ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፍሎሪዳ 'መጫወቻዬን ተቀማሁ' ያለ የ10 ዓመት ታዳጊ የእናቱን መኪና ይዞ ከጠፋበት ተያዘ
በአሜሪካዋ ግዛት ፍሎሪዳ በዋና መንገድ ላይ መኪና ሲያሽከረክር የነበረ የ10 ዓመት ታዳጊ ፖሊስን አስደንግጧል።
ፖሊስ የ10 ዓመቱ ታዳጊ የሚያሽከረክረውን መኪና እንዲያቆም ሲያደርግ ከ11 ዓመት እህቱ ጋር ሲመለከተው መደንገጡ ተዘግቧል።
እነዚህ የ10 እና የ11 ዓመት ታዳጊዎች ከመኖርያ ቤታቸው 300 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀው ነበር በፖሊስ የተያዙት።
የሁለቱ ታዳጊዎች እናት ልጆቿ መጥፋታቸውን ለፖሊስ ያመለከተችው የሳምንቱ መጀመርያ ላይ ነበር።
ሁለቱ ታዳጊዎች የሚጫወቱበትን የኤሌክትሮኒክስ መሳርያ ከተነጠቁ በኋላ ተያይዘው ለመጥፋት መወሰናቸው ተሰምቷል።
“የ10 ዓመት ወንድ ልጅ ከእህቱ ጋር ከመኪናው ሲወጣ የተመለከቱት ፖሊሶች ዓይናቸውን ማመን አልቻሉም ነበር” ሲል የነበረውን ሁኔታ ፖሊስ ገልጿል።
ታዳጊዎቹ ከሚያሽከረክሩት መኪና ጋር በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሐሙስ ዕለት አመሻሽ ላይ በአላቹአ ካውንቲ ሲሆን የአካባቢው ፖሊስም ሁኔታውን “ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጠ” ሲል ገልጾታል።
ታዳጊዎቹ ያሽከረክሯት የነበረችው ነጭ ሲዳን መኪና መጥፋቷ ሪፖረት የተደረገው ከአላቹአ 320 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ኖርዝ ፖርት ከተማ ነው።
ፖሊሶቹ ታዳጊዎቹን ካስቆሙ በኋላ የተረዱትን ነገር ሲገልጹ “ሁለቱም ታዳጊዎች እናታቸው የኤሌክትሮኒክስ መጫወቻወቻቸውን በአግባቡ እየተጠቀሙባቸው ባለመሆኑ የተነሳ ከወሰደችባቸው በኋላ በጣም ተበሳጭተው ነበር” ብለዋል።
ፖሊስ አክሎም እናታቸው በቤት ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ቅጣት እንደፈጸመችባቸው የሚያሳይ ምንም ነገር አላገኘንም ብሏል።
እናት የልጆቿን መገኘት ከሰማች በኋላ ሦስት ሰዓት ያህል ነድታ በመሄድ ልጆቿን ተረክባለች።
“ባልደረቦቻችን ከእናትየው ጋር ለረዥም ሰዓት የተወያዩ ሲሆን ሁለት ልጆቿን ለማሳደግ የምትችለውን ሁሉ የምታደርግ መሆኗን ተረድተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ድጋፍ በሚያስፈልጋት ወቅት ማድረግ ያለባትን ነገሮች አስተያየት እና ምክሮች ሲሰጣት ተቀባይ ነበረች” ብሏል።
በፍሎሪዳ በ15 ዓመት መኪና መለማመድ የሚቻል ቢሆንም ሙሉ መንጃ ፈቃድ ለመያዝ ግን እድሜው 18 መሙላት አለበት።