በአንዲት እናት ስህተት ዝነኛ የሆነችው ከተማ

በዕድሜ ብዛት አርጅቶ የነበረው ሥዕልና ለማደስ በተደረገ ሙከራ የተበላሸው ሥልዕ

የፎቶው ባለመብት, Centro de Estudios Borjanos

የምስሉ መግለጫ, በዕድሜ ብዛት አርጅቶ የነበረው ሥዕልና ለማደስ በተደረገ ሙከራ የተበላሸው ሥልዕ

ከተማዋ አይደለም የተሳሳተችው። አንዲት እናት ናቸው የተሳሳቱት። ለዚያውም ቀይ ስህተት።

እኚህ እናት በአንድ ቤተ ክርስቲያን የሚገኝ ሥዕልን ደግሜ አሻሸዬ ካልሰራሁ ብለው ተነሱ።

ደግሞ ማንም ሳያውቅ።

ይህ ሥዕል ተራ ሥዕል እንዳይመስላችሁ።

ከተሣለ ራሱ መቶ ዓመት ያለፈው የኢየሱስ ዝነኛ ምሥል ነው። ፒላጦስ ከደሙ ንጹሕ ነኝ ያለበትን ቅጽበት የሚያሳይ ሥዕል።

ይህ ሥዕል ታዲያ ቤተ ክርስቲያን ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ ነው የኖረው።

እኚህ ቤተ ክርስቲያን ሳሚ ሴትዮ አስተካክላለው በድጋሚ ለመሳል ብለው ነው ጌታ ‘እንኳ ይቅር አይለውም’ የተባለለት ጥፋት ያጠፉት።

እኚህ ሴት አዘውትረው ከሚሄዱበት ቤተክርስቲያን ውስጥ ተሰቅሎ ያለው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስል ‘ገረጣ’ ብለው አዘኑ። አልተመቸውም አሉ።

ቡሩሽ ይዘው መጡ። ኢየሱስ ከመሰቀሉ በፊት የእሾክ አክሊል አድርጎ የሚታይበት ሥዕል ዘንድ ወደ ግድግዳ ተጠጉ። ቀለም በጠበጡ። ማንም ሳያያቸው ነው ታዲያ።

ያሳዝናል። ቅርስ ነው የተባለው የሥዕል ሥራ ተበለሻሸ። ዓለም አዘነ። መገናኛ ብዙኃን እንደለመዱት አላዘኑ።

ይህ ሥራ የኢየሱስ ምሥል ያለበት ዝንተ ዓለም ሲወደስ የኖረ ከባድ የሥዕል ሥራ ነበር። የዓለም ሠዓሊያን ሰልፍ ወጡ።

እንዴት የዝነኛው ሠዓሊ የኤሊያስ ጋርሺያ ማርቲኔዝ ሥራ “በአንዲት እብድ አሮጊት ይደፈራል” አሉ።

በሴትየዋ ገጽታው የተቀየረው ምሥል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሴትየዋ ገጽታው የተቀየረው ምሥል

ሴትየዋ ያደረጉት ምንድነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እኚህ ሴትዮ ቤተ ክርስቲያን አይጠፉም።

ሁልጊዜም ታዲያ አንድ ነገር ይረብሻቸዋል።

በቤተ ክርስቲያኑ ግድግዳ ላይ የተሳለው ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥዕል።

ከዕለታት አንድ ቀን ይነሱና ሥዕሉን የተሻለ ገጽታ አላብሰዋለሁ ብለው ነጠላ ይደርባሉ።

ቡሩሽና ቀለም ይዘው ይጠጉታል። ታሪክ የተቀየረው ከዚህ በኋላ ነበር። ከዚህ ሌላ ምንም አላደረጉም። ሌላ ዓላማም አልነበራቸውም።

ይህ ነው የጥበቡን ዓለም ከፍና ዝቅ ያደረገው።

መቼና የት ነው ይህ የሆነው?

ይህ ክስተት መቼና የት እንደሆነ ለመረዳት ወደዚህች እምብዛምም ወደማትታወቅ ከተማ ገባ ብለን ቶሎ ለምን አንወጣም?

እኛ ብቻ ሳንሆን ብዙ ሕዝብ እየጎረፈ ነው።

ይቺ ከተማ ስፔን ውስጥ ነው የምትገኘው። በሰሜን ምሥራቅ ስፔን፣ ከማድሪድ ወዲያ፣ ዛራጎዛ ከተማ አቅራቢያ የምትገኝ ናት።

ነዋሪዋን ቆጥሮ ለመጨረስ ግማሽ ቀን ይበቃል። 5 ሺህ ሰው ነው የሚኖርባት።

በፊት እንዲያውም ማንም ይቺን ከተማ የሚያውቃት አልነበረም፤ ከነዋሪዎቿ ሌላ። አሁን ታሪክ ተቀይሯል። ዕድሜ ለኚህ ምስኪን አሮጊት።

ከተማዋ ፍጹም ባልተጠበቀ ፍጠነትና ሁኔታ ዝነኛ ሆናለች። ቱሪስት ትንፋሽ አሳጥቷታል። ባርሴሎናን እየሆነች ነው።

የዚች ጢኒጥዬ ከተማ መጠሪያ ስም ቦርዣ ይባላል።

ዝነኛው የኢየሱስ ሥዕል የሚገኘው ደግሞ በዚህ ከተማ ሳንቹሪዮ ዲ ላ ሚዜሮኮርዲያ በሚባል የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነበር።

ይህ ሥዕል ታዲያ የዋዛ እንዳይመስላችሁ። በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተሳለ ከመሆኑም በላይ እጅግ የሚወደድና የሚከበር የጥበብ ሥራ ነው።

ነገር ግን አረጀ። ይህ ያሳሰባቸው አንዲት አሮጊት ሴትዮ ተደብቀው በመምጣት ሊጠግኑት፣ ሊያሻሽሉት ፈለጉ።

ይህ የሆነው የዛሬ 10 ዓመት ገደማ በፈረንጆቹ 2012 ነበር።

ኢቼ ሆሞ (Ecce homo) ተብሎ ይጠራል ይህ ሥዕል፤ በደምሳሳው ሲተረጎም ‘ይህን ሰው በቁጥጥር ሥር አውሉት’ እንደማለት ነው።

በይዘት ሲተረጎም ደግሞ የፒላጦስ “ከደሙ ንጹህ ነኝ’ ቅጽበትን የሚተርክ ነው።

ኢየሱስ ከመሰቀሉ በፊት አናቱ ላይ የእሾክ አክሊል ተደርጎለት የሚታይበት ነው።

እኚህ ንጹሕ የዋህ እናትም ድርጊቱን ከፈጸሙ በኋላ ከደሙ ንጹህ ነኝ አላሉም። ወይም ብለዋል። ብቻ እንደ አተረጓጎማችን ነው።

ሴሲሊያ ጊሜኔዝ
የምስሉ መግለጫ, ሴሲሊያ ጊሜኔዝ

የዋኋ እናት

ሴትየዋ ሴሲሊያ ጊሜኔዝ ይባላሉ።

ያን ጊዜ ዕድሜያቸው 80 ደርሶ ነበር። አሁን ዕድሜያቸው ዘጠናን አልፏል።

የኢየሱስን እያረጀ የነበረ ሥዕል እጠግናለሁ ብለው ተነስተው እብድ የተጫወተበት ደብተር አስመሰሉት።

ያኔ ብዙ ጋዜጦች “ከኢየሱስነት ወደ ዝንጀሮነት የተለወጠው ምሥል” እያሉ ነው ቁጣቸውን የገለጡት።

ማኅበራዊ ሚዲያ በቧልት ተሞላ። በርካታ ኮሜዲ ትዕይንቶች ክስተቱን ለሳምንት መርሐ ግብር ግብአት አዋሉት።

የእናቲቱ ድርጊት በማኅበራዊ ሚዲያም መዘባበቻ ሆኖ ለዓመታት ቆየ።

120 ዓመት ባስቆጠረ ተወዳጅ ሥዕል ላይ የደረሰው ጥፋት ቁጣን ቀሰቀሰ።

አገሪቱ አበደች፤ ስፔን ጉድ ተባለ። ፖሊስ መያዣ አወጣ፤ ኒውዮርክ ታይምስ እና ቢቢሲ ሳይቀሩ በዝነኛው የሥዕል ላይ ወንበዴዎች ጉዳት አደረሱ ሲሉ ጻፉ።

ምክንያቱም ድርጊቱ በተፈጸመ ቅጽበት ማን ይህን እንደፈጸመ አልታወቀም ነበርና።

ነገሩ ከፍተኛ የዓለም ትኩረት ሳበ።

አንዲት እናት ከዘራ ይዘው ለፖሊስ እጅ ሰጡ።

ሴትዮዋ ሲሲሊያ ጊሜኔዝ ናቸው። ታሪካቸውን የነገርናችሁ ሴት።

እንዲያውም ቁጣው በርሳቸው ባሰ። “ምንድነው የምታወሩት” ብለው ቱግ አሉ፤ ፖሊስ ደነገጠ።

“ወንደበዴዎች ይህን አልፈጸሙም፤ እኔ ነኝ ይህን ያደረኩት” ብለው ተናዘዙ።

ተናዘዙ ሳይሆን ነገሩን አብራሩ።

“ድርጊቱን ተደብቄ አልፈጸምኩም፤ እዚህ ያሉትን ቀሳውስት አማክሪያቸዋለሁ፤ በጨለማም አልፈጸምኩትም። በጠራራ ፀሐይ ነው ሥዕሉን ለማደስ የሞከርኩት፤ ምንድነው ጥፋቴ?” ብለው ተንቀጠቀጡ።

“የጌታ ምሥል ተጎሣቅሎ አርፈሽ ቁጭ በይ ነው የምትሉኝ?”

ምስሉን ለመመልከት ቱሪስቶች እየጎረፉ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ምስሉን ለመመልከት ቱሪስቶች እየጎረፉ ነው

ከሃፍረት ወደ ዝና

ይቺ ጢኒጥ የስፔን ከተማ አሁን ቀን ወጥቶላታል።

መሳቅያ እንዳልነበረች አሁን ዝናዋ ናኝቷል።

ሰዎች ከብዙ ሺህ ማይልስ ተነስተው ይቺን ‘በስህተት የደመቀች’ ከተማን ለመጎብኘት ይመጣሉ።

ከ10 ዓመት በኋላ የኚህ አሮጊት ሴትዮ ድርጊት ‘በጎ ስህተት’ ተብሎ ተሞካሸ።

እኒያ ቤተ ክርስቲያን ሳሚ እናት ወትሮም ለጥፋት አልተነሱም።

ደግሞም ኢየሱስ ያስተማረን ስህተትን ይቅር እንድንል ነው ተባለ።

እኚህ እናት ዛሬ 91 ዓመታቸው ሆኖ በመጦሪያ እየኖሩ ነው።

የቦርጃ ከተማ ከንቲባ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፥ “አሮጊቷ ጤናቸው ተዳክሟል፤ ሆኖም ግን ድርጊቱን በደንብ ያስታውሳሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

ከንቲባ ፓብሎ ጨምረው እንዳሉት በቅርቡ ለሴትዮዋ ክብር ሻማ ይበራል። ይደገሳል። የ10 ዓመቱ ስህተት ድል ባለ ድግስ ይዘከራል።

ምክንያቱም ቦርዣ ከተማን ከመናኛ ከተማነት ወደ ዝና ማማ ያደረሱ ሴት ስለሆኑ።

ከንቲባው በኚህ ‘ጀግና’ ምስኪን እናት የተነሳ ከ110 አገሮች ቱሪስቶች ጎርፈውልናል ብለዋል።

አሁን በዓመት ይቺን ከተማ 40 ሺህ ቱሪስት ይጎበኛታል። ዕድሜ ለየዋህ ስህተት።

አሁን ያ ዝነኛ ሥዕል በተጎበኘ ቁጥር እኚህ በሥዕሉ ላይ ቀይ ስህተት የሠሩ አሮጊት ከጎብኚዎች ገቢ 40 ከመቶውን እንዲያገኙ ተደርጓል።

አሃ! ልክ ነዋ። አሁን እኮ ሥዕሉ የዝነኛው ጋርሺያ ብቻ አይደለም፤ አሮጊቷም ቀለም ‘ደፍተውበታላ’።

እሳቸው ግን ገንዘቡን ለበጎ አድራጎት በመስጠት ይታወቃሉ።

‘ጌታ ሆይ! አውቄ በድፍረት፣ ሳላውቅ በስህተት ለፈጸምኩት ይቅር በለኝ’ እያሉ ይሆን?