ዘሪሁን አስፋው፡ “ማስተማርን እንደ ፀጋ የቆጠሩ፣ ማስተማርን እንደ አባትነት የተቀበሉ”

ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው የካቲት 27/2015 ዓ.ም. ሌሊት በድንገት ባደረባቸው ሕመም ማረፋቸውን የቅርብ ጓደኞቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ገለፁ።

ፕሮፌሰር ዘሪሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከ40 ዓመት በላይ በሥነጽሑፍ መምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በተለያዩ ሥነ ጽሑፋዊ ጉዳዮች ላይ ጥናት እና ምርምሮችን በመስራት እንዲሁም በሃያሲነታቸውም ይታወቃሉ።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን እስከ ትናንት ሰኞ ለሊት ድረስ በቤታቸው በሥራ ላይ የነበሩ ሲሆን፣ ድንገት ታመው ለሕልፈት መዳረጋቸውን ጓደኞቻች እና ቤተሰቦቻቸው ይገልጻሉ።

ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ አንደሚያውቋቸው የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ደረጀ ገብሬ፣ ፕሮፌሰር ዘሪሁን “በሥራቸው የተመሰገኑ” ናቸው ብለዋል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን ከትምህርቱ ዘርፍ በተጨማሪ ከፖፑሌየሽን ሚዲያ ሴንተር ጋር በመሆን የተለያዩ የሥነ ሕዝብ ጥናቶችን መሥራታቸውን የሚናገሩት ደረጀ ገብሬ፣ ወጣት ደራሲያን እና ተመራማሪዎችን በማማከር እና በመደገፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ደረጀ፣ ተ/ፕሮፌሰር ዘሪሁን የሥነጽሁፍ መሠረታውያን የተባለውን ታዋቂ መጽሐፋቸውን ጨምሮ አራት መጽሐፍትን ለህትመት ማብቃታቸውን ተናግረዋል።

ሌላው ቢቢሲ ያነጋገረው እና ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ እንዳስተማሩት የሚገልጸው አንዱዓለም አባተ (ዶ/ር) ተ/ፕሮፌሰር ዘሪሁን “በአስተማሪነቱ ለራሱ፣ ለትምህርት ክፍሉ፣ በትምህርት ክፍሉ ውስጥ ላሉ እና ተማሪው ለሆኑ ሁሉ አርዓያ የሆነ” ሲል ይገልጻቸዋል።

ተ/ፕሮፌሰር ዘሪሁን በዩኒቨርስቲው ውስጥ በመምህርነት ባገለገሉባቸው አራት አስርት ዓመታት ሁሉ በሰዓት አክባሪነታቸው እንደሚታወቁ የሚያነሳው አንዱዓለም፣ “ማስተማርን እንደ ፀጋ የቆጠሩ፣ ማስተማርን እንደ አባትነት የተቀበሉ” እንደነበሩ ይናገራል።

ተ/ፕሮፌሰር ዘሪሁን በማስተማር ሥራቸው ብቻ ሳይሆን በጥናት እና ምርምር ሥራዎች ላይ ባስቀመጡት የጊዜ ገደብ ማከናወንን የሚመርጡ “ሰው ለመርዳት ቀዳሚ የሆኑ” መሆናቸውን ያክላል።

“የኢትዮጵያን ሥነጽሑፍ የሰነዱ” መሆናቸውን የሚገልፀው አንዱዓለም (ዶ/ር) ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስገራሚ የማስታወስ ችሎታ እንደነበራቸውም ያስረዳል።

“በማስተርስ እና በፒኤችዲ ያስተማራቸውን ተማሪዎች ሳይቀር በምን ጉዳይ ጥናታቸውን እንደሰሩ፣ ምን ክፍተት እንደነበረባቸው እና ጥናታቸው፣ ምን ጠንካራ ጎን እንደነበረው ሰንደው የያዙ ነበሩ” ይላል።

አንዱዓለም ብዙ ጊዜ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ የጥናት ርዕስ መደራረብ አንደሚያጋጥም፣ በአንዱ ዩኒቨርስቲ የተጠናውን ደብቀው አምጥተው ሌላ ዩኒቨርስቲ የሚያጠኑ መኖራቸውን አስታውሶ “ማ ምን አጠና የሚለው ዝርዝር መረጃ በእኛ የትምህርት ክፍል ያለው እርሱ ጋር ነው” ይላል።

“ከመጀመሪያው አንስቶ እስካሁን በዲግሪ የተጠኑ፣ በማስተርስ፣ በፒኤችዲ ደረጃ የተጠኑ የዲፓርትመንቱ መረጃ አለው” በማለት በቅርቡ ያሳተሙትም መጽሐፍ መኖሩን ይናገራል።

አንዱዓለም (ዶ/ር) እንዲሁም ደረጀ ገብሬ እንደገለጹት ተ/ፕሮፌሰር ዘሪሁን ለህትመት ዝግጁ የሆኑ “ሁለት ወይም ሦስት ሥራዎች” እንዳሏቸውም ገልፀዋል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን በማስተማር፣ በመጻፍ እና በምርምር ካበረከቱት አስተዋጽኦ በተጨማሪ በርካታ የሌሎች ሰዎች ሥራዎችን አርትኦት በማድረግም ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ባለ ትዳር እና የልጆች አባት ነበሩ።