የጦር ምርኮኞች እነማን ናቸው? ከተያዙ በኋላስ በምን ሁኔታ መቆየት አለባቸው?

ዓለም አቀፍ ሕግ፣ በጦርነት ወቅት በተቀናቃኝ ቡድን እጅ የሚወድቁ ወይም በፍቃዳቸው እጅ የሚሰጡ ተዋጊዎች ከተያዙ በኋላ ቆይታቸው ምን መምሰል እንዳለበት ይደነግጋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዓለም አቀፍ ሕግ፣ በጦርነት ወቅት በተቀናቃኝ ቡድን እጅ የሚወድቁ ወይም በፍቃዳቸው እጅ የሚሰጡ ተዋጊዎች ከተያዙ በኋላ ቆይታቸው ምን መምሰል እንዳለበት ይደነግጋል

በተለያዩ አገራት በሚካሄዱ ጦርነቶች ውስጥ ስለተያዙ የጦር ምርኮኞች ሁኔታ በተደጋጋሚ ሲነገር እንሰማለን።

ይህም ሁለት ተፋላሚ ወገኖች አንዳቸው በሌላቸው ላይ ነጥብ ከሚያስቆጥሩባቸው መንገዶች አንዱ ተደርጎም ይወሰዳል።

በዩክሬን ጦርነት የማሪዩፖል ከተማን እየተከላከሉ የነበሩ ወታደሮችን እንደ ማሳያ እንውሰድ።

በማሪዩፖል በሚገኘው አዞቫስታል የብረት ፋብሪካ ውስጥ የነበሩ ከ1,000 በላይ የሚሆኑ የዩክሬን ወታደሮችን ሩሲያ እንደያዘች አስታውቃለች።

የጦር ምርኮኞቹ ሩሲያ የምትደግፋቸው የዩክሬን አማጽያን በተቆጣጠሯቸው ቦታዎች እንዲቆዩ ተደርጓል።

እነዚህ ምርኮኞች በዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት እንደሚያዙም ሩሲያ ተናግራለች።

ይህ ዓለም አቀፍ ሕግ፣ በጦርነት ወቅት በተቀናቃኝ ቡድን እጅ የሚወድቁ ወይም በፍቃዳቸው እጅ የሚሰጡ ተዋጊዎች ከተያዙ በኋላ ቆይታቸው ምን መምሰል እንዳለበት ይደነግጋል።

ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አንደኛው ሌላኛውን የጦር ምርኮኞችን በማንገላታት ሲከሱ ተሰምቷል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ተቆጣጣሪ ቡድን ኃላፊ የሆኑት ማቲልዳ ቦግነር፣ ሁለቱም አገራት የጦር ምርኮኞችን በአግባቡ እንዳልያዙ "አስተማማኝ መረጃ" ተገኝቷል ብለዋል።

በጄኔቫ ስምምነት መሠረት የጦር ምርኮኞች ከተያዙ ወይም እጅ ከሰጡ በኋላ በተገቢው ሁኔታ መያዝ አለባቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጄኔቫ ስምምነት መሠረት የጦር ምርኮኞች ከተያዙ ወይም እጅ ከሰጡ በኋላ በተገቢው ሁኔታ መያዝ አለባቸው

ዓለም አቀፍ ሕግ ምን ይላል?

በጄኔቫ ስምምነት መሠረት የጦር ምርኮኞች ከተያዙ ወይም እጅ ከሰጡ በኋላ በተገቢው ሁኔታ መያዝ አለባቸው።

ይህም ከጎርጎሮሳውያኑ 1929 ጀምሮ መተግበር የጀመረ ደንብ ነው።

የጦር ምርኮኞች በሰብአዊ ሁኔታ እንዲያዙ፣ ስለ ይዞታቸው መረጃ እንዲቀርብ እንዲሁም በጦርነቱ ተሳታፊ ባልሆኑ ገለልተኛ አገራት እንዲጎበኙ ዓለም አቀፍ ሕጉ ያዛል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ብዙ አገራት ሕግ ጥሰዋል መባሉን ተከትሎ፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቱ በ1949 ማሻሻያ ተደርጎበታል።

ማሻሻያው የጦር ምርኮኞች ክብራቸው እንዴት ሊጠበቅ እንደሚገባ ይገልጻል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ይህንን የጄኔቫ ስምምነት 196 አገራት ፈርመዋል።

ለጦር ምርኮኞች ምን መደረግ አለበት?

ምግብ፣ ሕክምና፣ ማረፊያ ማግኘትን ጨምሮ የጦር ምርኮኞዎች ማግኘት የሚገባቸው ነገሮች በርካታ ናቸው።

ከእንግልት እና ከጉልበት ብዝበዛ የመጠበቅ መብትም አላቸው።

የጦር ምርኮኞቹ የሚያዙት በጦርነት ተሳታፊ እንዳይሆኑ እንጂ እንደ ቅጣት እንዳልሆነ ዓለም አቀፍ ስምምነቱ ይገልጻል።

ስለዚህም ማስፈራራት፣ ስድብ እና ሕዝባዊ ማንጓጠጥ ሊደርስባቸው አይገባም።

የጄኔቫ ስምምነት ፈራሚ የሆኑት ሩሲያ እና ዩክሬን ወቀሳ የበዛባቸው እነዚህን ስምምነቶችን በመጣሳቸው ነው።

የጦር ምርኮኞችን በቴሌቭዥን በማሳየትና ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ በማካተት አገራቱ ተተችተዋል።

የጄኔቫ ስምምነት እንደሚለው አንድ የጦር ምርኮኛ በጦርነት ላይ በመሳተፉ እንዲህ ያለ እንግልት ሊገጥመው አይገባም።

አገራት የጦር ምርኮኞችን በጦር ወንጀል ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብ ግን ይችላሉ።

በሌላ በኩል ጦርነት ሲቆም የጦር ምርኮኞች "ሳይዘገይ" ወደ አገራቸው መመለስ ይኖርባቸዋል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ብዙ አገራት ሕግ ጥሰዋል መባሉን ተከትሎ፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቱ በ1949 ማሻሻያ ተደርጎበታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ብዙ አገራት ሕግ ጥሰዋል መባሉን ተከትሎ፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቱ በ1949 ማሻሻያ ተደርጎበታል

የጦር ምርኮኛ የሚባሉት እነማን ናቸው?

የጄኔቫ ስምምነት እንደሚለው በዚህ ውስጥ የሚካተቱት ተዋጊዎች ብቻ አይደሉም።

በውጊያው ያልተሳተፉ የሚሊሻ አባላት እና ንጹሀን ዜጎች (ሲቪሎች) በዚህ ማዕቀፍ ይካተታሉ።

በዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተቱት ሰላዮችና ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው።

ሰላዮች በጦር ምርኮኞች ዝርዝር ውስጥ ባይካተቱም እንኳን ሰብአዊ ክብራቸው ተጠብቆ መያዝ እንዳለባቸው በጄኔቫው ስምምነት ተደንግጓል።

ሰላዮች በሕግ መጠየቅ ያለባቸው ባልተዛባ የፍትሕ ሥርዓት እንደሆነም ይጠቁማል።

የጦር ምርኮኞች ልውውጥ ምንድን ነው?

ሁለት ተቀናቃኝ ቡድኖች የጦር ምርኮኞችን ለመለዋወጥ የሚስማሙበት አጋጣሚ ይፈጠራል።

በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አሜሪካ እና ሶቪየት ኅብረት ያደረጉት ስምምነት እና የእስራኤል እና ፍልስጤም የወታደሮች ልውውጥ ስምምነት ይጠቀሳሉ።

ጄኔቫ የእስረኞች ልውውጥን በተመለከተ ደንብ ቢያወጣም፣ ከዚህ ደንብ መጽደቅ በፊትም የእስረኞች ልውውጥ ይደረግ ነበር።

ከ18ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ የተካሄደ ነው።

በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የጦር ምርኮኞች ልውውጥ ቢደረግም፣ የሩሲያ ምክር ቤት ከዚህ በኋላ ልውውጦች እንዳይካሄዱ የሚደነግግ ሕግ ለማውጣት እየተዘጋጀ ይገኛል።

ተፋላሚዎች ሁሌም ሕጉን ያከብራሉ?

አያከብሩም።

ለምሳሌ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጃፓን ወደ 10ሺህ የሚጠጉ የጦር ምርኮኞችን በረሃብና በበሽታ በመግደል ትወነጀላለች።

እአአ ከ1991 እስከ 2001 በተደረገው በዩጎዝላቪያው ጦርነትም ተመሳሳይ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸው ይነገራል።

የክሮኤሽያ-ሰርብ የቀድሞው ወታደር 200 የጦር ምርኮኞችን በመግደል የ20 ዓመት እስራት እንደተፈረደበት ይታወሳል።

እአአ ለ1965 እስከ 1975 በተካሄደው የቬትናም ጦርነት፣ አሜሪካ እና ሰሜን ቬትናም በጦር ምርኮኞች ላይ ወንጀል በመፈጸም ተወቅሰዋል።

አሜሪካ በሽብር ወንጀል ጠርጥራ በተለይም በጓንታናሞ ቤይ ያሰረቻቸው ግለሰቦችን ሰብአዊ መብት በመጣስ ትከሰሳለች።

ይህ በኩባ የተከፈተው ጓንታናሞ ቤይ እስር ቤት ከመስከረም 11ዱ ጥቃት በኋላ በሽብር የተጠረጠሩ ሰዎች የታሰሩበት ነው።

በዚህ የግንቦት ወር የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት 42 አባላት ያሉት መርማሪ ቡድን ሩሲያ የጦር ወንጀሎች ፈጽማ እንደሆነ እንዲያጣራ እንደሚያሰማራ ገልጿል።