ስታርመር አገራቸው ለሕንዳውያን የቪዛ ደንቦችን እንደማታላላ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር አገራቸው ለሕንዳውያን የቪዛ ደንቦችን እንደማታላላ ተናገሩ።
ስታርመር ወደ ሕንድ ከማምራታቸው በፊት እንደተናገሩት ከሆነ በሁለቱ አገራት መካከከል ያለውን የንግድ እና የባሕል ትስስር ለማሳደግ "ትልቅ ዕድል" አለ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሕንድ ከ100 በላይ ልዑካንን ይዘው የሚጓዙ ሲሆን በቡድኑ ውስጥ ሥራ ፈጣሪዎች፣ የባሕል መሪዎች፣ የዩኒቨርስቲ ምክትል ቻንስለሮች ተካትተውበታል።
የጉዟቸው ዓላማ የዩኬን ኢንቨስትመንት ማሳደግ እና ዘገምተኛ የሆነውን የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት እድገት ማሻሻል ነው ተብሏል።
ስታርመር ለዩኬ ተማሪዎችም ሆነ ሠራተኞች ተጨማሪ የቪዛ ገደቦችን የማላላት ዕቅድ የለም ሲሉ ተናግረዋል።
"ጉዳዩ የቪዛ አይደለም" ብለዋል ሰር ኪር ስታርመር።
"ንግግራችን ቢዝነሶችን እና ኢንቨስትመንቶችን፣ ሥራዎችን እና ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ስለሚመጣ ብልጽግና ይሆናል" ብለዋል።
በዩኬ እና በሕንድ መካከል ለዓመታት ድርድር ሲደረግ ቆይቶ ስምምነቱ የተፈረመው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ነው።
ይህንን ስምምነት ተከትሎ የዩኬን ውስኪ እና መኪኖች ወደ ሕንድ ለመላክ ርካሽ ሲሆን የሕንድ ጨርቃ ጨርቅ እና ጌጣ ጌጥን ወደ ዩኬ ለማስገባትም እንዲሁ ዝቅተኛ ዋጋ የሚጠየቅበት ይሆናል።
ይህም በቢሊዮኖች የሚቆጠር ንግድን በሁለቱ አገራት መካከል በማሳለጥ ቢዝነሶችን ከፍ ያደርጋል ተብሎ ታስቧል።
የሁለቱ አገራት ስምምነት በዩኬ በአጭር ጊዜ ቪዛ ተቀጥረው የሚሰሩ ሕንዳውያን ለሦስት ዓመት ያህል የሶሻል ሴኩሪቲ እንዳይከፍሉ አድርጓቸዋል።
ነገር ግን የሕንድ ባለሥልጣናት በዩኬ ኢሚግሬሽን ፖሊሲ ላይ መሠረታዊ ለውጥ የለም ሲሉ ይናገራሉ።
የሌበር ፓርቲ መንግሥት ወደ ዩኬ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥርን ለመቀነስ እየሰራ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ዩኬ መጥተው ለመቆየት የሚፈልጉ ስደተኞች ላይ ጥብቅ የሆነ ፖሊሲን ይፋ አድርጓል።
ወደ ሙምባይ እየተጓዙ ለጋዜጠኞች ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሰር ኪር ስታርመር፣ በሁለቱ አገራት የንግድ ንግግር ላይ ቪዛ "ምንም ሚና የለውም" ያ ነባራዊ ሁኔታም አልተለወጠም ብለዋል።
አሜሪካ በኤች ዋንቢ ፖሊሲዋ ላይ ለውጥ ማድረጓን ተከትሎ ዩኬ የሕንድ የቴክኖሎጂ ሰዎች ለመሳብ ለውጥ ታደርግ እንደሆነ ተጠይቀው ዩኬ "ምርጥ ክህሎት" ያላቸውን ከመላው ዓለም በመሳብ ምጣኔ ሃብቷን ማሳደግ እንደምትፈልግ ተናግረው፣ ነገር ግን ለሕንድ ሌላ አዲስ የቪዛ ደንብ አይኖርም ብለዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተጓዙት የብሪቲሽ ኤርዌይስ ልዑካን በሚቀጥለው ዓመት ከዴልሂ ወደ ሂትሮው በቀን ሦስተኛውን በረራ ለመጀመር ያላቸውን ዕቅድ ተናግረዋል።
ማንችስተር የሚገነው አውሮፕላን ማረፊያም ወደ ዴልሂ ቀጥታ በረራ እንደሚያደርግ አስታውቋል።












