የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ በኢትዮጵያ እና ጋዜጠኞች የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች

ለአስርታት ኢትዮጵያ በጋዜጠኞች እስር እና በፕሬስ ነጻነት ላይ ጫናን በማሳደር ስትወቀስ ቆይታ፤ ይህ ሁኔታ ተለውጦ የታሰሩ ጋዜጠኞች ሁሉ ተፈትተው፣ በርካታ የፕሬስ ውጤቶች ወደ ገበያ ተመልሰው ነበር።

ነገር ግን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ በፕሬስ ነጻነት በኩል የተፈጠረው ተስፋ ቀስ በቀስ ፈተና እየገጠመው መሆኑን የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪዎች እና ማኅበራት እየገለጹ ነው።

ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ ሲፒጄ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ከመጋቢት 25 እስከ ሚያዝያ 05/2015 ዓ.ም. ድረስ ባሉ አስራ አንድ ቀናት ውስጥ አዲስ አበባ ውስጥ ስድስት እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ደግሞ ሁለት ጋዜጠኞችን እስር እና እንግልት እንደተፈጸመባቸው አስታወቆ ነበር።

በአገሪቱ ውስጥ ተቃውሞ እና ፖለቲካዊ ውጥረት በሚከሰትበት የበይነ መረብ አገልግሎት መቋረጥ የጋዜጠኞች መታሰርና መዋከብ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጥማሉ።

ሲፒጄም ችግር በሚከሰትበት ጊዜ ከሕግ ውጪ ጋዜጠኞችን ማሰር እንዲቆም እና የፀጥታ ኃይሎች በጋዜጠኞች ላይ ፈጽመውታል የተባሉ ጥቃቶች እንዲመረምሩም መንግሥትን ጠይቋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የደቡባዊ አፍሪካ የሚዲያ ኢኒስቲቲዩት የዓለም ፕሬስ ነጻነት ቀንን በማስመልከት ባወጡት መለግለጫ ላይ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት በከፍተኛ ጥቃት ስር እንደሆነ አመልክተዋል።

በዚህም ሳቢያ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በመላው አገሪቱ ቢያንስ 29 ጋዜጠኞችን እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን አስረዋል። ትግራይ ውስጥም የክልሉ ባለሥልጣናት አምስት ጋዜጠኞችን “ከጠላት ጋር ተባብረዋል” በሚል ከሰዋል።

ጨምሮም ጋዜጠኞች በሚሰሯቸው ዘገባ የተነሳ እስር፣ እንግልት እና ወከባ እንደገጠማቸው እንዲሁም አንድ የውጭ አገር ጋዜጠኛም ከኢትዮጵያ እንዲባረር መደረጉን በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

እየበረታ የመጣው ጫና

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የእርስ በእርስ ቁጥጥር ሥርዓት እንዲኖር የሚሰራው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤትም ባወጣው መግለጫ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጋዜጠኞች ከሕግ አግባብ ውጪ ታፍነው እየታሰሩ እና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብርበራ እየተካሄደባቸው ነው” ብሏል።

በሚዲያ አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ጋዜጠኞች በፖሊስ ሲያዙም ሆነ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ባለመሆኑ ባለሙያዎች ሥራቸውን በነጻነት እንዳይሠሩ ከማድረጉም በላይ የፕሬስ ምኅዳሩ እንዲጠብ እያደረገው ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም (ኢሰመኮ) በተመሳሳይ የሚዲያ አባላትንና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ዒላማ ያደረገ እስር እና ወከባ በእጅጉ አሳሳስቦኛል ብሎ ነበር።

ኮሚሽኑ የሚዲያ አዋጁን በሚጻረር መልኩ የታሰሩ እና ክስ ሳይመሠረትባቸው በእስር የቆዩ መኖራቸውን ባደረኩት ክትትል ተመልክቻለሁ ብሏል።

የመብት ተሟጋቹ ኢሰመኮ እንዳለው በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሠረት በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው በተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ጠይቋል።

ጨምሮም በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ታሳሪዎች በሙሉ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ” ኮሚሽኑ ጠይቆ ነበር።

የሕግ ጥሰት

ጋዜጠኞች የሚፈጽሟቸው ስህተቶች ወይም የሕግ መተላለፎች ወደ እስር እና ፍርድ ቤት ከመሄዳቸው ይልቅ በሙያተኞች መካከል በሚደረግ ቁጥጥር እና በግልግል መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚሰራው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ታምራት ኃይሉ ጠቅላይ ሚንስት ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ለዘርፉ ጠቃሚ የሆኑ ሕጎች ወጥተዋል ይላሉ።

ለምሳሌም ኢትዮጵያ ያልነበራት የሚዲያ ፖሊሲ ወጥቷል። በአዲሱ የመገኛኛ ብዙሃን አዋጅ ዲጂታል ሚዲያ ዕውቅና ተሰጥቶታል። ስም ማጥፋትን በተመለከተ የወንጀል ተጠያቂነት መሆኑ እንዲቀር ተደርጓል። የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት እና የጥላቻ ንግግሮችን ለመቆጣጠረ የወጡ አዋጆችን ጠቅሰዋል።

ነገር ግን አፈጻጸማቸው ላይ ግን ክፍተቶች ከመግጠማቸው ባሻገር “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ በመምጣታቸው የሚዲያ ሥራ እጅግ አስጊ እስከመሆን ደርሷል ብለን እናምናለን” ሲሉ አቶ ታምራት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አክለውም በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ መሠረት ጋዜጠኞች ሲያጠፉ በቀጥታ ምርመራ ተደርጎ ለዐቃቤ ሕግ እንዲቀርቡ ቢጠይቅም “የፀጥታ አካላት ጋዜጠኞችን ያስራሉ፣ ያፍናሉ፣ ያሰሩበት ቦታም አይታወቅም። ፍርድ ቤት ያመላልሳሉ። ዋስትና ቢፈቀድላቸውም አይለቀቁም። አንድ ፍርድ ቤት የለቀቀውን ሌላ ቦታ የመከስሰ ነገርም ይታያል” ብለዋል።

እየጠበበ ያለው ምኅዳር

ከ50 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው እና ከ450 በላይ አባላት አለኝ የሚለው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት መሠረት አታላይ፣ ማኅበሩ የዕድሜውን ያህል “የጋዜጠኞችን መብት እና የፕሬስ ነጻነትን ለማስጠበቅ በቂ ሥራ አልሠራም” ይላሉ።

ማኅበሩ ከመንግሥት ጫና ስር አልወጣም የሚሉት አቶ መሠረት “በኢትዮጵያ መብቱ እና ሕጉ ቢኖርም የፕሬስ ነጻነት በተሟላ መልኩ የለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለአቶ ታምራት ችግሩ ከዚህም ይሰፋል። ሐሰተኛ እና የጥላቻ ንግግሮች “በመንግሥት ባለሥልጣናት እና ከመንግሥት ጋር ቅርበት ባላቸው ግለሰቦች” ሲሰራጩ በዝምታ እየታለፉ ጋዜጠኞች ግን በሥራቸው እስር እና እንግልት እየገጠማቸው ነው ይላሉ።

ከጋዜጠኞች ባሻገር ጥቂት የማይባሉ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትም የደኅንነት ስጋት ተጋርጦባቸዋል። ባለፉት ወራት ጥቂት የማይባሉ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚሰሩ ተቋማት ላይ ዘረፋ መፈጸማቸው ተዘግቧል።

አቶ ታምራት እንደሚሉት የመገናኛ ብዙኃን ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ በሕግ ቢገለጽም “አንዳንዶች ቢሯቸው ተሰብሮ የሥራ መሣሪያዎቻቸውን ተወስዶባቸዋል። ጋዜጠኞች ሲታሰሩ በብርበራ ሰበብ የተወሰዱ ዕቃዎቻቸው እስካለመመለስ ደርሷል።”

“ሁኔታዎች በጣም እየተባባሱ ነው የመጡት” የሚሉት አቶ ታምራት “አንዳንዴም ጋዜጠኞች ከታሰሩ በኋላ በሽብርተኝነት ስም የማንገላታት ነገር ይስተዋላል። ሁኔታው ትንሽ እየተባባሰ እንደመጣ እንወስዳለን። የሕግ መሻሻሎች ቢኖሩም፣ ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉ ነገሮችን ነጻነቱን እያጠበበው ነው” ብሏል።

እነዚህ ሁሉ ክስተቶችን ከግምት በማስገባት ተስፋ ሰጪ የነበረው የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ምኅዳር ጠቧል ብለው አቶ ታምራት ያስባሉ።

የሙያዊ ነጻነት ጉዳይ

አቶ መሠረት ደግሞ ማስፈራሪያ እና ዛቻ በተለይም በዲጂታል መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞች እና የማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ በስፋት እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ።

በመንግሥት ስር በሚተዳደሩት የመገናኛ ብዙኃን ዘንድ ደግሞ የሙያዊ ነጻነት ጉዳይ አንደ ችግር የሚታይ መሆኑን የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ መሠረት ያነሳሉ።

በኢትዮጵያ ትልልቅ የሚባሉትን የሚዲያ ተቋማት የሚቆጣጠረው መንግሥት ነው። ስለዚህም “የመንግሥትን በጀት እየወሰዱ መንግሥትን መተቸት አይችሉም። በዚህም መንግሥት ከሚለው በላይ አልፈው ስህተቶች እንዲታረሙ አቅጣጫ ማሳየት አልቻሉም።”

የፕሬስ ነጻነት እንዲከበር ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ነጻ ሆነው መሥራት አለባቸው ብለው ለሚያምኑት አቶ መሠረት፣ ሙያተኞች "ከመንግሥት ወይም ከተቃዋሚዎች ጋር ይለጠፋሉ” ይላሉ።

ለፕሬስ ነጻነት መከበር

ወደ 61 ሚጠጉ የሚዲያ ተቋማት እና የጋዜጠኞች ማኅበራት አባል የሆኑበት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት፣ የመገናኛ ብዙኃን አዋጁን የተቃረኑ አካሄዶች እና የሕግ ጥሰቶች በሚኖሩበት ጊዜ እንዲታረሙ ጥረት ይጥራል።

በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ውስጥ እየገጠሟቸው ነው ላሉት ችግሮች “መንግሥት የወጣው ሕግ በትክክል መተርጎሙን ማረጋገጥ፤ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ሕግን አክብረው ሥርዓት ባለው መንገድ መሥራታቸውን በተግባር ማሳየት ያስፈልጋቸዋል” ይላሉ አቶ ታምራት።

አክሎም በሕብረተሰቡ ዘንድ ደግሞ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ በሁሉም የሚተገበር መከበር ያለበት መሆኑን ከማወቅ ባለፈ፣ በመገናኛ ብዙኃን እና በጋዜጠኞች ላይ ጥቃት እና እስር በሚፈጸምበት ጊዜ ለምን? የሚል ማኅበረሰብ መፍጠር ያስፈልጋል ብሏል።

አቶ መሠረትም የፕሬስ ነጻነት እንዲኖር ሙያተኞች እና መገናኛ ብዙኃን ከመንግሥት ጫና ነጻ ሆነው እንዲዘግቡ እና እንዲሰሩ ማድረግ ወሳኝ እንደሆነ ይናገራሉ።