ለኮቪድ ክትባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሁለት ሳይንቲስቶች የኖቤል ሽልማትን አሸነፉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኖቤል የጤና እና የፊዚዮሎጂ ሽልማት ኤምአርኤንኤ የተባለውን የኮቪድ ክትባትን ለመሥራት የሚያስችል ቴክኖሎጂን ላዳበሩ ሁለት ሳይንቲስቶች በጋራ ተሰጠ።
ፕሮፌሰር ካታሊን ካሪኮ እና ፕሮፌሰር ድሪው ዋይስማን የዚህን ዓመት የኖቤል የጤና ሽልማትን በጋራ ማግኘታቸው ይፋ ሆኗል።
ቴክኖሎጂው የኮቪድ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት በሙከራ ደረጃ ላይ የነበረ ሲሆን፣ አሁን በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ወረርሽኙን ለመከላከል ተስጥቷል።
ይህ ቴክኖሎጂ በአሁኑ ጊዜ ካንሰርን ጨምሮ ለሌሎች በሽታዎች ጥቅም ላይ ለማዋል ምርምር እየተደረገበት ነው።
የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው ሁለቱን ሳይንቲስቶች ይፋ ሲያደርግ “በሰው ልጅ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ላጋጠመው ከፍተኛ የጤና ስጋት ሁለቱ ተሸላሚዎች ቀደም ሲል ባልታየ ሁኔታ ክትባት በማዳበር በኩል አስተዋጽኦ አበርክተዋል” ብሏል።
ሳይንቲስቶቹ የኖቤል ሽልማትን ማሸነፋቸው ዛሬ ሰኞ ጠዋት የተነገራቸው ሲሆን፣ የዓለማችን ዋነኛ ሽልማት አሸናፊ ሆነው በመመረጣቸው “ደስተኛ” መሆናቸውን መናገራቸው ተዘግቧል።
ክትባቶች የሰዎች ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከል ሥርዓት ቫይረስ እና ባክቴሪያን የጤና ጠንቆችን እንዲለይ እና እንዲዋጋ ያደርጋሉ።
የተለመደው ዓይነት በሽታን መከላከያ ክትባቶች የሚዘጋጁት ከሞቱ ወይንም ከተዳከሙ ቫይረሶች ወይም ባክቴሪያዎች ነው።
ከዚህ አንጻር ተሸላሚዎቹ ሳይንቲስቶች የፈጠሩት ኤምአርኤንኤ የተባለው ቴክኖሎጂ ግን ክትባት እንዲሠራ ፈጽሞ የተለየ መንገድን ይከተላል ተብሏል።
የኮቪድ ወረርሽኝ በተከሰተበት ጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የተደረጉት ሞደርና እና ፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባቶች ይህንን ኤምአርኤንኤ ቴክኖሎጂን መሠረት አድርገው ነው የተሰሩት።
ሁለቱ ዶክተሮች ካሪኮስ እና ዋይስማን አብረው መሥራት የጀመሩት በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ በአሜሪካው ፔንሲልቬኒያ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ሲሆን፣ በኤምአርኤንኤ ቴክኖሎጂ ላይ የነበራቸው ፍላጎት ብዙም የሚያዛልቅ አይደለም ተብሎ ታስቦ ነበር።
ይህ ቴክኖሎጂ በሰው ልጅ አካል ውስጥ እንደ አስተርጓሚ ሆኖ የሚሠራ ነው። ቴክኖሎጂው የሰው ልጅ ዘረ መል (ዲኤንኤ) ላይ ያሉ መረጃዎችን ተንትኖ ለመረዳት የሚያስችል ነው።
የሚገኘውን መረጃ መሠረት በማድረግም የሰው ልጅን የሚያጋጥሙ የጤና ጠንቆችን በዝርዝር በመረዳት፣ ተፈጥሯዊው በሽታን የመከላከያ ሥርዓት ቫይረስ ወይም ባክቴሪያዎችን ለመዋጋት እና ለማጥፋት የሚያስችለውን ዕውቀት እንዲያዳብር ያደርጋል።
ይህ ኤምአርኤንኤ ቴክኖሎጂን በተለይ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በታማሚዎች ውስጥ በሽታውን ለመቋቋም እና ለማጥፋት የሚያስችል ሁኔታን በመፍጠር ወሳኝ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ዶ/ር ካታሊን ካሪኮ በአሁኑ ጊዜ በሃንጋሪ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ዶ/ር ድሪው ዋይስማን ደግሞ እዚያው ፔንሲልቬኒያ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ፕሮፌሰር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።












