ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) አባት የሚባሉት ሳይንቲስት መጪው ዘመን አስፈሪ ነው አሉ
የሰው ሠራሽ አስተውሎት አባት ነው የሚባሉት ጀፍሪ ሒንተን ቻትጂፒቲን የመሰሉ ፈጠራዎች የሰው ልጅን መልሰው ሊቆጣጠሩት እንደሚችሉት ፍንጭ ሰጡ።
የ75 ዓመቱ ጀፍሪ ሒልተን ይህን የተናገሩት ጉግል ኩባንያን በለቀቁበት ወቅት ነው።
እኒህ ሳይንቲስት ለኒውዮርክ ታይምስ በጻፉት ሐተታ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዙርያ በሠሯቸው ሥራዎች አሁን ላይ ጸጸት እንደሚሰማቸው ጠቅሰዋል።
ሳይንቲስቱ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ደግሞ እንዴት አንዳንድ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፈጠራዎች ‘አስፈሪና አደገኛ’ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተንትነዋል።
‘ሰው ሠራሽ አስተውሎት ፈጠራዎች ለጊዜው ከሰው ልጅ በላይ አልሆኑም፤ በጊዜ ሂደት ግን የሰው ልጅን ይቆጣጠሩታል ይመስለኛል’ ብለዋል።
የዶ/ር ሒንተን በሰው ሠራሽ አስተውሎትና ልህቀት ዙርያ ያደረጓቸው ጥናትና ምርምሮች ቻትጂፒቲን ለመሰሉ ትልልቅ ሥራዎች መፈጠር መሠረት የጣሉ ናቸው።
የብሪታኒያና ካናዳ ጥምር ዜጋ የሆኑት ሳይንቲስቱ የአስተውሎት ሥነ ልቡና (cognitive psychologist) እና የኮምፒውተር ሳይንስ ዝነኛ ተመራማሪ ናቸው።
ከጉግል መልቀቃቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ቻትቦት በቅርብ ጊዜ የሰው ልጅ አእምሮ ሊሸከመው የሚችለውን መረጃ በተሻለ ሊሰንድ ይችላል ብለዋል።
”ለምሳሌ አሁን ጂፒቲ በጠቅላላ ዕውቀት ዙርያ ካየነው የሰው ልጆችን በሙሉ ይበልጣል። በምክንያታዊነትና ሚዛናዊነት ካየነው ገና ከሰው ልጅ አቅም አልደረሰም። ነገር ግን ምክንያታዊነትና አመክንዮን ቀስ በቀስ ተምሮ የሰው ልጅን ሊልቅ ይችላል” ብለዋል።
ሳይንቲስቱ ዶ/ር ሐንተን ጨምረውም፣ ‘አሁን ባለው ፍጥነት የሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰው ልጅን አስተውሎት በልጦ ለመገኘት ብዙ ዘመን አይወስድበትም’ ብለዋል።
በኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ደግሞ ዶ/ር ሒንተን ይህን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፈጠራ በጎ ላልሆኑ ጉዳዮች ማስፈጸሚያ የሚያውሉ አካላትን ወቅሰዋል።
የሰው ልጆችንና ቻትቦትን በማወዳደር አደገኛነቱን ሲያስረዱም፣10ሺህ ሰዎችን ለማሰልጠንና አንድ ቦታ ለማድረስ የሚወስደውን ዘመን በማሳያነት በመጥቀስ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ግን አንድን መረጃ አንድ ጊዜ ከተማሩት በኋላ በቅጽበት 10ሺህ ማሽኖች አወቁት ማለት ነው። ይህ ለሰው ልጅ ስጋት ነው ብለዋል።
ዶ/ር ሒንተን ሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ እየተሠራ ያለው ነገር አሳስቧቸው ሥራ መልቀቃቸውን ቢጠቅሱም ሌሎች ምክንያቶችም ሥራ ለመልቀቃቸው ምክንያት መሆናቸውን አልሸሸጉም።
“አሁን ዕድሜዬ 75 ደረሰ። ጡረታ ጊዜዬ ነው። ስለ ጉግልም በጎ ነገሮችን መናገር አለብኝ፤ ለጉግል እየሠራሁ ስለ ጉግል በጎ ነገር ባወራ አያምርብኝም፤መልቀቅ ነበረብኝ’ ብለዋል።
ዶ/ር ሒንተን ጉግል የሰው ሠራሽ አስተውሎትን በተመለከተ ኃላፊነት የሚሰማው ድርጅት እንደሆነ መስክረዋል።