የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ኃይሎች ሽራሮን ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎችን መያዛቸውን ታደሰ ወረደ ገለጹ

የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ታደሰ ወረደ

የፎቶው ባለመብት, tigray tv

የምስሉ መግለጫ, የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ታደሰ ወረደ

የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሠራዊት ባለፉት ቀናት በከፈተቱ መጠነ ሰፊ ጥቃት ሽራሮን ጨምሮ የተለያዩ የትግራይ አካባቢዎችን መያዛቸውን ገለጹ።

ዋና አዛዡ ማክሰኞ መስከረም 03/2015 ዓ.ም. ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ እየተካሄደ ነው ስላሉት ጦርነት በሰጡት መግለጫ “ከኤርትራ አቅጣጫ የመጣው የሁለቱ አገራት ሠራዊት ሽራሮን ተቆጣጥሯል” ብለዋል።

ከኤርትራ ድንበር 50 ኪሎ ሜትሮች በላይ የማትረቀው ሽራሮ ከተማ ወደ ሽረ እንዳስላሴ፣ ባድመ እና ሁመራ አቅጣጫ ለመጓዝ አዋሳኝ ከተማ ነች።

የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ መንግሥት ጥምር ጦሩ ሽራሮን ጨምሮ አንዳንድ የትግራይ አካባቢዎችን ይዘዋል ስለመባላቸው ያሉት ነገር የለም።

“አደመይቲ፣ ሀልነብሪ እና አደርቃይን ተቆጣጥረዋል” ያሉት ታደሰ ወረደ፤ “ማይ ፀብሪን ለመያዝ ማጥቃት ቀጥሏል። ማይ ፀብሪ ላይ ቆሞ ነው ያለው” ሲሉ እየተካሄደ ስላለ ውጊያ ተናግረዋል።

ታደሰ ወረደ የሰጡት መግለጫ የትግራይ አመራሮች የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነትን በንግግር ለመፍታት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ከገለጹ በኋላ ጦርነት ተጠናክሮ መቀጠሉን ያመላከተ ሆኗል።

የትግራይ አመራሮች በኢትዮጵያን የዘመን መለወጫ መስከረም 01/2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ አዲሱ ዓመት የተኩስ ደምጽ የማይሰማበት እንዲሆን፤ ግጭት በአስቸኳይ ቆሞ ንግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህን የህወሓት የተኩስ አቁም እና የንግግር ጥሪን የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት-ኢጋድ፣ የአፍሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ እና ጀርመን እንደሚደግፉት በመግለጽ የሰላም ንግግሩ በአፋጣኝ እንዲጀመር ጥሪ አቅርበው ነበር።

ጦርነቱን “በየትኛውን ጊዜ እና ቦታ” በንግግር ለመፍታት ዝግጁ ነኝ ሲል የነበረው የፌደራሉ መንግሥት የትግራይ አስተዳዳሪዎች የድርድር ጥሪን ተከትሎ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

የትግራይ ኃይሎች መሪ ጀነራል ታደሰ፤ የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት ምሥራቅ ዕዝ ወደ ኤርትራ ተሻግሮ ከኤርትራ ሠራዊት ጋር በመሆን በሁለት አቅጣጫ “ትልቅ ኃይል” አሰልፏል ያሉ ሲሆን፤ “አንዱ በሽራሮ አቅጣጫ የሚያጠቃ ነው። ሌላኛው ደግሞ ባድመን መነሻ አድርጎ ጥቃት ከፍቷል ብለዋል።

የትግራይ ኃይሎችን ‘ትጥቅ ማስፈታት’

ሽራሮ ካርታ

ጀነራሉ በትናንቱ መግለጫቸው እየተፋለሟቸው ያሉት ኃይሎች የጦርነቱን አካሄድ በተመለከተ በተለያዩ ምዕራፎች የተከፋፈሉ ዕቅዶች አሏቸው ብለዋል።

“አክሱም፣ አዲግራትን፣ ሽረን የመቆጣጠር እና መቀለ የመግባት እቅድ አለ። . . . ወደ ተንቤን የሚሄድ መንገድን የመዝጋት ዕቅድ አላቸው” ያሉ ሲሆን፤ በዕቅዳቸው መሠረት የመጨረሻው ምዕራፍ የትግራይ ኃይሎችን “ትጥቅ ማስፈታት ነው” ብለዋል።

ታደሰ ወረደ በመግለጫቸው ባለፉት አምስት ቀናት ያልተቋረጠ ከባድ የሚባል ጦርነት በተለያዩ ግንባሮች እየተካሄደ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ተከዜ ድልድይ ተሻግሮ ፀሊም ወየ ደረሶ ደደቢት ቀርቧል ብለዋል።

ጨምረውም ከኤርትራ በኩል የመጣው ኃይል እና ከደደቢት አቅጣጫ ከመጣው ጋር ለመገናኘት ብዙ ሞክረዋል ብለዋል።

“ተከበናል ስለዚህ አላማችን መከላከል ነው. . . እጅ እንድንሰጥ ነው የሚፈልጉት” ያሉት የጦር አዛዡ “የትግራይ ሕዝብ እስካሁን ከገጠመው ትልቁ ሊባል የሚችለው የተቀናጀ ማጥቃት ነው እየተካሄደ ያለው” በማለት እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ገልጸዋል።

ታደሰ ወረደ ጨምረውም የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት በንግግር ነው መቋጨት አለበት ሲሉም ተደምጠዋል።

የጦር አዛዡ፤ የትግራይ መንግሥት የሰላም ጥሪ እያደረገ ነው ያሉ ሲሆን፤ “እያደረግን ያለነው የመከላከል ውጊያ ነው። ያለው ብቸኛ አማራጭ ሰላም በመሆኑ. . . ጦርነቱ በሰላም ነው መጠናቀቅ ያለበት” ሲሉ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ ባይችልም የትግራይ ኃይሎች በተካሄዱት ውጊያዎች በርካታ የተቃናቃኞቻቸውን ወታድሮች መደምሰሳቸውንና እንዲበተኑ ማድረጋቸውን አዛዡ ተናግረዋል::

አዲስ የድሮን ጥቃት

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመቀለ ከተማ ዛሬ ረቡዕ 04/2015 ዓ.ም. ጠዋት አዲስ የአየር ጥቃት መፈጸሙን የትግራይ ኃይሎች ገልጸዋል።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ዛሬ ንጋት ላይ በመቀለ ከተማ የሰው አልባ አውሮፕላን የአየር ጥቃት መፈጸሙን ገልጸዋል።

የድሮን ጥቃት የመኖሪያ መንደሮችን ዒላማ ማድረጋቸውን እና በጥቃቱ በአሃዝ ያልገለጿቸው ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል።

የአይደር ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ክብሮም ገ/ሥላሴ ዛሬ ማለዳ በመቀለ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ለቢቢሲ አረጋግጠው፣ በጥቃቱ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።

ዛሬ ማለዳ 1፡30 ዳግም አምሳል በተባለ አካባቢ በተፈጸመ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት 10 ሰዎች መገደላቸውን እና 10 ሰዎች ጉዳት እንደ ደረሰባቸው የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በትናንትናው ዕለትም በመቀለ በተፈፀመ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት የድምፀ ወያኔ ቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣብያ እና መቀለ ዩኒቨርስቲ መመታቱ ተሰምቶ ነበር።

በመቀለ ከተማ በተፈጸመ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት እስካሁን ድረስ ከፌደራል መንግሥቱ በኩል የተባለ ነገር የለም።