲሁም ለአራት ወራት በሚቆየው የጾም ወቅትም በቀን አንድ ጊዜ በመመገብ በመጾም ይታወቃሉ።

ከአስር ዓመታት በላይ በሕንድ የጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበር ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ እስካሁን አንድም ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው አያውቁም። ነገር ግን በጥንቃቄ የተዘጋጁ ጥቂት ቃለ ምልልስ ሰጥተዋል።

ናሬንድራ ሞዲ የተወለዱት በአውሮፓውያኑ መስከረም ወር ላይ በ1950 ሲሆን፣ ሕንድ ነጻ ከወጣች በኋላ ተወልደው የመሪነትን ሥልጣን የያዙ የመጀመሪያው መሪ ናቸው። ቀደምቶቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በሙሉ የተወለዱት ሕንድ በብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ስር ሳለች ነው።

ለገጽታቸው ጠንቃቃ መሆናቸው የሚነገርላቸው ሞዲ በሕዝብ ዘንድ ያለቸውን ገጽታ በጥንቃቄ መቅረጽ የቻሉ ናቸው።

ከአለባበስ አንጻር በትውልድ አካባቢያቸው የሚታወቀውን ባህላዊ ልብስ የሚኣዘወትሩ ሲሆን፣ ፎቷቸው በሰፊዋ ሕንድ ውስጥ ከግዙፍ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች እስከ ኮቪድ ክትባት የማይታይበት ቦታ የለም።

የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር

የፎቶው ባለመብት, PM Office

ጠ/ሚ ሞዲ በተወካዮች ምክር ቤት ምን ተናገሩ?

ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በኢትዮጵያ የሚገኙት የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለሕዝብ እንደራሴዎች ንግግር አድርገዋል።

ሞዲ ረቡዕ ታኅሣሥ 8/2018 ዓ.ም. ለፌዴሬሽን እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር ሁለቱ አገራት ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት በማንሳት አድንቀዋል።

"በመካከላችሁ ስገኝ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል። እዚህ በኢትዮጵያ የአንበሶች ምድር በመገኘቴ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል" ብለዋል።

በ1.4 ቢሊዮን ሕንዳውያን ስምም "የወዳጅነት፣ የመልካም ምኞት እና የወንድማማችነት ሰላምታዬን አቀርብላችኋለሁ" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተገኙበት ባደረጉት በዚህ ንግግር በሕንድ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ዘላቂ ትስስርን ጠንካራነት ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በኢትዮጵያ 'ድር ቢያብር አንበሳ ያስር' የሚል አባባል እንዳለ ተነግሮኛል። በሕንድ ደግሞ 'ልቦች የሚያብሩ ከሆነ ተራራ መግፋት ይችላሉ' የሚል አባባል አለን። እውነትም አብሮነት ጥንካሬ ነው፤ ትብብር ኃይል ነው" ብለዋል።

"ዛሬ በዓለም ደቡባዊ ክፍል ያለው ሕዝብ፣ እንደ ጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት፣ እንደ ወዳጅ ኢትዮጵያ እና ሕንድ በጋራ ይቆማሉ" ሲሉ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ትብብር ጠቅሰዋል።

የሕንድ ኩባንያዎች ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰሳቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጨርቃ ጨርቅ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና ፣ በጤና እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ተሰማርተው እንሚገኙ አክለዋል።

የሕንድ ኩባንያዎች ከየትኛውም የውጭ ባለሃብት በበለጠ በኢትዮጵያ ውስጥ ሃብታቸውን ያፈሰሱ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ከ75 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ጠቅሰዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት በሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት ከፍ ማለቱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ይህም በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ፣ በማዕድን እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ መስኮች በሚደረግ ትብብር እንዲሁም አጋርነት እንደሚገለጽ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እና በሕንድ መካከል ያለው ሁለንተናዊ ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራቸው የምታደርገውን ድጋፍ ለማጠናከርም ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።

በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሳይበር ደኅንነት፣ በአቅም ግንባታ፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና ላይ በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሁለቱ አገራት ስለሚጋሯቸው ታሪኮች፣ ቅርሶች እና ፍላጎቶች ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በሕንድ እና በኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ውስጥ "አገር በእናት መመሰሏን" በማንሳት ያለውን መመሳሰል አስረድተዋል።

ይህም የኩራት ምንጭ እና ለአገር ያለ ኃላፊነትን ያሳያል ሲሉም አክዋል።

የሕንድ ዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በአገሪቱ ያለውን አገልግሎት አሰጣጥ እና አቅርቦት ማዘመናቸውን በማንሳት ለኢትዮጵያ ይህንን ልምዳቸውን ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የክብር ኒሻን ተሸልመዋል።