የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች፡ ከአሠልጣኝ እስከ ወኪል ‘የሚቀራመቱት’ የተጫዋቾች ደመወዝ

አምና የቡድኑ ማገርና ምሰሶ ሆኖ ደረቱ ላይ የተለጠፈውን አርማ እየሳመ ያያችሁት ተጨዋች ዘንድሮ የተቀናቃኝ ክለቡ አምበል ሆኖ ቢያዩት ሊገርምዎት አይገባም።
ምክንያቱም ይህ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ነው።
በአንድ መስኮት 11 ተጫዋች ማስፈረም ከመለመድ አልፎ 17 ተጫዋቾችን ማስኮብለል አዲስ ባሕል ሆኗል።
ኳስ እየተመለከቱ የጨዋታው ተንታኞች [ኮሜንታተር] ሃያ ሁለቱንም ተጫዋቾች የቀድሞ ክለባቸውን እየገጠሙ ይገኛሉ ቢልዎ አያስደንቅም።
ምክንያቱም ይህ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ነው።
ባለፈው ዓመት ዋንጫ ያነሳ አሊያም ሁለተኛና ሶስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ቡድን 8 እና 9 ተጫዋቾች ሲያስፈርም፤ የክለቡ አከርካሪ የሆነውን ተጫዋች ሲሸጥ ቢያሰተውሉ ግራ እንዳይጋቡ።
ምክንያቱም. . .
ለዚህ አንደኛውና ዋነኛው መንስዔ ሶልዲ ነው።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የተጫዋቾች ደመወዝ 50 ሺህ ገባ ሲባል ብዙዎች ‘ይህ ሁላ ገንዘብ. . .’ ብለው ተደንቀዋል።
ዘንድሮ 50 ሺህ ከጨዋታ በኋላ ለኪስ ተብሎ የሚሰጥ የላብ ገንዘብ መሆኑን እየሰማን ነው።
የአንድ ተጫዋች ዋጋ 7 ሚሊዮን ብር ደርሷል፤ 10 ሚሊዮን ብር ያወጡም አሉ።
ለመሆኑ የፕሪሚዬር ሊጉ ክለቦች ከካዝናቸው እየመዠለጡ ሚሊዮኖች የሚያፈሱት ከየት አምጥተው ነው? ተጫዋቾችስ ይህ ገንዘብ ኪሳቸው ይገባልን?
‘የምትሰማው ክፍያ ጆሮህን ያስይዝሃል’
በተጠናቀቀው የዝውውር መስኮት ክለቦች በርከት ያሉ ተጫዋቾች አስፈርመዋል፤ ውል አድሰዋል፤ ከታችኛው ሊግም አስመጥተዋል።
ከተስፋና ከታዳጊ ቡድን ያደጉ ተጫዋቾችንም እየተመለከትን ነው።
ከውጭ ሃገራት በተለይ ደግሞ ከምዕራብ አፍሪካ ሃገራት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ቁጥርም ከፍ ብሏል።
በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረም ሊደረስበት ያልቻለው ወልቂጤ ከተማ ነው። ወልቂጤ 17 ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።
ዝቅተኛው ደግሞ [ሶስት ተጨዋቾች] ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው።
በቀድሞ ስሙ መከላከያ በዘንድሮው ስሙ መቻል፤ ከነዓን ማርክነህን ጨምሮ 16 ተጨዋቾችን አስፈርሟል።
ይህ ሁሉ ተጫዋቾች በአንድ መስኮት አስፈርሞ እንዴት ነው ዘላቂ የሆነ ቡድን መመሥረት የሚቻለው የሚለውን ለጊዜው ወደጎን እንተውውና የተጨዋቾች ዝውውር ዋጋና ደመወዝ ላይ እናተኩር።
"ተጫዋቾቹ የሚዘዋወሩበት መንገድ ምንም ግልፅ አይደለም። የክፍያው ሁኔታ ትክክለኛ ነው ብለህ ለመገመት ትቸገራለህ" ይላል የስፖርት ጋዜጠኛው አብረሃም ተክለማርያም ።
"አንዳንዱ የምትሰማው ክፍያ ጆሮህን ያስይዝሃል። አንድ ተጫዋች ለሁለት ዓመት 10 ሚሊዮን ብር እንደተከፈለው ሰምቻለሁ።"
በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ዝቅተኛው የተጫዋች ዝውውር ቆይታ አንድ ዓመት ነው፤ ከፍተኛው ደግሞ አምስት ዓመት።
ነገር ግን አንድ ተጫዋች ከዚህ በላይ በሆነ ዋጋ ሊፈርም አይችልም አሊያም ደመወዙ ከዚህ ሊያንስ ወይም ሊበልጥ አይገባም የሚል ሕግ የለም።
እርግጥ ይህ አብዛኛው ዓለም የሚመራበት ሕግ ነው። ነገር ግን እግር ኳስ ተመንድጓል በሚባልበት የዓለም ክፍል ‘ፋይናንሻል ፌር ፕለይ’ የተሰኘ መመሪያ አለ።
ይህ መመሪያ ዋነኛ ዓላማው ክለቦች ስኬትን ሽጠው ከገበያቸው በላይ ወጪ እንዳያደርጉ የሚያግድ ነው። ይህ ሕግ ክለቦች የፋይናንስ አዘቅት ውስጥ እንዳይገቡ የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት።
የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የክለቦችን የገቢ ምንጭና ወጪ የሚቆጣጠርበት መመሪያ ይኖረው እንደሆን ግልጽ አይደለም።
የተጫዋቾች ዝውውርን በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡን የደውልንላቸው የሊጉ አክሲዮን ማሕበር ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሰይፈ "ይህ የፌዴሬሽኑ ጉዳይ ነው" የሚል ምላሽ ነው የሰጡን።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ‘ፋይናንሻል ፌር ፕለይ’ አሊያም የክለቦች ፍትሐዊ ወጪና ገቢን የሚቆጣጠርበት ኦፊሴላዊ መመሪያ እንደሌለው አብረሃም ይናገራል።
"ኢትዮጵያ ውስጥ ‘ፋይናንሻል ፌር ፕሌይ’ በመባል የምናውቀው ሕግ የለም። ነገር ግን ለምሳሌ ‘ሳለሪ ካፕ’ የሚባል የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ የወጣ ሕግ ነበር። ይህ ሕግ የደመወዝ ጣራ 50 ሺህ ብር እንዲሆን ወስኖ ነበር። ቅጥ ያጣ የዝውውር ገንዘብን ለመግታት በሚል ነበር ይህ ሕግ የወጣው።"
አብርሃም፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት የስፖርት ኮሚሽን ባሠራው ጥናት መሠረት የኢትዮጵያ ክለቦች አጠቃላይ ዓመታዊ ወጪ ከ2 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያስታውሳል።
ጥያቄው እግር ኳስ የወጪውን ግማሽ ያህል እንኳ ገቢ እያደረገ ነው ወይ? ነው።
አብርሃም ‘አይመስልኝም’ ይላል። "ለምሳሌ በአምናው [2014] የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ተሳታፊ ከነበሩ ክለቦች ከሶስት ወይም አራት ክለቦች በቀር ሁሉም የደመወዝ ክፍያ ችግር ነበረባቸው።"
ፌዴሬሽኑ በክለቦችና በተጫዋቾች መካከል መቃቃር ሲፈጠር ከማደራደር በቀር ሌላ ምንም ሥልጣን እንደሌለው አብረሃም ይናገራል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀን ፌዴሬሽኑንም ሆነ ፕሪሚዬር ሊጉን ጠንቅቀው ከሚያውቁ ሰዎች አንዱ በዚህ ይስማማል።
የተጫዋቾች ደመወዝ 50 ሺህ ብር በነበረበት ወቅት "ትላልቅ የሚባሉ ተጫዋቾችን ጨምሮ ብዙዎች በጎን ተጨማሪ ገንዘብ ይቀበሉ ነበር" ይላል።
"50 ሺህ ብሩን ፌዴሬሽኑ ያፀድቅልሃል። ለምሳሌ ይህን ያህል ጎል ካስቆጠርኩ ይህን ያህል ይከፈለኛል የሚል ካለም ፌዴሬሽኑ ያፀድቃል። ነገር ግን ተጨዋቹና ክለቡ ከዚህ ውጭ ሌላ ድርድር ያደርጋሉ። 200 እና 300 ሺህ የሚበሉ ነበሩ።"
በክለቡና ተጫዋቹ መካከል አለመግባባት ሲኖር ግን ፌዴሬሽኑ ከማደራደር ውጭ ምንም ማድረግ እንደማይችል ይናገራል። ለዚህም ነው አንዳንድ አለመግባባቶች ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት የሚሄዱት ሲል ያስረዳል።
በቀደመው ግዜ፤ ማለትም የተጫዋቾች ደመወዝ 50 ሺህ ብር በነበረበት ወቅት አንዳንድ ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው ብድር ይሰጡ እንደነበር ይህ ውስጥ አዋቂ ይናገራል።
"ለምሳሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፊርማው ገንዘብ የተወሰነውን በብድር መልክ ይሰጥ ነበር።"
ዘንድሮስ? የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ አሁን አሁን ግን አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ሙሉውን ገንዘብ ቀድመው ይቀበላሉ። ከዚያ በየወሩ የሚደርሳቸው ድጎማ [ኢንሴንቲቭ] ነው።"
‘ከፌዴሬሽኑ ጋር ተጋጭቼ ክለቤ እንዲጎዳ አልፈልግም’ ብለው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን የክለብ ሥራ አስኪያጅ "አሠራሩ [ከፍተኛ ክፍያው] ትክክል አለመሆኑን ሁሉም ሰው ያውቀዋል" ይላሉ።
"የፕሪሚዬር ሊግ አክሲዮን ማሕበሩ በጠራው ስብሰባ ላይ ይህን ሐሳብ አንስተናል። ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ ዓመቱ ሲጀምር ገንዘባቸውን ያገኛሉ። እኛ ደግሞ በየወሩ ለተጫዋቾች ደመወዛቸውን እንከፍላለን።"
አብርሃም፤ ከታችኛው ሊግ ወደ ፕሪሚዬር ሊግ የሚመጡ ተጫዋቾች እንዲሁም ከተስፋና ታዳጊ ቡድን የሚያድጉ ተጫዋቾች የሚያገኙት ደመወዝ አነስተኛ ነው ይላል።
ይህን ለማጣራት በቅርቡ ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ ካደጉ መካከል ወደ አንዱ ክለብ ሥራ አስኪያጅ ስልክ ደወልን። ስማቸው ይፋ እንዳይሆን የጠየቁን ሥራ አስኪያጁ "አዎ እውነት ነው" ይላሉ።
"በጣም ዝቅተኛ ደመወዝ ከሚከፍሉት መካከል ነው የኛ ክለብ። ግን ምን ማድረግ እንችላለን" ሲሉ ሥራ አስኪያጁ ምሬታቸውን ያሰማሉ።
"የሌሎቹ ክፍያ ከፍ ማለቱ ይጎዳናል? አዎ ይጎዳናል። 300 እና 500 ሺህ ለጠየቀ ሁሉ ከፍለን የማይሆን ነገር ውስጥ መግባት አንፈልግም። እኛ የማንቀበለው፤ የማንጓዝበት ራሱን የቻለ ሚስጥር አለው ይህ ክፍያ። እንጂ ተጫዋቹ ያን ሁሉ ገንዘብ ያገኘዋል ብለህ አትጠብቅ።"
ተጫዋቹ ሙሉውን ገንዘብ ካላገኘው ማነው ተጠቃሚ?
![የፋሲል ከነማው አምሳሉ ጥላሁን [በስተግራ] የመቻል ተጫዋቹ ሳሙዔል ሳሊሱ [በስተቀኝ]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/5971/live/c16564f0-556c-11ed-ac87-630245663c6a.jpg.webp)
‘እንቆቅልሽ ሆኖብናል’
በተጫዋችነት ዘመኑ ለኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ለብሔራዊ ቡድኑ የተሰለፈው ኤፍሬም ወንድወሰን አሁን የፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ማሕበር ምክትል ፕሬዝደንት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
"እግር ኳሱ እያደገ በመምጣቱ የገንዘብ መጠኑም ከፍ ብሏል" ይላል ኤፍሬም።
"እግር ኳስ እንደ በፊቱ በሳምንት ሁለትና ሶስት ቀን የሚሠራ ሳይሆን የሙሉ ጊዜ ሥራ ሆኗል። እግር ኳሱ በዚህ ደረጃ አድጓል አላደገም ሌላ ጥያቄ ነው።"
የተወሰኑ የክለብ አመራሮች፣ የተወሰኑ አሠልጣኞች እና በመሃል ባሉ ሰዎች ምክንያት ተጫዋቾች የሚገባቸውን ገንዘብ እያገኙ እንዳልሆነ ተጫዋቾቹ ይነግሩናል ይላል ኤፍሬም።
"ማስረጃ አምጡልን፤ የሕግ ባለሙያ ስላለን ድጋፍ እናደርጋለን ስንላቸው ግን ፈቃደኛ አይሆኑም። ፈሪ ሆነህ እንድትጫወት ነው የሚፈለገው።"
ኤፍሬም ተጫዋቾቹ ጉዳዩን ቢያጋልጡ ሥራቸውን ሊያጡ ይችላሉ ይላል።
"ከአንድ ክለብ አሠልጣኝ ጋር ካልተስማማህ ወደሌላ ክለብ እንዳትሄድ ትደረጋለህ። ብትጎዳም ቤተሰብ አለብኝ፣ ቤት ኪራይ ደርሶብኛል ብለህ አንገትህን ደፍተህ እንድትጫወት ትደረጋለህ። ምክንያቱም ክለቦችና አሠልጣኞች እንዲሁም በመሃል ያሉ ሰዎች ይተባበሩብሃል።ተጫዋቾች የሚገባቸውን ገንዘብ አለማግኘታቸው ልናጠራው ያልቻልነው እንቆቅልሽ ሆኖብናል።"
አብርሃምም በጋዜጠኝነት ዘመኑ እንዲሁ ተጫዋቾች በደል ደርሶብናል ብለው ነግረውት ነገር ግን ጉዳዩን አደባባይ ለማውጣት ሳይችሉ እንደቀሩ ያስታውሳል።
"እከሌ የሚባል አሠልጣኝ ይህን ያህል ገንዘብ ተቀብሏል፤ እከሌ ለሚባል ሥራ አስኪያጅ ይህን ያክል ገንዘብ ሰጥተነዋል ይሉናል። ይህ መረጃ ነው። ማስረጃ ለምሳሌ ባንክ ያስገቡበት ደረሰኝ ስትላቸው ያንን ለማድረግ ፈቃደኛ አይደሉም። እኔ እንኳ ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ቴሌቪዥንም ራድዮም ላይ ላቀርባቸው ተቀጣጥረን የጠፉብኝ አሉ።"
ውስጥ አዋቂ ምንጫችንም በአንድ ስብሰብ ላይ የተጫዋቾች ማሕበር ፕሬዝደንት [ዮሃንስ ሳሕሌ] "ተጫዋቾቹ ገንዘቡን አያገኙትም ሲሉ ሰምቻለሁ" ይላል።
"ይታወቃል እኮ" ይላል ምንጫችን።
"አንድ ተጫዋች ሲሰጥ ነው የሚሳካለት። ለአሠልጣኙ ደመወዙን ሰጥቶ ነው የሚገባው። ከአንድ አሠልጣኝ ጋር ክለብ የሚቀያይሩ ብዙ ተጫዋቾች የምታየው ለዚህ ነው። ብቃቱ ጥሩም ይሁን፤ አይሁን ተጨዋቹ አብሮት ይዞራል። አሠልጣኝ፤ የቡድን አመራር. . . ሁሉም ተነካክቷል።"
የተጫዋቾች ማሕበር ምክትል ፕሬዝደንት ኤፍሬምም ይህ እውነት ነው ይላል።
"ይህን ያህል ለአሠልጣኝ፤ ይህን ያህል ደግሞ ለኔ ትሰጠኛለህ ተብሎ ቅድመ ክፍያ ሁሉ ይፈፀማል። ነገር ግን ቀጥታ ሳይሆን በወኪሎች አማካኝነት ነው የሚነግረው።"
ፌዴሬሽኑ ይህን ለመግታት ከጥቂት ጊዜ በፊት ፈቃድ ላላቸው ወኪሎች ብቻ ፈተና አዘጋጅቶ እንደነበር ውስጥ አዋቂው ለቢቢሲ ይናገራሉ።
አልፎም እያንዳንዱ ተጫዋች ወኪል እንዲኖረው የሚል መመሪያ አውጥቶ እንደነበር ያስታውሳል። ይህ የፊፋ መመሪያ እንደሆነም ይጠቁማል።
"ፌዴሬሽኑ ሕግ ለማውጣት ጎበዝ ነው። ነገር ግን የሚቆጣጠርበት መንገድ የለውም። ለምሳሌ በቅርቡ በተዘጋው የዝውውር መስኮት ወቅት የወኪሎች ፈተና አልነበረም።"
አብረሃም፤ በተለይ የከነማ/ከተማ አስተዳደር ክለቦች ከገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ ስማቸው እንደሚነሳ ይናገራል።
በቅርቡ ወደ ፕሪሚዬር ሊግ ያደገው ክለብ ሥራ አስኪያጅም ይህን ይላሉ።
"በደመወዝ አከፋፈል ከከተማ ቡድኖች ጋር መወዳደር የማይታሰብ ነው።"
"እስከ ዓመቱ መጨረሻ መክፈል ይችላሉ ወይ? እሱ ሌላ ጥያቄ ነው። 3 እና 5 ሚሊዮን ብር እየከፈልክ ውጤት ማምጣት ትችላለህ። እኛ ግን በዚህ እንመራም።"
አብረሃም እንደሚለው የከተማ አስተዳደር ክለብ የቦርድ አባላት የሚታሙበት ሌላኛው ጉዳይ የሚፈልጉት ተጫዋች እንዲመጣ የሚያሳድሩት ጫና ነው።
"አንዳንድ ጊዜ የማይጠቅማቸው ተጫዋች በ6 እና 7 ሚሊዮን ብር ወደ ክለባቸው ይመጣና እነሱ በመሃል ገንዘብ ያገኛሉ" ይላል።
"ይህንን የሚያሳልጡት እነማን ናቸው ካልከኝ አንደኛው የተጫዋቹ ‘ኤጀንት’ [ወኪል] ነው፤ ቀጥሎ ደግሞ ወኪሉንና ክለቡን የሚያገናኝ ደላላ አለ። አሠልጣኝ አሊያም የቴክኒክ ዳይሬክተር፣ የክለብ ሥራ አስኪያጅ ወይም ደግሞ የክለቡ የበላይ ጠባቂ ሊሆን ይችላል።"
ለመሆኑ እነዚህ ክለቦች የገንዘብ ምንጫቸው ምንድን ነው? ገቢና ወጪያቸውን የሚቆጣጠረውስ ማን ነው?

የክለቦች የገቢ ምንጭ
"ገቢህን እኮ የምታውቀው አንድ ነገር ወደ ገበያ ይዘህ ስትወጣ ነው" ይላል አብራሃም።
አብረሃምም ሆነ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀን ምንጫችን እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች በውል የሚታወቅ ገቢ ከዲኤስቲቪ የቴሌቪዥን መብት ሽያጭ የሚያገኙት ገቢ ነው።
"የዲኤስቲቪ ገቢ ከ9 ሚሊዮን ጀምሮ እንደየደረጃቸው የሚከፋፈል ነው። ከዚያ በተረፈ ግን እንኳን የከተማ አስተዳደርና የከነማ ቡድኖች ይቅርና ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና እንኳ በጀታቸው አይታወቅም" ይላል አብረሃም ተክለማርያም።
እንደምሳሌ ኢትዮጵያ ቡናን ያነሳል። ክለቡ ከስፖንሰሮች እንዲሁም ከሌሎች ምንጮች በገንዘብና በዓይነት በሚያገኘው ገቢ ብቻ እንደማይመራ ግልጽ ነው ይላል።
"ለምሳሌ የተጫዋቾች ክፍያን ተመልከት። በዚህኛው የዝውውር መስኮት 12 ገደማ ተጫዋቾች ናቸው የፈረሙት። ደመወዛቸውን ብትደምረው በጣም ብዙ ነው። የኦፕሬሽን ወጪ አለ፤ የጉዞ ወጪ አለ፤ የሚያርፉበት ቦታ ክፍያ አለ፤ ድጎማ አለ። ይህ ወጪ ከስፖንሰርና ከቡና ላኪዎች ብቻ በሚገኝ ገቢ የሚሸፈን አይደለም።"
ስሙን የማንጠቅሰው ምንጫችንም እንዲሁ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሲዳማ ቡናና ወላይታ ድቻን የመሳሰሉ ቡድኖች የገቢ ምንጫቸው ቢታወቅም ወጪያቸው ግን የትየለሌ እንደሆነ ይናገራል።
"በቅርቡ ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ የመጣው ወልቂጤ የከተማ አስተዳደሩ እኔ አልችልም በማለቱ ድጋፍ የሚደረግለት በፕሬዝደንቱ ነው። ፕሬዝደንቱ ገንዘብ ስላላቸው ክለቡ ውጥንቅጥ ውስጥ ሲገባ ከኪሳቸው እያወጡ ብዙ ጊዜ ከፍለዋል።"
ወልቂጤ በቅርቡ በተገባደደው የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት አንጋፋው አሥራት መገርሣን ጨምሮ 17 አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል።
"ክለቦች እንደምናስበው ወረቀት ላይ ያለው ‘ፋይናንሻል ስትራክቸር’ የላቸውም። የከተማ አስተዳደር ክለቦች ሲቸግራቸው ክልሉን ይጠይቃሉ።"
አብረሃም የክልል ክለቦች መሠረታዊ ገበያ ከከተማ አስተዳደርና ነዋሪዎች የሚያገኙት ገንዘብ እንደሆነ ይጠቁማል።
ድሬዳዋ፣ ፋሲል፣ አርባ ምንጭ. . . ከከተማ ነዋሪዎችና ከደጋፊዎች የተወሰነ ገንዘብ እንደሚያገኙ ይናገራል።
"ምን ያክል ሰብስበው በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ አውለዋል? አይታወቅም። የኛ ሃገር ክለቦች ስካፍርና ‘ሬፕሊካ’ ማሊያ ነው እንጂ ሌላ ለገበያ ይዘው የሚወጡት ነገር የላቸውም።"
የመንግሥት ቡድን የሆኑት እነ ኢትዮ ኤሌክትሪክና መድህን በጀታቸውን የሚያገኙት ከመንግሥት ካዝና እንደሆነ ይታወቃል።
ምንጫችን እንደሚለው ከዲኤስቲቪ ከሚገኘው ገቢ 85 በመቶው ለክለቦች የሚከፋፈል ነው። 50 በመቶውን እኩል ይከፋፈሉትና የቀረው ደግሞ እንደወጡበት ደረጃ የሚሰጣቸው ይሆናል።
የዳኛ፣ የጨዋታ አመራር. . . የመሳሰሉትን ወጪዎች የሚሸፍኑት ከዚህ ገቢያቸው እንደሆነ የሚናገረው ምንጫችን አንድ ዳኛ በጨዋታ 3 ሺህ፣ የቀን አበል 2 ሺህ፤ በጠቅላላ 5 ሺህ ብር እንደሚያገኝ ነግሮናል።
ምንጫችን አክሎ ፌዴሬሽኑ ክለቦች ገቢና ወጪያቸውን በኦዲተር አስመዝግበው እንዲያመጡ መመሪያ ቢያስቀምጥም አብዛኛዎቹ ክለቦች ይህን ማድረግ አልቻሉም ይላል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን የክለብ ሥራ አስኪያጅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የራሱን ቁጥጥር ማድረግ አለበት ይላሉ።
የተጫዋቾች ማሕበር ምክትል ፕሬዝደንቱ ኤፍሬም፤ "አብዛኛዎቹ ክለቦች በልምድ እንጂ በዕውቀት ስለማይመሩ ነው ይህ ችግር የተባባሰው" ይላል።
አብረሃም ደግሞ ፌዴሬሽኑ፣ ክለቦች፣ ደጋፊዎች. . . ሁሉም ይመለከተዋል ባይ ነው።













