አሜሪካዊው ራፐር ዲዲ ድጋሚ በመድፈር ወንጀል ክስ ተመሰረበት

አንዲት ሴት በአውሮፓውያኑ 1991 የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ሾን ‘ዲዲ’ ኮምብስ ማደንዘዣ ሰጥቶኝ ወሲባዊ ጥቃት አድርሶብኛል ስትል ከሰሰች።

ቢቢሲ የተመለከተው የክስ መዝገብ እንደሚገልጠው ከሳሽ፤ ዲዲ የመድፈር ወንጀል ፈፀመብኝ ያለችው ከራፐሩ ጋር ለመዝናናት በወጡበት ወቅት ነው።

ሾን ኮምብስ በቅርቡ በአርኤንድቢ አቀንቃኟ የቀድሞ የፍቅር አጋሩ ካሳንዳራ ቬንቹራ ክስ ቀርቦበት በድርድር መፍታቱ ይታወሳል።

የራፐሩ ተወካይ አዲሱን ክስ “የፈጠራ ወሬና የማይታመን ነው” ብለውታል።

“ይህ በግልጥ ገንዘብ ለማግኘት የሚደረግ ሙከራ እንጂ ሌላ ምንም ዓላማ የለውም” ይላል የራፐሩ ቃለ አቀባይ ለቢቢሲ የላኩት መግለጫ።

ጆይ ዲከርሰብ-ኒል የተባለችው ከሳሽ በከፈተችው መዝገብ የተዋወቀችው በጓደኞች አማካይነት መሆኑን ትገልጣለች።

ፓፍ ዳዲ እንዲሁም ፒ ዲዲ በተሰኙ የመድረክ ስሞቹ የሚታወቀው ራፐር በሙዚቃ ቪድዮው ላይ እንዳካተታትም የክስ መዝገቡ ያመላክታል።

መዝገቡ እንደሚለው ጥር 3/1991 ከሳሿ “እያመነታች” ሾን ኮምብስን ከምትሰራበት አንድ ሐርለም የሚገኝ ሬስቶራንት ለማግኘት ቀጠሮ ያዘች።

መዝገቡ አክሎ “በከተማዋ ሌሎች ጉዳዮችን እያከናወነ ሳለ አብራው እንድትሆን አደረጋት።”

እሷ እንደምትለው በቀጠሯቸው ወቅት ዲዲ ተከሳሿ “መቆምም ሆነ መራመድ እስኪሳናት ድረስ” መርዟታል።

ከዚያም ወዳረፈበት ሆቴል ይዟት ሄዶ ወሲባዊ ጥቃት እንደፈፀመባት የክስ መዝገቡ ያትታል።

ከሳሿ፤ ራፐሩ ድርጊቱን በቪድዮ ካሜራ በድብቅ ቀርፆ ካስቀረ በኋላ ለሌሎች ሰዎች ማሳየቱን ትናገራለች።

የክስ መዝገቡ እንደሚጠቅሰው ዲዲ የተጠረጠበትን ድርጊት ከፈፀመ በኋላ ከሳሽ ሕይወቷ “ተመሰቃቅሏል”፤ የአእምሮ ጤናዋ ተቃውሷል፤ አልፎም ትምህርቷን ለማቋረጥ ተገዳለች።

የኒው ዮርክ አዳልት ሰርቫይቨርስ አክት የተሰኘው የወሲብ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ጊዜው ቢያልፍ እንኳ ክስ መመሥረት እንዲችሉ የሚፈቅደው አንቀፅ ዛሬ ከጥቅም ውጭ ከመሆኑ ከሰዓታት በፊት ነው ክሱ የተመሠረተው።

“ደንበኛችን ኮምብስ ከዓመታት በፊት ካደረሰባት ጉዳት ሙሉ በሙሉ አላገገመችም” ይላሉ ከከሳሿ ጠበቆች አንዱ ጆናታን ጎልድሂርሽ።

“በአዳልት ሰርቫይቨርስ አክት መሠረት በስተመጨረሻ ፍትሕ ለማግኘት ወደ ፍርድ ቤት ትሄዳለች።”

ሾን ‘ዲዲ’ ኮምብስ በወሲባዊ ጥቃት ተጠርጥሮ በአንድ ወር ውስጥ ክስ ሲቀርብበት ይህ ሁለተኛው ነው።

ካሳንድራ ቬንቹራ ባለፈው ሳምንት የራፕ ሙዚቃ ጉምቱ እየተባለ የሚጠራው ዲዲን በመድፈር እና በወሲብ ዝውውር በፌዴራል ፍርድ ቤት መክሰሷ አይዘነጋም።

ኬሲ በተሰኘ የመድረክ ስሟ የምትታወቀው አቀንቃኟ፤ ለ10 ዓመት ያክል እሷ 19 ራፐሩ ደግሞ የ37 ዓመት ዕድሜ ላይ ከነበረቡት ጊዜ ጀምሮ የመድፈር ወንጀል ፈፅሞባታል፤ ደብድቧታል።

ክሱ በተመሠረተ በነጋታው ሁለቱም በድርድር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይፋ አድርገዋል።

ሾን ዲዲ ከቬንቹራ የቀረበበትን ክስ የሚያጣጥል ሲሆን ጠበቃዎቹ ደግሞ ጉዳዩ በስምምነት መፈታቱ ጥፋት እንዳጠፋ ማመኑን የሚያሳይ አይደለም ይላሉ።