4.8 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጣ የወርቅ ሽንት መፀዳጃ የሰረቁት ወንበዴዎች ጥፋተኛ ተባሉ

የወርቅ መፀዳጃ

የፎቶው ባለመብት, Blenheim Palace

ዋጋው 4.8 ሚሊዮን ፓውንድ የሆነ የወርቅ መፀዳጃ ከአንድ ኤግዚቢሽን ላይ ሰርቀዋል የተባሉ የወንበዴ ቡድን አባላት ጥፋተኛ ሆነው ተገኙ።

ዘራፊዎቹ ይህን ያደረጉት በአውሮፓውያኑ 2019 ብሌንሀይም ፓላስ በተባለው ቤተ-መንግሥት ነው።

መፀዳጃው በደማቅ ድግስ ከተመረቀ በኋላ ወደ ውስጥ ገብተው ነቅለው ይዘውት እንደጠፉ የፍርድ ቤት መዛግብት ያመለክታሉ።

ማይክል ጆንስ ዝርፊያውን በማቀናጀት ጥፋተኛ ሲባል ፍሬድ ዶ ደግሞ ወርቁን ለመሸጥ በመመሳጠር ጥፋተኛ ነው ተብሏል። ቦራ የተባለው ተከሳሽ ወርቁን በማሻሻጥ በሚል ከቀረረበት ክስ ነፃ መሆኑን ተረጋግጧል።

የወንበዴ ቡድን መሪ የሆነው ጄምስ ሺን ማረሚያ ቤት የሚገኝ ቢሆን ባለፉት ዓመታት እሱ ባቀነባበረው ዝርፊያ 5 ሚሊዮን ፓውንድ መሰረቁ ተነግሯል።

ምንም እንኳ አምስት ሰዎች ሽንት ቤቱን ተሸክመው ሲወጡ በደኅንነት ካሜራ ቢታዩም በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሺን እና ጆንስ ናቸው።

አሜሪካ የተባለ ስም የተሰጠው የጥበብ ሥራ በቀናት ውስጥ ተሰባብሮ ወርቁ መሸጡን ፍርድ ቤቱ ሰምቷል። ከተሰረቀው ወርቅ አንዱም ሊገኝ እንዳልቻለ ተነግሯል።

የኦክስፎርድ ሰው የሆነው ሺን ባለፈው ዓመት ፖሊስ የዲኤንኤ ማስረጃ ካመጣበት በኋላ ጥፋተኛ መሆኑን ሲያምን በሌሎችም ወንጀሎች ጥፋተኛ እንደሆነ ተደርሶበታል።

የ40 ዓመቱ ግለሰብ ከዚህ ቀደም በማጭበርበር፣ በስርቆት እና የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት ተፈርዶበት ያውቃል። የወርቅ መጸዳጃውን ለመዝረፍ አቅዷል በሚል ተጠርጥሮ ከስርቆቱ ከአራት ሳምንታት በኋላ በቁጥጥር ሥር ቢውልም በዋስ መለቀቁ ይታወሳል።

ከዚህ ዝርፊያውም በኋላ ከእንግሊዙ ብሔራዊ የፈረስ ውድድር ሙዚየም 400 ሺህ ፓውንድ የሚያወጡ የወርቅ እና የብር ዋንጫዎችን መስረቁ ታውቋል።

ዘራፊዎች በዩኔስኮ የዓለም ቅርሶች ከተመዘገበው ብሌንሀይም ቤተ-መንግሥት የወርቅ መፀዳጃውን እንዴት አድርገው እንደሰረቁት በዝርዝር ለፍርድ ቤቱ ይፋ ተደርጓል።

ወንጀለኞቹ የወርቅ ሽንት ቤቱ በይፋ ተመርቆ ለዕይታ ይፋ በሆነበት ምሽት ነው በተሰረቀ መኪና አጥር ጥሰው ገብተው መስታወት በመሰባበር ዘርፈው የወጡት።

ዘራፊዎቹ 98 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን መፀዳጃ አጥር ጥሰው ገብተው ለመስረቅ የወሰደባቸው ጊዜ ሶስት ደቂቃ ነው። ፖሊስ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ወደ ሥፍራው ቢደርስም ዘራፊዎቹን ማግኘት አልቻለም።

ሰዎቹ እንዴት አድርገው ወርቁን ሰባብረው እንደሸጡት ባይታወቅም በተሰረቀ ከሁለት ቀናት በኋላ አንድ ኪሎ ወርቅ በ25 ሺህ ፓውንድ መሸጣቸው ተሰምቷል።

ጥፋተኛ የተባሉት ግለሰቦች ፍርድ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ይዟል።