የኢስታንቡል ነዋሪዎች 'ሕንፃ ይደረመስብናል' የሚል ስጋት ይዟቸዋል

ሜሱት ሚታሊቦግሉ በመኝታ ቤቱ በኩል ያለው ግድግዳ ተሰንጥቆ የመኪና ቁልፍ ይደብቃል።

ስጋት የገባው ሜሱት ቤተሰቡን ይዞ ለ15 ዓመታት ከኖረበት የመኖሪያ ሕንፃ ለመልቀቅ ንብረቱን ሸክፎ ጨርሷል።

ሕንፃው ርዕደ-መሬት ይቋቋም እንደሁ ተሞክሮ ፈተናውን ወድቋል። አያድርገውና የመሬት መንቀጥቀጥ ቢመጣ ሙሉ በሙሉ ከመደርመስ የሚድን አይመስልም።

ስጋት የገባው ሜሱት ብቻ አይደለም። የኢስታንቡል ነዋሪዎች ስጋት ላይ ናቸው።

በደቡባዊ ቱርክ ሁለት ጊዜ የተከሰተው ርዕደ-መሬት የ50 ሺህ ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል። ይህ ደግሞ ለኢስታንቡል ነዋሪዎች ጭንቀት ሆኗል።

15 ሚሊዮን ሰዎች የሚኖሩባት ኢስታንቡል ከ2030 በፊት ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊመታት ይችላል ሲሉ ሙያተኞች ይገምታሉ።

ከተማዋ ካሏት ሕንፃዎች 70 በመቶ ያክሉ ጠበቅ ያለ የሕንፃ ግንባታ ሕግ ከመውጣቱ በፊት የተገነቡ መሆኑ ስጋቱን ከፍ ያደርገዋል።

ከሶስት ወራት በፊት የወጣ አንድ ጥናት ኢስታንቡል የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያጋጥማት 90 ሺህ ያክል ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ ብሏል።

አሁን ሩጫው ከተማዋን ከርዕደ-መሬት አደጋ መታደግ ነው።

ሜሱት በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ካህራማንማራስ በተሰኘችው ደቡባዊት ከተማ የሚኖሩ ዘመዶቹን አጥቷል።

በቅርቡ ወደ ሥፍራው ሄዶ ለቅሶ ደርሶ መምጣቱን ይናገራል።

“ትዝ ይለኛል ንጋት 10 ሰዓት ገደማ ተደውልሎኝ ስነቃ ከስልኩ ሌላኛው ጫፍ ጩኸት ይሰማኛል” ሲል ሳግ እየተናነቀው ሁኔታውን ያስታውሳል።

“ወደ ቦታው ለሶስት ቀናት ያክል መሄድ አልቻልንም። እዚያ ስንደርስ ቦታው ተደረማምሷል። እንዴት እንደምገልፀው አላውቅም። ፈጣሪ ሌሎችን ከዚህ ይጠበቅ።”

በደቡብ ቱርክ ከደረሰው መሬት መንቀጥቀጥ በኋላ የኢስታንቡል ከተማ አስተዳደር ከመቶ ሺህ በላይ ሕንፃዎችን ይመርመር የሚሉ ማመልከቻዎች ደርሰውታል።

አሁን ወረፋው በመብዛቱ አንድ ሕንፃ ለማስመርመር ከሶስት አራት ወራት በላይ መጠበቅ ግድ ይላል።

ተከራይም ሆነ አከራይ ሕንፃ እንዲመረመር መጠየቅ ይችላሉ። ነገር ግን የገንዘብ ቅጣት ሊያስከትል ስለሚችል አንዳንድ ሰዎች ሳያመልክቱ ይቀራሉ።

በመሬት መንቀጥቀጥ ስጋት ምክንያት ከጋራ መኖሪያ ሕንጻ ለቀው ለሚወጡ ሰዎች የሚሰጣቸው ድጎማ አነስ ያለ ነው።

የከተማዋ ከንቲባ ኤክሬም ኢማሞግሉ የአደጋ ጊዜ ሠራኞች የተሻለ ሥልጠና እንደሚሰጣቸው ገልጠዋል።

አልፎም በአደጋ ጊዜ 4.5 ሚሊዮን ሰዎች የሚያስጠጋ መጠለያ ሊሠራ እንደሆነ ተናግረዋል። ነገር ግን ብዙዎች ይህ በቂ አይደለም ይላሉ።

በኢስታንቡል ጎዳናዎች ሲጓዙ ነዋሪዎች ለምን ስጋት እንደያዛቸው ይገባዎታል።

ስትራክቸራል እና የመሬት መንቀጥቀጥ ኢንጂነር የሆነው ዶ/ር ኩርቱሉስ አታሴቬር የኮንክሪት ጥራት ወሳኝ እንደሆነ ለቢቢሲ ይናገራል።

“ከፀሐይ የሚከላከል ጥላ ያላቸው ቤቶች አሉ። ደካማ አሊያም ስስ ወለል ያላቸው ብዙ ናቸው። አጫጭር ቋሚ የተሸከማቸው ሕንፃዎችም አሉን። ብቻ ብዙ ችግር ያለባቸው ሕንፃዎች ሞልተዋል።”

በቀላሉ ለመግለጥ በርካታ የኢስታንቡል ሕንፃዎች መሠረታቸው ደካማ ስለሆነ መሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰት ከላያ ያለውን ጫና መቋቋም አይችሉም።

ኢስታንቡል 50 ኪሎ ሜትር የሚረዝም መሬት መንቀጥቀጥ ሲመጣ የሚጠቁም ሽቦ እየቀበረች ነው። ነገር ግን ከተማዋ በጣም ትልቅ ስለሆነች ነዋሪዎች በአደጋ ጊዜ ወዴት እንደሚሄዱ አያውቁትም።

የቱርክ ፕሬዝደንታዊና የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ ሁለት ወራት ይቀሩታል። የመሬት መንቀጥቀጥ አንዱ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል።

የቱርክ መሬት መንቀጥቀጥ የሃገሪቱን ኢኮኖሚም አንዘፍዝፏል። ብዙዎች መንግሥት በወሰደው የአደጋ ጊዜ እርምጃ ደስተኛ አይደሉም።