በቤኒን ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ 34 ሰዎች በእሳት አደጋ ሞቱ

ቤኒን ከሰሜናዊ ናይጄርያ በምትዋሰንበት የድንበር ከተማ አቅራብያ ቅዳሜ ዕለት በተነሳ እሳት 34 ሰዎች መሞታቸው ተዘገበ።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አላሳኔ ሴዱ፣ ሴሜ ፖጂ በተባለች ከተማ በተቀሰቀሰ እሳት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ 34 ሰዎች መሞታቸውን ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

አክለውም የእሳቱ መነሻ ምክንያት በሕገወጥ መንገድ የተከማቸ ነዳጅ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን ይበሉ እንጂ ሮይተርስ የሟቾቹን ቁጥር 35 ያደርሰዋል።

ሮይተርስ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ አደጋው የተቀሰቀሰው የነዳጅ ዘይት በሚቀዳበት ወቅት ነው ብሏል።

የእሳት አደጋው በአካባቢው የሚገኙ ሱቆችን ማውደሙን እንዲሁም 35 ሰዎችን መግደሉን የአሪቱ ፍትህ ሚኒስትር ተወካይ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

በእሳት አደጋው ተቃጥለው ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ፣ 20 ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ በመጎዳታቸው ሆስፒታል ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ነው ተብሏል።

የእሳት አደጋው እንደተነሳበት በተገለጸው ሕገወጥ የነዳጅ ማከማቻ መጋዘን አካባቢ በወቅቱ ሞተር ሳይክሎች፣ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች እና መኪናዎች ነዳጅ ለመቅዳት ተሰባስበው ነበር ተብሏል።

አክሎም የእሳት አደጋውን መንስዔ ለማወቅ ምርመራ መጀመሩን ተወካዩ መናገራቸውን ገልጿል።

በቤኒን ነዳጅ አምራች ከሆነችው ጎረቤት አገር ናይጄርያ በሕገወጥ መንገድ ነዳጅ ማስገባት እና ማከማቸት የተለመደ ተግባር ነው።

የቤኒን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥርን ከመግለጽ ባለፈ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ከናይጄርያ በሕገወጥ መልኩ የሚገባው ነዳጅ ዘይት በጥቁር ገበያ በሕገወጥ ነጋዴዎች አማካኝነት ለተጠቃሚዎች ይሸጣል።

በቤኒን በነዳጅ ማከማቻ ላይ የእሳት አደጋ ያልተለመደ ቢሆንም በናይጄርያ ግን በተደጋጋሚ ይከሰታል።

ናይጄርያ ከዚህ ቀደም የነዳጅ ዋጋ ላይ ድጎማ ታደርግ የነበረ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ድጎማውን በማንሳቷ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።