የቢቢሲ የመቶ ዓመት ዕድሜ እና 10 ትውስታዎች

ቢቢሲ በዓለም ላይ ካሉ ትላልቅ የመገናኛ ብዙኃን መካከል አንዱ ነው።
የተመሠረተው እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በጥቅምት 18/1922 በለንደን ከተማ ነበር።
1. የመጀመሪያው የቢቢሲ ራዲዮ ጣቢያ

በኅዳር 14/1922 (እአአ) በለንደን ከተማ ራዲዮ ሥርጭት ጀመረ።
የመጀመሪያ ዜናው 18፡00 ጂኤምቲ ላይ ከዜና ወኪል የተቀበለውን ዜና አሰራጨ። ዜናውን ተከትሎ የአየር ትንበያ ተላለፈ።
ዜናዎቹ የተነበቡት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የፕሮግራሞች ዳይሬክተር በነበሩት አርተር ባሮውስ ነበር።
ባሮውስ ዜናውን ሲያነቡ እያንዳንዱን ዜና ሁለት ጊዜ ነበር። መጀመሪያ ፈጠን ቆፍጠን ብለው፣ ቀጥለው ደግሞ ረጋ ሰከን ብለው።
ይህን ያደረጉት አድማጮች ጠቃሚ መረጃዎችን ጽፈው እንዲመዘግቡ ጊዜ ለመስጠት ነበር።
2. የቢቢሲ ዓለም አቀፍ መርሐ ግብር መጀመር

በታኅሣሥ 19/1932 (እአአ) ንጉሥ ጆርጅ 5ኛ የመጀመሪያውን የገና በዓል ንጉሣዊ መልዕክት ለዩናይትድ ኪንግደም በከፊል ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አደረሱ።
በዚህ ሥርጭት ወቅት የንጉሡ “ይህ መልዕክት በብሪቲሽ ዘውዳዊ ግዛት መንግሥት ሥር ላላችሁ ወንዶችና ሴቶች፣ በበረዶና በበረሃ እንዲሁም በባሕር ምክንያት ሩቅ ላላችሁ ድምጼ ብቻ ነው ይህን ሁሉ አቆራርጦ ሊደርሳችሁ የሚችል፤ መልዕክቴ በአየር ሞገድ ይድረሳችሁ” ብለው ነበር።
ይህ ንግግር የዚያን ጊዜውን የቢቢሲ ዘውዳዊ መንግሥት አገልግሎት፣ የአሁኑን የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት መጀመርን አበሰረ።
የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ በቋንቋ ስብጥር፣ በተደራሽነት እና በሚያካልለው ቦታ የሚስተካከለው ጣቢያ የለም።
በቴሌቪዥን፣ በበይነ መረብ እና በራዲዮ በ40 የተለያዩ ቋንቋዎች ሥርጭቱን በየዕለቱ ያደርሳል።
3. የቢቢሲ ማይክሮፎን

ለሥርጭት የሚሆኑ ማይክሮፎኖች በ1930ዎቹ ውድ ነበሩ። ቢቢሲ ማርኮኒ ከሚባል ኩባንያ ጋር የራሱን ሞዴል ለማግኘት በጋራ መጣመር ነበረበት።
በ1934 ታይፕ-ኤ የሚባሉ ማይክሮፎኖች የራዲዮ ሥርጭት ላይ ዓይነተኛ ለውጥ አመጡ።
በዘመን ውስጥ እነዚህ ማይክራፎኖች እየተሻሻሉ ቀጥለው በኋላ ላይ የቢቢሲ ማይክራፎኖች የሚል ስም ያዙ። በብዙ የብሪቲሽ ድራማና ፊልሞች ላይ አሁንም ድረስ በስፋት ይታያሉ።
4. የቢቢሲ አረብኛ ቋንቋ

በዓለም አቀፉ መርሐ ግብር ቋንቋዎች ሁሉ አረብኛን የቀደመ የለም። ይህም እንደ አውሮፓዊያኑ በ1938 ነበር።
ግብፃዊው አሕመድ ከማል ሱሩር ኢፈንዲ ከግብፃ ራዲዮ ለዜና አቅራቢነት ተመለመለ።
የርሱ መምጣት በአንድ ጊዜ ቢቢሲ አረብኛን አገነነው።
ጋዜጠኛ ኢፈንዲ በዓረቡ ዓለም እጅግ ተወዳጁ የራዲዮ ዜና አቅራቢ ሆነ።
በቀጣይ ዓመታት በርካታ ቋንቋዎች ቢቢሲን ተቀላቀሉ።
ይህም መጀመሪያ በራዲዮ በኋላ ላይ ደግሞ በቴሌቪዥን መርሐ ግብሮች ተግባራዊ የሆነ ነበር።
ቢቢሲ የበይነ መረብ ሚዲያ ብቅ ያለው ግን ዘግይቶ እንደ አውሮፓውያኑ በ1997 ነበር።
የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ብቅ ማለት ደግሞ ቢቢሲ ኒውስ እና ቢቢሲ ዎርልድ ሰርቪስ በመላው ዓለም በብዙ ቋንቋዎች ተደራሽ እንዲሆን አስችሎታል።
ዛሬ ቢቢሲ በመቶኛ ዓመቱ ዋዜማ ላይ ሆኖ ቢቢሲ ዎርልድ ሰርቪስ አዲስ አቅጣጫን እየያዘ ነው። አዲሱ አቅጣጫ ቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ሙሉ ትኩረቱ ዲጂታል-መር ይዘት እንዲኖረው ማስቻል ነው።
5. የቢቢሲ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ፕሮዲዩሰር

ኡና ማርሰን በቢቢሲ ታሪክ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ፕሮዲዩሰር በመሆን ታሪክ ሠርታለች።
ማርሰን ትውልዷ ጃማይካ ነው። ቢቢሲ ሥራ ስትጀምር የተዋጣላት እና ልምድ ያላት ጋዜጠኛ ነበረች። ይህም እንደ አውሮፓዊያኑ በ1939 የሆነ ነበር።
6. የ2ኛው የዓለም ጦርነት መገባደድ እና ቢቢሲ

በግንቦት 01/1945 (እአአ) ቢቢሲ የጀርመኑ አዶልፍ ሒትለር ራሱን ማጥፋቱን በዜና አወጀ።
ይህ በሆነ በነገታው ማታ 1፡00 ሰዓት ላይ ይተላለፍ የነበረ መደበኛ መርሐ ግብር እንዲቋረጥ ተደርጎ ሰበር ዜና ተነገረ። ይህም የጀርመን ጦር በጣሊያን አገር እጅ መስጠቱን የሚያበስር ነበር።
በግንቦት 4 ደግሞ በዴንማርክ እጅ ሰጡ። ይህም የጦርነቱ ማብቂያን አመላከተ።
ከቀናት በኋላ ዊንስተን ቸርችል የአውሮፓ የድል ቀን መሆኑን ያበሰሩት በቢቢሲ ነበር።
ይሁንና ብዙ ሰዎች በደስታ ሰክረው ስለነበር የቸርችልን መልዕክት ከመስማት ይልቅ ደስታቸውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ ተመው ነበር።
7. ቢቢሲ በሳተላይት ተሰራጨ

በአውሮፓውያኑ በ1967 ‘አወር ዎልድ’ የተሰኘው የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ታሪክ ሠራ።
ይህ መርሐ ግብር ከመሠራጨቱ በፊት የሳተላይት ቴሌቪዥን ጥቂት አገሮችን ነበር የሚያስተሳስረው። ይህም ለሙከራ ያህል የሚደረግ ነበር።
በነገራችን ላይ ቢቢሲ ከፍተኛ ጥራት (ሃይ ዴፊኒሽን) ምሥል በቴሌቪዥን ለማስተላለፍ የመጀመሪያው ጣቢያ ነበር።
አወር ዎርልድ መርሐ ግብር ግን ከዚህ በተለየ ታሪክ የሠራው በቀጥታ ቴሌቪዥን ከተለያየ አህጉር ያሉ ሰዎችን በሳተላይት አገናኝቶ ማሰራጨቱ ነበር።
ዘ ቢትልስ በኋላ ላይ ዝነኛ የሆነውን ሙዚቃቸውን ‘ኦል ዩ ኒድ ኢዝ ላቭ’ የሚለውን ሥራቸውን አቀረቡ። ይህ ሙዚቃ በቢቢሲ መታየቱን ተከትሎ ከፍተኛ ዝናን ተጎናጸፈ።

ይህ መሳካቱ በኋላ ላይ በ1985 (እአአ) ለኢትዮጵያ ረሀብ ዓለም እገዛ እንዲያደርግ ያስቻለውን ‘ላይቭ ኤይድ’ ለማሰራጨት አስቻለ።
ይህ ከብዙ መድረኮች የተላለፈው የሙዚቃ ኮንሰርት የተሰናዳው በቦብ ጌልዶፍ እና ሜጄ ኤዮ ነበር።
ቢቢሲ ለዚህ ኮንሰርት መሳካት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ይህን ኮንሰርት በ60 አገራት የሚገኙ 400 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች በቀጥታ እንዲመለከቱት አስችሏልና።
8. የዣንጥላው ግድያ

ከላይ ያለው ምሥል ጋዜጠኛ ጆርጅ ማርኮቭ የተገደለበት መሣሪያ ነው። ዣንጥላ ይመስላል።
በመስከረም 07/1978 (እአአ) ማርኮቭ ወደ ቢቢሲ ቡሽ ሐውስ ቢሮ፣ ለንደን እየሄደ ነበር። አንድ ሰው ከጀርባው በጥላው እጀታ ወጋ አድርጎት ሸሸ።
ማርኮቭ ሦስት ቀናት ሆስፒታል ቆየና ሞተ።
እርሱ እንደሚያምነው በቡልጋሪያ ደኅንነቶች ተመርዞ መገደሉን ነው።
የግድያው መልክ ብዙ አነጋገረ። ጋዜጠኛው የቡልጋሪያን ኮሚኒስት አስተዳደር ክፉኛ ይተች ነበር።
ኬጂቢ በነገሩ እጁን ሳያስገባ አልቀረም።
በኋላ ላይ የዚህ ጋዜጠኛ ገዳይ በምሥጢር ስሙ ፒካዲሊ የሚባል ሰላይ እንደነበር ተደረሰበት።
ይሁንና ገዳዩ ለፍርድ አልቀረበም።
9. የአፍሪካ ስፖርት ኮከብ ሽልማት

ይህ ዋንጫ ለስፖርት ሰዎች የሚሰጥ ዓመታዊ የቢቢሲ ሽልማት ነው። በ2018 ግብፃዊው መሐመድ ሳላህ ወስዶታል።
ከ2001 (እአአ) ጀምሮ ለእግር ኳስ ተጫዋቾች ብቻ ነበር የሚሰጠው። ከ2012 ጀምሮ ግን ለሁሉንም ስፖርት ዘርፍ እንዲያካትት ተደረገ።
ይህ ዋንጫ መጀመሪያ ቅርጹ የተሠራው በሴራሊዮን የልጅ ወታደር በነበረ ሰው መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
10. ዴቪድ አተንበሮ እና ቢቢሲ

ዘጋቢ ፊልሞችን ያየ ዴቪድን የማያውቅ አይኖርም። አስገምጋሚ ድምጹ በሚሊዮኖች እዝነ ልቦና ውስጥ ዛሬም አለ።
የዱር አራዊት ዘጋቢ ፊልሞችን በመተረክ ይታወቃል። ይህ ዘጋቢ ፊልም ለ80 ዓመታት የዘለቀ ነው።
ብሉ ፕላኔት፣ ናቹራል ዎርልድ በሚሊዮኖች ታይተውለታል።
ዴቪድ በቢቢሲ አቅራቢ የሆነው በ60ዎቹ ነበር።
የእርሱ ሥራዎች በመላው ዓለም ይታወቃሉ።
በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ አስገንዛቢ ሥራዎቹ ይበልጥ ይታወቃል።
የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት የ2021 ተሸላሚም ነበር።












