ሁለት የእንጀራ ልጆቿን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል የተጠረጠረችው ሴት በቡራዩ ፖሊስ እየተፈለገች ነው

በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ ቡራዩ ክፍለ ከተማ አንዲት እንጀራ እናት ሁለት ልጆችን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደሏ እየተፈለገች መሆኑን ፖሊስ ገለፀ።

በቡራዩ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ባልደረባ የሆኑት ዋና ሳጅን ቀነኒሳ ታደሰ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ወንጀሉ የተፈፀመው ቅዳሜ ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም. በከታ ወረዳ ልዩ ስሙ ሦስተኛ ቡራዩ በሚባል ስፍራ ነው።

ወንጀሉ የተፈፀመው ሌሊት መሆኑን የገለጹት ዋና ሳጅን ቀነኒ፣ ሁለት ሕጻናት በአሰቃቂ ሁኔታ በእንጀራ እናታቸው ተገድለዋል መገኘታቸውን ተናግረዋል።

“ተጠርጣሪዋ ነጋሴ ከበደ ብሩ የምትባል ስትሆን፣ የባለቤቷን ሁለት ልጆች አንገታቸውን ቀልታ፣ በተኙበት ብርድ ልብስ አልብሳ እሳት ለኩሳባቸው አምልጣለች ተብላ ተጠርጥራለች።”

የልጆቹ አባት የሆኑት አቶ ጌታሁን ባልቻ በአካባቢው የሚገኝ ቄራ የሚሰሩ ሲሆኑ፣ ግድያው በተፈፀመበት ዕለት ማምሻውን ከባለቤታቸው ጋር በልጆቻቸው ጉዳይ ተነጋግረው እንደነበር ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“በልጆቼ ጉዳይ ተነጋግረን ነበር። እንደዚህም ምክንያት እንለያይ ተባብለን፤ እርሷም ‘እኔ እሄዳለሁ፣ አንተ እዚህ ትኖራለህ’ አለችኝ” ሲሉ ለመጨረሻ ጊዜ የተነጋገሩትን ያስታውሳሉ።

ምሽት ሲነጋገሩ አቶ ጌታሁን ከባለቤታቸው ዛቻም ሆነ ለእንደዚህ አይነት አሰቃቂ ድርጊት ያበቃል ብለው የሚጠረጥሩት ጠቋሚ ነገር አለማየታቸውን ይናገራሉ።

አክለውም “ሌሊት ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ወደ ቤት ስመለስ የቤቱ በር ክፍት ነበር። ወደ ውስጥ ስገባ እሳት ይነዳል። ልጆቼን አልጋ ላይ ሳያቸው ጭሱ አፈነብኝ ብዬ ሮጬ ወደ ውጪ አወጣኋቸው። በወቅቱ ትልቁ ልጄ ተቃጥሏል። ትናሿ ልጄንም አወጣኋት። ወደ ውጪ ካወጣኋቸው በኋላ እነርሱ ላይ ወድቄ ራሴን ሳትኩኝ።”

አቶ ጌታሁን ልጆቹን መጀመሪያ ሲያያቸው በሕይወት ያሉ መስሎት እንደነበር እና ያሟሟታቸውን ሁኔታ ራሱን ከሳተበት አንድ ቀን በኋላ ነቅቶ ከአካባቢ ነዋሪዎች እና ከፖሊስ መስማቱን ይናገራል።

ሳጅን ቀነኒሳ እና ሌላ የቅርብ ጓደኛውም አቶ ጌታሁን ራሱን ከሳተበት የነቃው ትናንት፣ እሁድ ዕለት መሆኑን ይናገራሉ።

“ልጆቼን ማሳደግ እፈልጋለሁ እንለያይ አልኳት. . . እኔ እሄዳለሁ አንተ እዚህ ትኖራለህ አለችኝ። ይህንን ብቻ ነው የተናገረችኝ። እንደዚህ ዓይነት ድርጊት በልጆቼ ላይ፣ ቤተሰቤ ላይ፣ እንስሳትም ላይ ታደርጋለች ብዬ አላሰብኩም።”

በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት የአቶ ጌታሁን ልጆች አንደኛው የ13 ዓመት ወንድ ሲሆን፣ ሌላኛዋ ደግሞ የ4 ዓመት ተኩል ሴት ናቸው።

ሁለቱም አንገታቸው ተቀልቶ መገደላቸውን ፖሊስ ተናግሯል።

አቶ ጌታሁን በ2013 ዓ.ም የልጆቻቸውን እናት በሞት ካጡ በኋላ ባለፈው ታኅሣሥ ነበር ከተጠርጣሪዋ ጋር የተጋቡት።

ሲጋቡም የልጆቻቸውን ሁኔታ ገልፀው፣ ተማምነው እንደነበር ይናገራሉ።

ከእናታቸው ሞት በኋላ ልጆቹ አያታቸው ጋር የነበሩ ሲሆን፣ የአቶ ጌታሁን አባት ባለፈው ነሐሴ ማረፋቸውን ተከትሎ ልጆቹ ወደ አባታቸው ዘንድ መጥተዋል።

ተጠርጣሪዋ ከዚህ በፊት ለአራት ዓመት በአረብ አገር ቆይታ እንደነበር ፖሊስ ቤተሰቦቿን ጠቅሶ ሳጅን ቀነኒ ይናገራሉ።

ከዚያ በኋላ እዚያው ቡራዩ አካባቢ “ሽሮ ቤት” ከፍታ ስትሰራ ቆይታለች።

ነዋሪነቷም እዚያው ቡራዩ አካባቢ ኤጀርሳ ጎሮ የሚባል አካባቢ እንደሆነ ፖሊስ አክሎ ገልጿል።

አሁን ፖሊስ ተጠርጣሪዋን በቁጥጥር ስር ለማዋል ማኅበራዊ ሚዲያን ጨምሮ ፎቶዋን በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች አሰራጭቶ እየፈለገ ይገኛል።

በቁጥጥር ስር የዋሉ የቤተሰቦቿ አባላትም መኖራቸውን ዋና ሳጅን ቀነኒሳ ይናገራሉ።

ከሰበታ እስከ አንቦ ድረስም ከተጠርጣሪዋ ጋር የሚመሳሰሉ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችም መኖራቸውን ዋና ሳጅን ቀነኒ አክለው ገልጸዋል።