ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የ2030 የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ በ3 አህጉራት ውስጥ በሚገኙ 6 አገራት ሊካሄድ ነው
በአውሮፓውያኑ 2030 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ በሦስት የተለያዩ አህጉራት ውስጥ በሚገኙ ስድስት አገራት እንደሚካሄድ የዓለም እግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ ፊፋ አስታወቀ።
በዚህም ስፔን፣ ፖርቱጋል እና ሞሮኮ፤ የመክፈቻውን ሦስት ግጥሚያዎችን ከሚያስተናግዱት ከኡራጓይ፣ ከአርጀንቲና እና ከፓራጓይ ጋር በመጣመር የዓለም ዋንጫ ይካሄድባቸዋል።
የመክፈቻዎቹ ጨዋታዎች በደቡብ አሜሪካ አገራት ውስጥ እንዲካሄድ የተፈለገው፣ የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያው ጨዋታ የተካሄደበትን አንድ መቶኛ ዓመት ለመዘከር ነው።
ይህ ውሳኔ በሚቀጥለው የአውሮፓውያን ዓመት በሚካሄደው የፊፋ ጉባኤ ላይ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ውሳኔውን ተከትሎ የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ “የተከፋፈለውን ዓለም፣ ፊፋ እና እግር ኳስ አንድ ያደርጉታል” ብለዋል።
“የዓለም እግር ኳስ ማኅበራት የተወከሉበት የፊፋ ምክር ቤት፣ በ1930 (እአአ) ኡራጓይ ውስጥ የተጀመረውን የዓለም ዋንጫ ውድድር አንድ መቶኛ ዓመት ተገቢ በሆነ ሁኔታ እንዲከበር በሙሉ ድምጽ ተስማምቷል።
“ስለዚህም በ2030 በሦስት አህጉራት በአፍሪካ፣ በአውሮፓ እና በደቡብ አሜሪካ ውስጥ በሚገኙት በአርጀንቲና፣ በሞሮኮ፣ በፓራጓይ፣ በፖርቱጋል፣ በስፔን እና በኡራጓይ ስድስት አገራት የዓለም ዋንጫ በተለየ ሁኔታ በድምቀት ይስተናገዳል” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
በተጨማሪም በ2034 (እአአ) ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅነት በእስያ እና በኦሺኒያ ክፍለ አህጉራት ከሚገኙ የእግር ኳስ ማኅበራት ብቻ ጥያቄዎችን እንደሚቀበል ፊፋ አስታውቋል።
ሳዑዲ አረቢያ በ2034 የሚካሄደውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን ለማስተናገድ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥያቄ ታቀርባለች ተብሎ ይጠበቃል።
የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ ጨዋታን በ1930 (እአአ) ያስተናገደችው የኡራጓይ ዋና ከተማ ሞንቴቪዲዮ በቀጣይ 2030 የሚካሄደውን የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታን የምታስተናግድ ሲሆን፣ በተከታይነት በአርጀንቲና እና በፓራጓይ ቀጣይ የመክፈቻ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከዚያም የቀሩት 48 ጨዋታዎች በሰሜን አፍሪካዋ ሞሮኮ እና በአውሮፓውያኑ ስፔን እና ፖርቱጋል ይደረጋሉ።
ይህ የቀረበው የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ ዕቅድ የሚጸድቅ ከሆነ ሞሮኮ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ ከአፍሪካ የዓለም ዋንጫን በማስተናገድ ሁለተኛዋ አገር ትሆናለች።
ስፔን በ1982 (እአአ) የዓለም ዋንጫን የማስተናገድ ዕድል አግኝታ የነበረ ሲሆን፣ ፖርቱጋል ግን ከዚህ ቀደም ውድድሩ ተካሂዶባት አያውቅም።
የ2030 የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅ አገራት ሆነው የተመረጡት ኡራጓይ፣ አርጀንቲና፣ ፓራጓይ፣ ስፔን፣ ፖርቱጋል እና ሞሮኮ ከዚህ በፊት እንደሚደረገው ሁሉ ለውድድሩ ያለማጣሪያ የሚያልፉ ይሆናል።