አዲሱ አይፎን 15 በ ‘ታይፕ ሲ’ ቻርጀር ከ70ሺህ ብር ጀምሮ ለገበያ ቀረበ

አፕል አዲሱን ምርቱን ይፋ አድርጓል። የአውሮፓ ሕብረት የአፕል ምርቶች ቻርጅ የሚደረጉበት ቀዳዳ መቀየር አለበት ማለቱን ተከትሎ አዲስ ገመድ ይዞ ብቅ ብሏል።

ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አይፎን 15 ምርቱን ይፋ ሲያደርግ ‘ዩኤስቢ ሲ’ የተባለውን ገመድ ለዓለም ገበያ አቅርቧል።

አፕል፤ አይፎን 15ን ብቻ ሳይሆን አዲስ የአፕል ዋች ምርትም ለገበያ ማቅረቡን ገልጧል።

ነገር ግን የቴክኖሎጂ አዋቂዎች አይፎን በአዲሱ ምርቱ አዲስ ነገር ይዞ ብቅ አለማለቱ ሊጎዳው ይችላል ይላሉ።

አዲሱ አይፎን በሚቀጥለው ሳምንት ለሽያጭ የሚቀርብ ሲሆን አማራጭ ቻርጅ ማድረጊያ ገመድ ይዞ ብቅ ሲሆን ከአውሮፓውያኑ 2012 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ኩባንያው እንደገለጠው ዩኤስቢ ሲ የተባለው ቻርጅ ማድረግ ገመድ ለስልኮችና አይፓዶች ብቻ ሳይሆን እንደ ለባለገመዱ እና ገመድ አልባው ማዳመጫዎች ኤርፖዶችም ይሆናሉ።

የአውሮፓ ሕብረት አፕል ከሌሎች ስልኮች ለየት የሚለውን ቻርጅ ማድረጊያ ቀዳዳ ቀይሮ ተጠቃሚዎች ገንዘብ እንዲቆጥቡ፤ አልፎም የሚጣሉ የቴክኖሎጂ ምርቶችን እንዲቀንሱ ማሳሰቡ ይታወሳል።

ነገር ግን አንዳንዶች ይህ መሆኑ እንደውም ከጥቅም ውጭ ሆነው የሚጣሉ ቻርጅ ማድረጊያ ገመዶች እንዲበርክቱ ያደርጋል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

ይህን ተከትሎ አፕል አዳዲስ ምርቶቹን ማክሰኞ ይፋ ሲያደርግ ተፈጥሮ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ምርቶቹን እየቀነሰ እንደሆነ ገልጧል።

በአይፎን ስልኩ እና አፕል ዋች በተሰኘው የእጅ ሰዓቱ ውስጥ የሚገኙ ቁሶች መልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደሚያደርግም ኩባንያው አስታውቋል።

በአውሮፓውያኑ 2030 ‘ካርበን ኒውትራል’ እሆናለሁ ያለው አፕል በአዳዲሶቹ ምርቶቹ ላይ ምንም ዓይነት የቆዳ ምርት እንደማይጠቀም ይፋ አድርጓል።

ካርበን ኒውትራል ነን የሚሉ ድርጅቶች ወደ አየር ንብረት የሚለቁትን ካርበን ዳይኦክሳይድ ለማመጣጠን የሚሞክሩ ናቸው።

የአፕል አለቃ ቲም ኩክ አዲሱ ምርታችን “በጣም ምርጡና ብዙ ተግባራት ያዘለ ድንቅ ምርታችን ነው” ብለዋል።

አይፎን 15 እና 15 ፕላስ ምርቶች ስክሪናቸው የጠራ፣ ካሜራቸው የተሻሻለ ሲሆኑ አይፎን 15 ፕሮ እና ፕሮ ማክስ ደግሞ ከታይታኒየም የተሠራ ገላ ያላቸው በመሆናቸው ጥንካሬያቸው ከፍ ያለ ነው።

ፕሮ እና ፕሮ ማክስ ‘አክሽን በተን’ የተባለ አዲስ ቴክኖሎጂ ይዘዋል። ለወትሮው ስልክ ‘ሳይለንት’ ለማድረግ የሚረዳው ቴክኖሎጂ አሁን የተለያዩ ተግባራትን እንዲፈፅም ሆኖ ተሠርቷል።

ነገር ግን የቴክኖሎጂ አዋቂዎች አዲሶቹ የአፕል ምርቶች በጣም ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ አዲስ ነገር ባለመያዛቸው ተጠቃሚዎች ረብጣ ዶላር አውጥተው ይገዛሉ ወይ ብለው እንዲጠይቁ ሆነዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም አይፎን 15 ፕሮ ዋጋው 999 ፓውንድ ነው።

ባለፈው ሳምንት የቻይና መንግሥት ባለሥልጣናት የአፕል ምርቶችን እንዳይጠቀሙ መከልከሉን ተከትሎ የአፕል የገበያ ዋጋ ወርዶ ነበር።

የቻይናው ሁዋዌ አዲስ ስማርት ስልኮችን ለገበያ ማቅረቡ ደግሞ ለገበያ ዋጋው መውረድ ሌላ ምክንያት ሆኗል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የስማርት ስልኮች ገበያ ቀዝቀዝ ቢልም አፕል ከሌሎቹ ኩባንያዎች ሲነፃፀር ብዙም አልተጎዳም ይላል ካውንተርፖይንት ሪሰርች የተሰኘው ድርጅት ያወጣው መረጃ።