በጀርመን ሌቦች ወደ ባንክ ሰርስረው በመግባት 30 ሚሊዮን ዶላር ዘረፉ

ፖሊስ ዘራፊዎቹ ወደ ባንኩ ለመግባት የመኪና ማቆሚያ ጋራዥ ተጠቅመዋል ብሏል

የፎቶው ባለመብት, Gelsenkirchen Police

የምስሉ መግለጫ, ፖሊስ ዘራፊዎቹ ወደ ባንኩ ለመግባት የመኪና ማቆሚያ ጋራዥ ተጠቅመዋል ብሏል

በምዕራብ ጀርመን ዘራፊዎች የባንኩ የገንዘብ እና ውድ ዕቃዎች ካዝና ወደሚገኝበት ክፍል ሰርስረው በመግባት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ጥሬ ገንዘብ እና ውድ ዕቃዎችን መዝረፋቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

ዘራፊዎች ወደ ባንኩ ለመግባት እና በካዝና የተቀመጠን 35 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ጥሬ ገንዘብና ውድ ዕቃዎችን ለመዝረፍ ቁፋሮ ማካሄዳቸው ተገልጿል።

በዘረፋው ከ2,700 በላይ የባንኩ ደንበኞች መጎዳታቸውን ፖሊስ እና ዝርፊያው የተፈጸመበት ስፖርካስ ባንክ አስታውቀዋል።

የፖሊስ ቃል አቀባይ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል የስርቆቱን ሂደት የባንክ ዝርፊያ ሲፈጸም ከሚታይበት የሆሊውድ ፊልም "ኦሽንስ ኢለቨን" ጋር አነጻጽረው የገለፁት ሲሆን "በጣም ሙያዊ በሆነ መልኩ የተፈፀመ ነው" ብለዋል።

በጌልሰንኪርቼን ከተማ በሚገኘው የስፓርካስ ባንክ ዝርፊያ ወቅት ዘራፊዎቹ ገንዘብ፣ ወርቅና ጌጣጌጥ የያዙ ከ3,000 በላይ ሳጥኖችን ሰብረዋል።

የጌልሰንኪርቼን ፖሊስ ወንጀሉ መፈጸሙን የተረዳው ሰኞ ጠዋት የእሳት አደጋ ማስጠንቀቂያው ደወል መጮሁን ተከትሎ ነው።

እስካሁን ድረስ ወንጀሉን ከፈጸሙት መካከል አንድም ሰው አለመያዙን ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።

ፖሊስ ሌቦቹ በቡየር ዲስትሪክት በሚገኘው ኒየንሆፍስትራሴ ላይ የሚገኘውን ሕንፃ ለመዝረፍ "እንቅስቃሴ አልባ የሆነውን የገና ዕለት" ተጠቅመዋል ብሏል።

የመጀመሪያ ምርመራ እንደሚያሳየው ከሆነ ወደ ባንኩ መግባት ከቻሉ በኋላ በአቅራቢያው ባለ የመኪና ማቆሚያ ጋራዥ በኩል አምልጠዋል።

የዓይን እማኞች ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ሌሊት ጋራዡ ውስጥ ትላልቅ ከረጢቶችን የያዙ በርካታ ወንዶችን እንዳዩ ሪፖርት አድርገዋል።

ፖሊስ ሰኞ ጠዋት በዴ-ላ-ቼቫሌሪ-ስትራሴ ጥቁር ኦዲ አርኤስ 6 መኪና ከጋራዡ ሲወጣ በደህነንት ካሜራው ላይ እንደሚታይ ተናግሯል።

ሰኞ ማለዳ የእሳት አደጋ ማንቂያ ደወሉ ተሰምቶ ፖሊስ ወደስፍራው ሲደርስ በባንኩ የገንዘብ ማስቀመጫ ክፍል ውስጥ የተቆፈረ ጉድጓድ በማግኘቱ ከእሳት አደጋ ሠራተኞች ጋር በመሆን ሕንጻው ውስጥ አሰሳ አድርገዋል።

በዘረፈው ጉዳት የደረሰባቸው የባንክ ደንበኞች ማክሰኞ ዕለት የስፓርካስ ባንክን ለማነጋገር በባንኩ ዙሪያ ተሰባስበው ነበር።

አንድ የባንኩ ደንበኛ ዌልት ለተሰኘ የመገናኛ ብዙኃን ገንዘቡን የቆጠበው ለመጦሪያው መሆኑን ገልጾ "ትናንት ማታ መተኛት አልቻልኩም። ምንም ዓይነት መረጃ እያገኘን አይደለም" ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል።

በባንኩ ድረ ገጽ ላይ የተቀመጠ መልዕክት ቅርንጫፉ ማክሰኞ ዕለት ዝርፊያውን ተከትሎ ዝግ እንደሚሆን ይጠቁማል።

ስፓርካስ እንዳለው ከሆነ 95 በመቶ የሚሆኑ የደንበኞች የቁጠባ ሳጥኖች በዘራፊዎቹ ተሰብረዋል፤ ስለዚህ በዘረፋ የመጠቃት ዕድላቸው "በጣም ከፍተኛ" ነው።

የእያንዳንዱ የቁጠባ ሳጥን እስከ 10,300 ዩሮ የሚደርስ ዋስትና ያለው ሲሆን ደንበኞች በግላቸው ተጨማሪ የመድን ዋስትና ገብተው ከሆነ እንዲያረጋግጡ ጠይቋል።