ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሊቢያ የጎርፍ አደጋ ወደ 20 ሺህ ሰዎች ሞተው ሊሆን እንደሚችል ተገለጸ
በሊቢያ ደርና ከተማ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ወደ 20 ሺህ ሰዎች ሞተው ሊሆን እንደሚችል ተገለጸ።
የሊቢያ ምሥራቃዊ ክፍል አስተዳዳሪ ሂሻም ቺክዋት ጎርፉ ወደ ባሕር በርካታ ሬሳዎችን እያመጣ እየጣለ ነው ብለዋል።
የአደጋው ስፋትና የረድኤት አቅርቦቱ ባለመመጣጠኑ አስክሬን በተገቢው ሁኔታ መቅበር እንኳ አልተቻለም። በርካታ የጅምላ ቀብሮችን ለመፈጸም ተገደዋል።
ሱናሚን የመሰለ ጎርፍ የተከሰተው አውሎ ንፋስን ተከትሎ የግድብ ዉሃ ጥሶ ደርና ከተማን በማጥለቅለቁ ነው።
ነፍስ አድን ሠራተኞች ከፈራረሱ ሕንጻዎች ውስጥ ሕይወት ለማትረፍ ቁፋሮ ላይ ናቸው።
የሊቢያ ባለሥልጣናት 10ሺህ ሰዎች ደብዛቸው ጠፍቷል፤ ከ30ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል ብለዋል።
ነጂብ ታህሮኒ የተባለ በደርና የሚገኝ ሐኪም እሱና ጓደኞቹ በርካታ ቤተሰቦቻቸውን በጎርፉ ማጣታቸውን ተናግሯል። ሆስፒታሉም በሬሳ መሞላቱንም ገልጧል።
“ሁኔታውን የሚረዳ የእርዳታ ሰጪ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ። እስትንፋስ ከፍርስራሽ አነፍንፎ የሚጠቁም የሰለጠነ ዉሻ ያለው የእርዳታ ሰጪ ቡድን ያስፈልጋል፣ የሚሰራውን የሚያውቅ ማለቴ ነው” ብሏል።
ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን የአስቸኳ ጊዜ እርዳታ ሰጪ ሐሙስ ደርና ይደርሳል፤ ሁኔታውን ይገመግማል ብሏል።
ደርና ከተማ አሁን ጎዳናዎቿ በጭቃና በቤት ፍርስራሽ ተሞልተዋል።
አንዳንድ ሰፈሮች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ደብዛቸው ጠፍተዋል።
“ሙሉ የመኖርያ ሰፈር ሙልጭ ብሎ ሲወድም፤ ሲጠፋ አስበው’ ሲል ሱናሚው ያደረሰውን ጉዳት የገለጸው ደግሞ ቺኩዋት የተባለ ሊቢያዊ ነው።
ጣሃ ሙፍታህ የተባለ ሊቢያዊ የፎቶ ጋዜጠኛ ግድቡን ጥሶ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል ባለሙያዎቹ ሲያሳስቡ የነበረው ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ እንደነበረ አስታውሶ፣ ነገር ግን ማንም ጆሮ ሊሰጣቸው አልቻለም ብሏል።
ለቢቢሲ 'ኒውስ አወር' መርሐ ግብር አስተያየቱን የሰጠው ጣሃ የግድቡ ዉሃ ከቁጥጥር ውጭ ሲወጣ የተሰማው ድምጽ፣ ከፍተኛ የአየር ጥቃት ሲደርስ ከሚሰማው ከፍተኛ ድምጽ ጋር ተመሳሳይ ነበር።
“አሁን ዉሃው ጠፍቷል። ሕንጻዎች ፈራርሰዋል። ነዋሪዎቹ ደግሞ ከመሬት በታች ተቀብረዋል” ሲል ነባራዊ ሁኔታውን ለቢቢሲ አስረድቷል።
በጎርፍ ከተወሰዱት ሊቢያዊያን መካከል እውቅ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ይገኙበታል ብሏል፣ የሊቢያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ።
የአራት ሥመ ጥር እግር ኳስ ተጫዋቾችን ስም ዝርዝርም ይፋ አድርጓል።
በነዳጅ ሃብቷ የምትታወቀው ሊቢያ የጋዳፊን መገደል ተከትሎ ላለፉት 13 ዓመታት በፖለቲካ ተረጋግታ አታውቅም።
አሁንም ድረስ ትሪፖሊን መቀመጫው ባደረገ በጊዜያዊ አስተዳደር ሥር ነው የምትገኘው።
በምሥራቅ ሊቢያ ደግሞ ሌላ ኃይል አካባቢውን ያስተዳድራል።