ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሊቨርፑልን ከአርሰናል ያገናኘው የፕሪሚየር ሊግ ሳምንት ግምት
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሐሙስ፣ አርብ እና ቅዳሜ - የሱተን ግምት ምን ይላል?
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ቡድኖች ቅዳሜ አንፊልድ ተገናኝተው ይፋለማሉ።
ከአርሰናል እና ከሊቨርፑል ማን ለዋንጫው ያለውን ጥማት ያሳየናል?
የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን ባለፈው ዓመት ሁለቱ ቡድኖች በአንፊልድ ሲገናኙ የሆነውን ያስታውሳል።
“በርካታ ሰዎች ቀጣይ ቅዳሜ የሚደረገውም ጨዋታ በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል ይላሉ። እኔ ግን ዘንድሮ ሊቨርፑል እያሳየ ያለው አቋም ተመችቶኛል። ሞሐመድ ሳላህ የተለመደ ብቃቱን ቢያሳየን አይደንቀኝም” ይላል።
የፕሪሚዬር ሊጉን 380 ጨዋታዎች የሚገምተው ሱተን ሐሙስ፣ አርብ እና ቅዳሜ የሚደረጉ ፍልሚያዎችን ግምት እንዲህ አስቀምጧል።
ሐሙስ
ክሪስታል ፓላስ ከብራይተን
ክሪስታል ፓላስ ጥሩ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች አሉት። ነገር ግን ጉዳት እየፈተናቸው ነው። ኤቤሬቺ ኤዜ እና ጆርዳን አዮ ለዚህ ጨዋታ እንደሚደርሱ እገምታለሁ።
ንስሮቹ ክሪስታል ፓላሶች ባለፈው ሳምንት ወደ ማንቸስተር ሲቲ ሜዳ አቅንተው አቻ በመውጣት ጥሩ ድል ሲያስመዘግቡ ብራይተን በበኩሉ ከአርሰናል ጋር በነበረው ጨዋታ ያሳየን ብቃት ደካማ ነበር።
ብራይተን ባለፈው የውድድር ዘመን ያሳዩንን ዓይነት ነገር እያሳዩን አይደለም። በአውሮፓ ሊግ እየተጫወቱ መሆናቸው አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል።
ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ይመስለኛል። ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ተገናኝተው ከስድስት ጨዋታዎች በአራቱ 1 አቻ ተለያይተዋል።
ግምት፡ 1 - 1
አርብ
አስተን ቪላ ከሼፊልድ ዩናይትድ
ሼፊልድ ዩናይትድ በተዓምር ካልሆነ በቀር በቪላ ሜዳ ነጥብ ያገኛሉ ብዬ አልገምትም።
እርግጥ ነው ሼፊልድ ዩናይትድ ክሪስ ዋይልደርን አሠልጣኝ አድርገው ከቀጠሩ በኋላ የተወሰነ ለውጥ አምጥተዋል። ነገር ግን አሁን የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ናቸው።
በሌላ በኩል ቪላ እየበረረ ነው። ባለፈው ሳምንት በብሬንትፈርድ ሜዳ ከኋላ ተነስተው ማሸነፍ ችለዋል። በሜዳቸው የሚነካቸው አልተገኘም።
እርግጥ ነው በቪላ ፓርክ ከተሸነፉ ብዙ ጊዜ ሆኗቸዋል። አንድ ቀን ማሸነፋቸው አይቀርም። ከሼፊልድ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ግን አይደለም።
የኡናይ ኤምሪ ቡድን ይህን ጨዋታ ካሸነፉ እና ሊቨርፑልና አርሰናል አቻ ከወጡ የገና በዓልን ሊጉን በመምራት ያሳልፋሉ።
ግምት፡ 2 - 0
ቅዳሜ
ዌስት ሀም ከማንቸስተር ዩናይትድ
ማንቸስተር ዩናይትድ ወደ አንፊልድ ተጉዘው ዘግተው በመጫወት ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል። ይህን በዌስት ሀም ሜዳ ይደግሙታል? አይመስለኝም።
እኔ እንደሚመስለኝ ዌስት ሀም ይህን ጨዋታ ያሸንፋል። ዌስት ሀም ባለፈው ሳምንት ከዎልቭስ ጋር ያደረጉት ጨዋታ አስደናቂ ነበር።
እኔ የኤሪክ ቴን ሃግ ቡድን ምንም አልመሰጠኝም። የዩናይትድ ደጋፊዎች ቡድኑ ከሊቨርፑል ጋር አቻ መውጣቱ ሊያታልላቸው አይገባም። እንደውም ይህ የሚያሳየው ዩናይትድ ምን ያህል እንደወደቀ ነው።
ግምት፡ 2 - 1
ፉልሀም ከበርንሊ
ፉልሀም ያለ አጥቂው ራውል ሂሜኔዝ ነው ይህን ጨዋታ የሚያደርገው።
ሂሜኔዝ ከኒውካስል ጋር በነበረው ጨዋታ ቀይ ካርድ መመልከቱ ይታወሳል። ነገር ግን ቡድኑ ያለሱም ቢሆን ጎል ማስቆጠር ይሳነዋል ብዬ አልገምትም።
ስለበርንሊ በየሳምንቱ ተመሳሳይ ነገር እያልኩ እንደሆነ ይሰማኛል። ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አላስብም።
ከዚህ ጨዋታ አንድ ነገር ማግኘት ይፈልጋሉ። ነገር ግን በርንሊ አሁን ባለው አቋም ፕሪሚዬር ሊጉን የሚመጥን ክለብ ነው ብዬ አላምንም።
ግምት፡ 2 - 0
ሉተን ከኒውካስል
የሉተን አምበል ቶም ሎክየር ባለፈው ሳምንት በነበረው ጨዋታ ሜዳ ላይ ተዝለፍልፎ ወድቆ አሁን በመልካም ጤንነት ላይ መገኘቱ መልካም ዜና ነው።
ሉተን ጨዋታው ከመቋረጡ በፊት በቦርንመዝ ሜዳ ያሳዩት ጨዋታ መልካም ነበር። ነገር ግን ከስምንት ጨዋታዎች አንድ ብቻ ነው ያሸነፉት።
ቢሆንም ኒውካስልም ከሜዳ ውጭ እያሳዩ ያለው አቋም የሚያስተማምን አይደለም።
የኤዲ ሃው ቡድን ከአንድ እስከ አራት ማጠናቀቅ ከፈለገ ከሜዳ ውጭ ከሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ውጤት ማግኘት አለበት።
ኒውካስል ከዚህኛው ጨዋታ በጠባብ የጎል ልዩነት ሙሉ ነጥብ እንደሚያገኝ እገምገታለሁ።
ግምት፡ 1 – 2
ማንቸስተር ሲቲ ከ ብሬንትፈርድ
ይህ ጨዋታ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። ሲቲ ወደ ሳዑዲ ተጉዞ በፊፋ ክለብ ዎርልድ ካፕ ከብራዚሉ ቡድን ፍሉሚነንስ ጋር ለፍጻሜ ይጫወታል።
ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ቦርንመዝ
ፎረስት በአዲስ አሰልጣኝ ይመለሳሉ። ስቲቭ ኩፐር በመጨረሻው ጨዋታቸው ቶተነሃምን ጥሩ አድርገው ፈትነው ነበር። ይህ ጨዋታ ስቲቭ ኩፐርን ከመባረር ያስቀራል የሚል ግምት ነበረኝ።
አዲሱ አሰልጣኝ ኑኖ ኤስፒሪቶ ሳንቶስ በድል ይጀምሩ ይሆን? ቀላል አይሆንላቸውም። በተለይ ድንቅ ብቃት እያሳ ያለውን ዶሚኒክ ሶላንኬን የያዘው ቦርንመዝ ጥሩ አቋም ላይ ነው የሚገኘው።
ግምት፡ 1 – 1
ቶተነሃም ከ ኤቨርተን
ይህ አስደናቂ እና ለመገመት ከባድ የሆነ ጨዋታ እንደሆነ አስባለሁ።
ሾን ዳይሽ በኤቨርተን እጅግ አስደናቂ ሥራን እየሰሩ ነው። እስካሁን ባየነው አቋም የዓመቱን ምርጥ አሰልጣኝ ምረጥ ብባል ቀዳሚ ምርጫ ሾይን ዳይሽ ነው።
ሰፐርስም ቢሆን ጥሩ እየተጫወተ ያለ ቡድን ነው። አንዳንዴ ደግሞ ሳይጠበቅ የደከመ አቋም ያሳያል። በዚህ ጨዋታ ደግሞ ቢሱማን በቅጣት አጥተዋል።
ቶተነሃም በቀላሉም ባይሆን እንደሚያሸንፍ፤ ኤቨርተንም ጎል እንደሚያስቆጥር እገምታለሁ።
ግምት፡ 3-1
ሊቨርፑል ከ አርሰናል
አርሰናል ባለፈው ሳምንት በአንፊልድ እንዳየነው ዩናይትድ ሆኖ አይቀርብም። መድፈኞቹ እንደባለፈው የውድድር ዓመት ባይሆንም አሁንም ግን በተጋጣሚ ቡድን ላይ አደጋ መፍጥር ይችላሉ።
ብዙዎች እንደሚሉት ሁነኛ የፊት መስመር አጥቂ ይጎድላቸዋል። እኔም በዚህ እስማማለሁ። ይሁን እንጂ የሁሉም መስመር ተሰላፊዎች ጎል ማስቆጠር ይችላሉ።
ሊቨርፑል በሜዳው ይሸነፋል ብዬ መገመት ይከብደኛል። ይህ በጠባብ ውጤት የሚጠናቀቅ ጨዋታ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ሊቨርፑል በሜዳው እንደመጫወቱ አቻ መውጣትን የሚፈልግ አይመስለኝም።
ግምት፡ 2 -1
ዕሁድ
ዎልቭስ ከ ቼልሲ
ዎልቭስ ባለፈው ሳምንት ከዌስት ሃም በነበራቸው ጨዋታ የነበራቸውን ንቁ የሆነ እንቅስቃሴ ማስቀጠል ተስኗቸው ተመልክቻለሁ። በዚህ ጨዋታ ግን በደጋፊዎቻቸው ታግዘው ጥሩ ይጫወታሉ ብዬ እጠብቃለሁ።
የቼልሲ ጉዳይ ግን ግራ የገባው ነገር ነው። ከሞሪሲዮ ፖቼቲኖ ቡድን ምን መጠበቅ እንዳለብኝ እንኳ አላውቅም። ጨዋታው አቻ ይጠናቀቃል ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ 1 – 1