ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
8.7 ቶን የሚመዝን ሩዝ በአንድ ብረት ድስት በማብሰል የዓለም ክብረ ወሰን የያዘችው ሼፍ
ሒልዳ ባሲ ታዋቂ ሼፍ ናት። ሁለት ጊዜ የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ (ጊነስ ወርልድ ሪከርድ) ክብረ ወሰንን አሸንፋለች።
ናይጄሪያዊቷ ምግብ አብሳይ "ስኬታማ የሆንኩት ገንዘብ ስለምወድና በሕይወት ጥሩ ነገሮች ስለሚማርኩኝ ነው" ትላለች።
የ30 ዓመቷ ሼፍ ዝነኛነቷን በደስታና በፀጋ ነው የምትቀበለው። በአገሯ የተከበረች ምግብ አብሳይ ናት።
ለቤተሰቦቿና ለፍቅር አጋሯ የምታሳየው ማንነትና እንደ ሼፍ ለሕዝብ የምታሳየው ማንነት እንደሚለያይ ትናገራለች።
"ከማንኛውም ነገር ቀድሞ ነጋዴ ነኝ። ምንም እያደረግኩ ቢሆን ቅድሚያ የምሠጠው ለሥራዬ ነው" ትላለች።
'My Food by Hilda' የሚለው የኢንስታግራም ገጿ ከሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሉት።
በሌጎስ ታዋቂ ሬስቶራንት ያላት ሲሆን በራሷ ስም በከፈተችው የኢንስታግራም ገጽ 3.2 ሚሊዮን ተከታዮች አፍርታለች።
የምግብ አበሳሰል የምታስተምረው ሒልዳ "ሰዎችን ለፈጠራ ማነሳሳት ደስ ይላል። ብዙዎች ከኔ ምክርና መልስ መፈለጋቸው ግን ትንሽ ጫና ያሳድርብኛል። ሆኖም ከአቅሜ በላይ እንዲሆን አልፈቅድም። ከግቤ እንዲያሰናክለኝም አላደርግም" ትላለች።
በደቡባዊ ናይጄሪያ ካላባር ነው የተወለደችው። ከእናቷ እንዲሁም ከወንድምና እህቷ ጋር ወደ መዲናዋ አቡጃ ካቀናች በኋላ፤ ገና ወጣት እያለች ነው ታዋቂ መሆን የጀመረችው።
እናቷ በአቡጃ ከመከላከያ ሚኒስቴር ፊትለፊት ምግብ ቤት ነበራቸው። ከትምህርት ቤት ስትወጣ እናቷን ታግዝ ነበር።
"ሙሉ የምግብር ዝርዝሩን በቃሌ ስለምሸመድድ ጉርሻ ይሰጠኝ ነበር። በጣም ተጫዋችም ነበርኩ። ያለንን ምግብ እየዘረዘርኩ አስመርጥ ነበር" ስትል ታስታውሳለች።
እአአ በ2023 ነበር ሒልዳ ወደ ዝና ማማ መውጣት የጀመረችው። ለአራት ቀናት (93 ሰዓታት እና 11 ደቂቃዎች) ሳታቋርጥ ምግብ በማብሰል የዓለም ክብረ ወሰን ይዛለች።
በሒልዳ ተይዞ የነበረው ክብረ ወሰን በሌላ ሼፍ ቢሰበርም ዝናዋ በዓለም ናኝቷል። የፖለቲከኞችና ታዋቂ ሰዎችን ትኩረትም መሳብ ችላለች።
8.7 ቶን የሚመዝን ጆሎፍ ሩዝ በመሥራት ያሳለፍነው ወር አዲስ ክብረ ወሰን ይዛለች። ጆሎፍ ሩዝ (jollof rice) በምዕራብ አፍሪካ ታዋቂ ምግብ ነው።
ሒልዳ ምግቡን ያበሰለችው በአንድ ትልቅ ብረት ድስት ውስጥ ነው።
ሒልዳ እንዴት ገጽታዋን መገንባት እንዳለበት ወጥና ነው የምትሠራው። ክብረ ወሰን የያዘችበትን የሩዝ ምግብ ለማብሰል የወጠነችው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር።
"ለረዥም ሰዓት በማብሰል ክብረ ወሰን ለመያዝ ሳስብ እንዴት ነው ገጽታዬን የሚገነባው? የሚለውን አስቤበታለሁ" ትላለች።
ሒልዳ ለሙያዋ የተሰጠች ብትሆንም ሼፍ የሆነችው በአንድ ጀንበር አይደለም።
ምኞቷ ጠበቃ መሆን ነበር። ከዚያም ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለመማር አሰበች። በስተመጨረሻ ሶሽዮሎጂ አጠናች።
ተዋናይትና የቴሌቭዥን መሰናዶ አቅራቢ መሆንም ትፈልግ ነበር። "በጣም አዝናኝ ነው። በዛ ላይ ዝነኛ ያደርጋል" ትላለች።
በልጅነቷ እናቷ ምግብ እያበሰሉ እንዴት ሕይወታቸውን እንደለወጡ ማየቷ ሼፍ እንድትሆን ገፋፍቷታል።
የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳለች ለተለያዩ ተቋማትና የምሽት ክበቦች ማብሰል ጀመረች። የነፍስ ጥሪዋን እንዳገኘችም አወቀች።
ከወንድሟ ጋር ምግብ የማመላለስ ሥራ ጀምረው ነበር። በቴሌቭዥን ላይ ምግብ አሠራር የማስተማር ዕድልም አግኝታለች።
'Dine on a Budget' የተባለ የራሷን መሰናዶ ጀምራለች። ታዋቂ ሰዎችን ለቃለ ምልልስ በመጋበዝ በርካሽ ዋጋ ሦስት ዓይነት ምግብ ስትሠራላቸው የሚያሳይ መርሃ ግብር ነው።
ሩዝ የሠራችበት ውድድር ላይ የጋና ሼፍም የተሳተፈ ሲሆን በውድድሩ 5,000 አግኝታለች።
ሒልዳ ለስኬቷ ፈጣሪንም ታመሰግናለች።
"ፈጣሪ እንድናደርግ የምንፈልገውን ነገር ስናከናውን ያሳውቀናል። መልስ ይሰጠናል" ትላለች።
ሒልዳ ስኬታማ ሼፍ ብትሆንም በማኅበረሰቡ ባለው 'ፆታዊ ሚና' ምክንያት ጫና እንደሚደርስባት አልሸሸገችም።
"በየቀኑ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መቼ ነው የምታገቢው? አላገባሽም? እያሉ ይጠይቁኛል። በኛ አገር ይሄ የተለመደ ነው። ያላገባች ሴት ስኬቷ ሙሉ ነው ተብሎ አይታሰብም። እኔ ባመጣሁት ለውጥ ደስተኛ ነኝ። እኔን የመሰሉ ያላገቡና ድንቅ የሆኑ ስኬታማ ሴቶች አሉ።"
ሒልዳ አክላም "ማግባት እፈልጋለሁ። ፍቅር የምወድ ሴት ነኝ። ግን ራሴ ላይ ጫና አላሳድርም። የምወደውና አብሬው ስሆን ደስተኛ የሚያደርገኝ ሰው ካገኘሁ አገባዋለሁ። ማኅበረሰቡ አሁን እንዳገባ ስለፈለገ ብቻ ግን ትዳር አልመሠርትም" ትላለች።
ሕልሟ እስከወዲያኛው ድረስ አብሯት የሚዘልቅ ስም መገንባት ነው።
"የራሴ የሆነ የስኬት ታሪክ መገንባት እፈልጋለሁ። '100 ዓመታት አስቆጥረዋል' እንደሚባሉት ተቋማት ዓይነት ስሜን መትከል እሻለሁ።"
በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በደቡብ አፍሪካና ሌሎችም አገራት ሬስቶራንቶች ከፍታ የናይጄሪያን ምግብ ታዋዊ ማድረግን ታልማለች።
ጆሎፍ ሩዝ በዓለም ዝነኛ ቢሆንም ሌሎም እምብዛም ያልታወቁ የአገሯን ምግቦች ማስተዋወቅ እንደምትፈልግ ትናገራለች።
"እኔ የሠራሁት የኮኮናት ሩዝ አለ። በዓለም እንዲታወቅ ነው የምፈልገው። በሁሉም ሬስቶራንቶች የምግብ ዝርዝር ላይ እንዲገኝ እሻለሁ።"