ፊፋ የክሪሚያን ካርታ ባለማካተቱ ይቅርታ ይጠይቀኝ ስትል ዩክሬን ከሰሰች

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ የ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ድልድል ይፋ ባደረገበት ወቅት "ይቅርታ የማይደረግለት ስኅተት" ፈፅሟል ስትል ዩክሬን ወቀሰች።

ፊፋ ያስመለከተው የዩክሬን ካርታ ክሪሚያ የተባለችውን ግዛት ያላካተተ ነበር።

በቀጣናዊ ፖለቲካ ምክንያት እርስ በርስ የማይጫወቱ ሀገራት ስክሪን ላይ ሲታዩ ነው የክሪሚያ ሰርጥ የሌለበት የዩክሬን ካርታ የመጣው።

ክሪሚያ ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ በሩሲያ ቁጥጥር ስር ብትሆንም ከጥቂት ሀገራት በቀር በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የዩክሬን አካል ተደርጋ ነው የምትቆጠረው።

የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄዎርሂይ ቲኺ ሀገራቸው "ኦፊሴላዊ ይቅርታ" እንደምትጠብቅ አስታውቀዋል።

ፊፋ "ጉዳዩን ማስተዋሉን" አሳውቆ ፎቶውን ከቋቱ ማስወገዱን ተናግሯል።

የዩክሬኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊፋ "ከዓለም አቀፍ ሕግ ውጭ የሆነ ተግባር ከመፈፀሙም" በላይ "የሩሲያን ፕሮፖጋንዳ፣ የጦር ወንጀል እና ዩክሬን ላይ የተፈፀመውን ወረራ ደግፏል" ሲሉ በኤክስ ገፃቸው ፅፈዋል።

አክለው ፊፋ ስኅተቱን አርሞ "የተሻሻለ" እና ክሪሚያ የዩክሬን አካል የሆነችበት ፎቶ እንዲለጥፍ ጠይቀዋል።

እርስ በርስ ከማይጫወቱ ሀገራት መካከል ዩክሬን እና ቤላሩስ፤ ስፔን እና ጂብላርታር እንዲሁም ኮሶቮ ከቦስኒያ እና ሄርዜጎቪና አሊያም ከሰርቢያ ይገኙበታል።

የዩክሬን እግር ኳስ ማኅበር ለፊፋ ዋና ፀሐፊ ማቲያስ ግራፍስሮም እና ለአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ዋና ፀሐፊ ቴዎዶር ደብዳቤ ልኳል።

"ታኅሣሥ 13/2024 የታየውን ካርታ በተመለከተ የተሰማንን ለመግለፅ ነው ይህንን ደብዳቤ የላክነው" ይላል።

ደብዳቤው አክሎ ፊፋ ያደረገው "በፍፁም ተቀባይነት የሌለው እና የፊፋ እና የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር የተለያየ አቋም መያዛቸውን የሚያሳይ ነው" በማለት ወቅሷል።

የ2026 የዓለም ዋንጫ በአውሮፓውያኑ ሰኔ 11 በሜክሲኮ ሲቲ ጀምሮ ሐምሌ 19 በአሜሪካዋ ኒው ጀርዚ ይጠናቀቃል።

በአዲስ መልክ የሚካሄደው እና 48 ሀገራት የሚሳተፉበት የ2026 የዓለም ዋንጫ 39 ቀናት ይቆያል።

ዩክሬን በማጣሪያው በምድብ መ ከአይስላንድ፣ አዘርባይጃን እና ከፈረንሳይ አሊያም ክሮኤሺያ ተደልድላለች። በአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ፈረንሳይ ከክሮኤሺያ የምትጫወት ሲሆን አሸናፊዋ ሀገር በምድብ መ ትከተታለች።