በ36 ሰከንዶች ውስጥ ከሥዕል ጋለሪ የተሰረቀው ከ360 ሺህ ዶላር በላይ የሚያወጣው ሥዕል

በ36 ሰከንዶች የተሰረቀው ሥዕል

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, በ36 ሰከንዶች የተሰረቀው ሥዕል በፖሊስ ከተገኘ በኋላ

በማዕከላዊ ለንደን ከሚገኝ የሥዕል ጋለሪ ውስጥ ከ360 ሺህ ዶላር በላይ ያወጣል የተባለው የባንክሲ የህትመት ሥዕል እንዴት ሊሰረቅ አንደቻለ ሲያነጋግር ከርሟል።

የዚህ ሥዕል ስርቆት ውስብስብ ሁኔታን የፈጠረ ሲሆን፣ ሁለት ግለሰቦች በድርጊቱ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት እየተመላለሰ ጉዳያቸው እየተሰማ ነው።

ስርቆቱ ከተፈጸመ ከአንድ ዓመት በኋላ አሁን ሥዕሉን በመስረቅ የተጠረጠረው ግለሰብ በመቶ ሺህ ዶላሮች የሚያወጣውን ሥዕል እንዴት እንደሰረቀ ከደኅንነት ካሜራ ላይ ከተገኘ ምሥል ለፍርድ ቤት ማስረጃ ቀርቧል።

ከመጀመሪያው አንስቶ የ54 ዓመቱ ጄምስ ላቭ እና ላሪ ፍራሰር የተባለ የ48 ዓመት ግለሰቦች በሥዕሉ ስርቆት ተጠያቂ ሆነው እራሳቸውን እየተከላከሉ ነው።

ስርቆቱን የፈጸመው ግለሰብ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር መጀመሪያ ምሽት ላይ ሥዕሉ የነበረበትን የግሮቭ የሥዕል ጋለሪን የበር መስታወት ሰበሮ በመግባት ውስን ህትመት የነበረውን ውድ ሥዕል ከ30 ሰከንድ ብዙም ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይዞ ለመውጣት ችሏል።

የሥዕል ጋላሪው ባለቤት ጄምስ ራያን ባወጣው መግለጫ ላይ በደኅንነት ካሜራ በተቀረጸው ቪዲዮ ላይ ፊቱን በጭንብል የሸፈነ አንድ ግለሰብ ወደ ጋለሪው ሰብሮ በመግባት ሥዕሉን ይዞ ለመውጣት የፈጀበት ጊዜ 36 ሰከንዶች ብቻ መሆኑን አመልክቷል።

ዐቃቢያነ ሕጎች ጄምስ ላቭ የተባለው ግለሰብ ተመሳሳይ የሥዕል ሥራዎችን የሰበሰበ መሆኑን በመጥቀስ፣ ስርቆቱ በተፈጸመበት ዕለት ጠዋት እና ከተሰረቀ በኋላም ወደ ጋለሪው መጥቶ ነበር ብለዋል።

በተጨማሪም ግለሰቡ ሥዕሉን ከሰረቀው ፍራሰር ጋር ወንጀሉ በተፈጸመበት ዕለት በተደጋጋሚ ሲገናኙ ነበር ተብሏል።

የተሰረቀው ሥዕል ዓይነት አንዳንዶቹ የተፈረመባቸው አስራ ሦስት ኦሪጂናል የባንክሲ የጥበብ ሥራዎች ቅጂዎች ተመርጠው በሥዕል ጋለሪው ውስጥ ለዕይታ እንዲቀርቡ ተዘጋጅተው እንደነበር ለፍርድ ቤቱ ተገልጿል።

የጋለሪው ባለቤት እንደተናገሩት የተሰረቀው የሥዕል ሥራ በውስን ቁጥር መጀመሪያ የታተመው በአውሮፓውያኑ 2004 ነበር።

ጨምረውም የተሰረቀው ከእነዚያ አንዱ ሲሆን "ሥዕሉ ከ360 ሺህ ዶላር በላይ የሚያወጣ እና ንብረትነቱም የአንድ በግሉ ሥዕሎችን የሚሰበሰብ ግለሰብ" መሆኑን ተናግረዋል።

ሥዕሉን ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ በ36 ሰከንዶች የሰረቀው ግለሰብ ሥዕሉን በአቅራቢያ ወደሚገኝ ቤት ወስዶ እዚያው ማስቀመጡን ለፍርድ ቤት ተገልጿል።

በዕለቱ ሥዕሉ ተሰርቆ የተወሰደበት ቤት የምሽት ጥበቃ ተረኛ የነበረው ግለሰብ፣ ሁለት ሰዎች ገፍትረውት ወደ ውስጥ ሲገቡ በከባድ ድንጋጤ ውስጥ እንደነበር አስረድቷል።

ከዚያም "የአሻንጉሊት" የሚመስል ሥዕል ሽንት ቤቱ ውስጥ ተቀምጦ ማየቱን ቃሉን ሰጥቷል።

ኋላ ላይም አንድ ነጭ እና አንድ ጥቁር ግለሰቦች በሩን ሲታገሉ አይቶ ሲከፍትላቸው በጥድፊያ ገፍትረውት በመግባት ወደ ሽንት ቤቱ በማምራት ሥዕሉን ይዘውት መሄዳቸውን አስረድቷል።

ነገር ግን ሥዕሉን በመስረቅ የተጠረጠሩት ሁለቱ ግለሰቦች ቤት ሰብረው በመግባት ዝርፊያ አለመፈጸማቸውን ክደው የተከራከሩ ሲሆን፣ የፍርድ ሂደቱ ይቀጥላል።