ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጋዜጠኞች ከሕግ አግባብ ውጪ እየታሰሩ ነው አለ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጋዜጠኞች ከሕግ አግባብ ውጪ ታፍነው እየታሰሩ እና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብርበራ እየተካሄደባቸው ነው አለ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ሚያዚያ 9/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በሚዲያ አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ጋዜጠኞች በፖሊስ ሲያዙም ሆነ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ባለመሆኑ ባለሙያዎች ስራቸውን በነጻነት እንዳይሰሩ ከማድረጉም በላይ የፕሬስ ምህዳሩ እንዲጠብ እያደረገው ነው ብሏል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሁለት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ የሚዲያ አባላትንና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ዒላማ ያደረገ እስር እና ወከባ በእጅጉ አሳሳስቦኛል ብሎ ነበር።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በመግለጫው በሚዲያ አማካይነት የወንጀል ድርጊት በመፈፀም የተጠረጠረ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት የሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዓቃቤ ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት አዋጅ ቁጥር 1238/13 ጠቅሶ አስታውሷል።
ይሁን እንጂ ጋዜጠኞች እንደ ማንኛውም ተከሳሽ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው ለፖሊስ በመፍቀድ እንዲታሰሩ ማድረግ በምንም መለኪያ ተቀባይነት የለውም ብሏል ምክር ቤቱ በመግለጫው።
በተመሳሳይ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሚዲያ አዋጁን በሚጻረር መልኩ የታሰሩ እና ክስ ሳይመሠረትባቸው በእስር የቆዩ መኖራቸውን ባደረኩት ክትትል ተመልክቻለሁ ብሏል።
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሠረት በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት በማቅረብ ተፈጻሚ መሆን አለበት ያለ ሲሆን፤ በሚዲያ አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ታሳሪዎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ ኢሰመኮ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ምክር ቤት የዜጎች መብት በፍትሕ አካላት በተደጋጋሚ እየተጣሰ ነው ካለ በኋላ ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ በመግለጫው ጠይቋል።
መንግሥት መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ ተግባሩ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በማያጠብና የዜጎችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተሳትፎ በማያቀጭጭ መልኩ ሊሆን ይገባል ያለው ምክር ቤቱ፤ የፍትሕ ሥርዓቱ በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ ድንጋጌ ብቻ በመመራት ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቋል።