በሱዳን የሰዎች ቤት እየተሰበረ ከቴሌቪዥን እስከ ጫማ እየተዘረፈ ነው ተባለ

በእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ በምትገኘው ሱዳን የሰዎች መኖሪያ ቤት እየተሰበረ ከቴሌቪዥን እስከ ጫማ፤ ከልብስ እስከ ጥሬ እህል እየተዘረፈ መሆኑ ተገለጸ።

ሱዳንን በጋራ ሲሟሯት የነበሩት ሁለት የጦር ጀነራሎች በስልጣን ሹኩቻ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ ከ7 ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ በአየር እና የብስ መኖሪያ ቤቱን ጥሎ ተሰዷል።

ታዲያ ይህን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ወንጀለኛ ቡድኖች እና በጦርነት ምክንያት የሚበሉትን ያጡ ሱዳናውያን የተሰደዱ ሰዎችን መኖሪያ ቤቶች እያደኑ ከኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች እስከ ጥሬ እህል እየዘረፉ ይገኛሉ።

ዘረፋው በተለይ ደግሞ በካርቱም እና ኦማድሩማን ከተሞች ተበራክቶ ይገኛል። ዘረፋው ቀድሞ የጀመረው ባለ ጸጋ የሆኑ ሱዳናውያን መኖሪያ ቤቶች ላይ ነበር። አሁን ግን በካርቱም እና ኦማድሩማን የቤት ባለቤት የሌለበት ቤት የዘራፊዎች ሲሳይ ሆኗል።

ዘራፊዎች ወደ አንድ መኖሪያ ቤት ዘልቀው በመግባት ይጠቅማል ያሉትን ይዘው ይጣሉ። በአንዳንድ አጋጣሚዎች ሰዎች የዘረፉትን በአህዮቻቸው እየጫኑ ሲወስዱ ታይተዋል።

የአገሪቱ ጦር መሪ ጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጀነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ አገሪቱ ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ከገባች ሰባት ወራት አልፈዋል።

በጦርነቱ ምክንያት በአገሪቱ መንግሥት አለ ማለት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። የፖሊስ ኃይል ተበትኗል። እስር ቤቶች ተሰብረው ወንጀለኞች ነጻ ሆነዋል እንዲሁም ፍርድ ቤቶች አገልግሎት እየሰጡ አይደለም።

በተለይ በካርቱም ከሚገኙ ሃብታም ከሚባሉ ሱዳናውያን መኖሪያ ቤት የተዘረፉ ንብረቶች የደሆች መንደር በሆኑት ኦምባዳ እና አል-ታዋራዋ ለሽያጭ ቀርበው ይታያሉ።

በእነዚህ መንደሮች የሚኖሩ ሰዎች እንደ አብዛኛዎቹ የካርቱም ዜጎች ቀያቸውን ጥለው አልተሰደዱም። እኚህ በየዕለቱ የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት የሚጣጣሩ የኦምባዳ እና አል-ታህራዋ መንደር ነዋሪዎች ሳይሰደዱ የቀሩት ትተውት የሚሄዱ ንብረት አሳስቷቸው ሳይሆን ለመሰሰደድ እንኳ አቅሙ አጥሯቸው ነው ትላለች ሱዳናዊቷ ጋዜጠኛ ዘይነብ ሞሐመድ ሳሊህ።

በሰላሙ ወቅት የዚህ መንደር ነዋሪ ከሆኑ ሴቶች መካከል ቢያንስ ሩብ ያክሉ የካርቱም ሃብታም ሰዎች ቤት ውስጥ የቤት ሰራተኛ ሆነው የሚሰሩ ነበሩ።

አሁን ላይ ከዚህ ቀደም በሃብታም ሰዎች ቤቶች ውስጥ የቤት ሠራተኛ የነበሩት ሴቶች ከሃብታም ሰዎች ቤት የተዘረፉ እቃዎች ነጋዴ ሆነዋል።

ከዚህ ቀደም 150ሺህ የሱዳን ፓዎንድ ይሸጥ የነበረው ዲጂታል ቴሌቪዥን አሁን ላይ በድሆቹ መንደር በ10ሺህ የሱዳን ፓዎንድ መግዛት ይቻላል።

በካርቱም መኖሪያ ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ ግዙፍ መጋዘኖችም ለዝርፊያ ተጋልጠዋል።

ከእነዚህ መካከል በኦማዱርማን ከተማ ይገኝ የነበረው ምግብ የያዘ መጋዘን ይገኝበታል። ይህ መጋዘን ለተከታታይ ሳምንታት ሲዘረፍ ቆይቶ ባዶውን ከቀረ በኋላ ሆን ተብሎ በእሳት እንዲጋይ ተደርጓል።

በአንድ የሽቶ ፋብሪካ ላይ ዘረፋ ሲፈጸም ደግሞ አንድ አሳዛኝ ክስተት ተፈጥሯል። በዘረፋ ወቅት ፍንዳታ አጋጥሞ ሕጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ ከ120 ያማያንሱ ሰዎች በእሳት ተቃጥለው ሕይወታቸው አልፏል።

የአካባቢው ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ በሽቶ ፋብሪካው እሳት የተነሳው አንድ የሚሰረቅ ነገር ፍለጋ የሄደ ወጣት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ አልታይ ሲለው ላይተሩን ሲለኩስ ፍንዳታ በማጋጠሙ ነው።

በወቅቱ በሽቶ ፋብሪካ ውስጥ የገቡ ሴት ዘራፊዎች የሚያገኙትን ሽቶ እየተቀባቡ ስለነበረ ለእሳቱ በፍጥነት መሰራጭ ምክንያት መሆኑ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

ከእሳት አደጋው በኋላ ዘመድ አዝማድ የሟቾችን አስክሬን መለየት እቅቷቸው ነበር። አንዳንዶቹ ወደ አመድነት ተቀይረው ነበር።

እንደ ኦማባዳ ነዋሪዎች ከሆነ ከዚህ አደጋ ለታሪክ ነጋሪነት አንድ ሰው ብቻ ተርፏል። ይህም በድቅድቅ ጨለማ ብርሃን ፍለጋ ላይተር የለኮሰው ልጅ ታላቅ ወንድም ነው።

ይህ ሰው ወደ ፋብሪካው ዋና በር ማፈግፈጉ ሕይወቱን እንዳተረፈለት ይገልጻል። ከሞት ያመለጠው ሰው በሱዳን የተከሰተው ግጭት የሰው ሕይወትን እንዲህ ርካሽ ማድረጉ እጅግ ያሳዝናል ይላል።